የኢትዮጵያ መንግሥት የስድስት ወራት የሀገር ውስጥ ወለድ ክፍያ ካለፈው ዓመት 250% ጨመረ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 28 2018
ያለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ መንግሥት የዕዳ ክፍያ ግዴታ ከ2017 ተመሣሣይ ወቅት አኳያ ሲነጻጸር በሀገር ውስጥ ወለድ እና ፍሬ ብድር ክፍያ ምክንያት እንደጨመረ የገንዘብ ሚኒስቴር ትላንት ማክሰኞ ይፋ ያደረገው ሪፖርት አሳይቷል።
በዐይነቱ የመጀመሪያ የሆነው “የማክሮ ኢኮኖሚ እና መዋቅራዊ ማሻሻያ ሪፖርት” ያለፉትን የ18 ወራት አፈጻጸም እና የወደፊት አካሔድ ይፈትሻል።
በሪፖርቱ መሠረት የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት የ2018 የመጀመሪያ መንፈቅ የሀገር ውስጥ ዕዳ ወለዱ 126.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል። ወለድ ለስድስት ወራት ለዕዳ ክፍያ ከተመደበው 64.6 በመቶ ድርሻ አለው።
መንግሥት ለሀገር ውስጥ ዕዳ የከፈለው ወለድ ከ2017 ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ግን ከ250 በመቶ በላይ ጨምሯል። በሪፖርቱ መሠረት በ2017 የመጀመሪያ ስድስት ወራት መንግሥት 36 ቢሊዮን ብር ለሀገር ውስጥ ወለድ ከፍሎ ነበር።
የውጭ ዕዳ ወለድ በአንጻሩ በ2018 የመጀመሪያ መንፈቅ ባለፈው ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ከነበረበት 11.7 ቢሊዮን ብር መለስተኛ ጭማሪ አሳይቶ 16.9 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
የሀገር ውስጥ ወለድ ለምን አሻቀበ?
ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የመንግሥት ወጪ እየሰፋ ሲሔድ “ገንዘብ ማተም ተለምዷል” ሲሉ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ይናገራሉ። መንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ሲሸጥ የሚከፍለው ወለድ እስከ 2 በመቶ ብቻ ነበር።
በዋንኛነት “የጡረታ ገንዘብን እና የልማት ባንክ ከፍተኛ ገንዘብን” ይጠቀም የነበረ ሲሆን የሚከፈለው ወለድ ዝቅተኛ ነበር። በዚህም ምክንያት ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት “የግል ባንኮች መሳተፍም ትተው ነበር።” ከአምስት ዓመታት ገደማ በፊት ለግምጃ ቤት ሰነድ የሚከፈለው ወለድ “ገበያውን የሚያንጸባርቅ” ሆኖ ከ16 እስከ 18 በመቶ ደርሷል።
መንግሥት የበጀት ጉድለትን ለመሙላት ከብሔራዊ ባንክ መበደር ማቆሙ በእርግጥም ለማክሮ ኤኮኖሚ መረጋጋት አዎንታዊ እንደሆነ በገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ የተደረገው ሪፖርት ያደንቃል። ይሁንና የዕዳ ክፍያ ወጪ እንዲጨምር ማድረጉን እና የጥሬ ገንዘብ እጥረት ማስከተሉን አትቷል።
በሪፖርቱ መሠረት ከ2017 በጀት ዓመት የዕዳ ክፍያ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የወለድ ክፍያ ነው። በዓመቱ መንግሥት 100.6 ቢሊዮን ብር ዕዳ የከፈለ ቢሆንም አብዛኛው ለሀገር ውስጥ ወለድ የዋለ ነው። በዓመቱ 97.53 ቢሊዮን ብር ለሀገር ውስጥ ወለድ ሲከፈል 3.09 ቢሊዮን ብር ለዕዳ ክፍያ ውሏል።
መንግሥት የበጀት ጉድለት ባጋጠመው ቁጥር ለመሸፈን ተጨማሪ ለመበደር እንደሚገደድ የገለጹት ዶክተር አብዱልመናን በዚህም የወለዱ መጠን “በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ” እንደሚሔድ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ብድር ስንት ነው?
የገንዘብ ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መሠረት እስከ መጋቢት 22 ቀን 2018 ድረስ ያለው የኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ብድር 51.8 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። የውጭ ብድር 33.5 ቢሊዮን ዶላር ድርሻ ሲይዝ የቀረው 18.3 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ የሀገር ውስጥ ብድር ነው።
ከሀገር ውስጥ ብድር ከፍተኛውን ድርሻ ማለትም 17.5 ቢሊዮን ዶላር የፌድራል መንግሥት ነው። በገንዘብ ሚኒስቴር የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መሠረት የተቀረው 800 ሚሊዮን ዶላር የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከብሔራዊ ባንክ የተበደሩት ነው።
የመንግሥት የሀገር ውስጥ ብድር እንዲጨምሩ ካደረጉ እርምጃዎች አንዱ የገንዘብ ሚኒስቴር የ10 ዓመት ቦንድ በማውጣት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የነበረባቸውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕዳ መረከቡ ነው። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከንግድ ባንክ የተበደረውን 263.3 ቢሊዮን ብር ጨምሮ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 845.3 ቢሊዮን ብር ዕዳ ወደ ረዥም ጊዜ ቦንድ የተቀየረው በጥቅምት 2017 ነበር።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀ አዋጅ የሚወጡት የዕዳ ሰነዶች ከሦስት ዓመታት የችሮታ ጊዜ በኋላ በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተከፍለው የሚጠናቀቁ ሲሆን በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና በንግድ ባንክ ሥምምነት የሚወሰን ወለድ ይከፈልባቸዋል።
እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 መንግሥት በግምጃ ቤት ቢል 492.3 ቢሊዮን ብር፣ በረዥም ጊዜ ቦንድ እና በግምጃ ቤት ቦንድ 2.2 ትሪሊዮን ብር እንደተበደረ ገንዘብ ሚኒስቴር ለሕግ አውጪው ምክር ቤት ባቀረበው ማብራሪያ አሳይቷል። በአጠቃላይ የመንግሥት የሀገር ውስጥ ብድር 2.7 ትሪሊዮን ብር ደርሷል። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 125.8 ቢሊዮን ብር ብድር ሲታከልበት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ዕዳ ብር 2.8 ትሪሊዮን ብር ደርሷል።
ለመንግሥት የሚያበድረው ማን ነው?
የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ በሚያደርገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የግል ባለወረቶች የመንግሥት የዕዳ ሰነዶችን እንዲገዙ አመቻችቷል። ዋንኛዎቹ ገዥዎች ግን የንግድ ባንኮች ናቸው። የ28፣ የ91 እና የ184 ቀናት የግምጃ ቤት ሰነዶችን እየገዙ የሚያበድሩት ባንኮች “በጣም ከፍተኛ የሆነ ወለድ ከመንግሥት ስለሚያገኙ ለእነሱም ተመችቷቸዋል” ሲሉ ዶክተር አብዱልመናን ያስረዳሉ። “የውጭ ብድር ብዙ ድርድር አለው” የሚሉት የገንዘብ ባለሙያው የሀገር ውስጥ ብድር ለመንግሥትም እንደቀለለው ያምናሉ።
ለ2018 የጸደቀው 1.9 ትሪሊዮን ብር የፌድራል መንግሥት በጀት 277.5 ቢሊዮን ብር ጉድለት እንደሚገጥመው ይጠበቃል። በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ብቻ የበጀት ጉድለቱ 93.6 ቢሊዮን ብር እንደነበር የገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት ይጠቁማል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት መንግሥት ከታክስ 710 ቢሊዮን ብር፣ ታክስ ካልሆኑት ካፒታል ገቢን ጨምሮ 55.4 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከብድር እና እርዳታ በበጀት ድጋፍ መልክ 171 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ሚያዚያ 26 ቀን 2018 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት አድርገዋል። በዘጠኝ ወራት የመንግሥት አጠቃላይ ገቢ 1.137 ትሪሊዮን ብር ነው።
በተመሣሣይ ጊዜ ውስጥ መንግሥታቸው የገጠመውን የበጀት ጉድለት ለመሸፈን 208 ቢሊዮን ብር ከሀገር ውስጥ የመበደር ዕቅድ ነበረው። ይሁንና የተበደረው ከዕቅዱ በላይ 232.4 ቢሊዮን ብር ነው። ከዚህ ውስጥ 12.4 ቢሊዮን ብር በግምጃ ቤት ቦንድ የተበደረው ሲሆን ቀሪው 220 ቢሊዮን ብር በግምጃ ቤት ቢል የተወሰደ እንደሆነ የአቶ አሕመድ ሽዴ ሪፖርት ይጠቁማል።
አቶ አሕመድ “የበጀት ጉድለትን ለመሙላት የዋጋ ግሽበትን ከማያባብሱ ምንጮች ወይም ከግምጃ ቤት ሰነድ እና ቦንድ ሽያጭ ከሀገር ውስጥ ብድር በመውሰድ መሸፈን ተችሏል” ሲሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረድተዋል። መንግሥት የበጀት ጉድለት ሲገጥመው ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደው የቀጥታ ብድር እንዲቆም ያደረገው ማሻሻያ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴን ጨምሮ በሀገሪቱ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ እንደ ትልቅ ስኬት የሚያቀርቡት ጉዳይ ነው።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ ከሁለት ሣምንታት ገደማ በፊት መንግሥታቸው ባለፉት 100 ቀናት እና በዘጠኝ ወራት ያሳካቸውን ጉዳዮች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ ሲያስረዱ “የበጀት ጉድለታችን ዝቅተኛ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። በ2017ም ይሁን በተያዘው ዓመት የበጀት ጉድለትን ለመሸፈን መንግሥት “አንድም ብር ከብሔራዊ ባንክ ቀጥታ” እንዳልተበደረ የገለጹት ዶክተር ፍጹም በመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ “ከፍተኛ ገንዘብ ማምጣት ችለናል” ሲሉ ተናግረዋል።
የበጀት ጉድለት ለመሙላት መንግሥት በቀጥታ ከማዕከላዊው ባንክ ሲበደርበት የቆየው አሠራር ተቀይሮ ፊቱን ወደ ሀገር ውስጥ ብድር ሲያዞር፤ አላስፈላጊ የገንዘብ ሕትመትን ለመግታት እና የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ያግዛል በሚል ዕምነት ነበር። መንግሥት የሚበደረው በገበያ መርኅ አማካኝነት በመሆኑ የፖሊሲ ተዓማኒነትን ያሳድጋል ተብሎም ይታመናል።
ዶክተር አብዱልመናን የገንዘብ ሕትመት መቆሙ ከፍ ያለ ፋይዳ እንዳለው ቢስማሙም አሁን መንግሥት የተከተለው አካሔድ ፈር መያዝ እንዳለበት ይሞግታሉ። “የገንዘብ ሕትመት የሚያመጣው ቀውስ በጣም መጠነ-ሰፊ ነው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን መንግሥት ባደረገው ማሻሻያ ይስማማሉ።
“ገንዘብ ሕትመት ይቁም ማለት ግን የመንግሥት ወጪ ልቅ ይሁን ማለት ዐይደለም። እንደነበረበት ይተውና ደግሞ ከሀገር ውስጥ፣ ከባንክ ሥርዓቱ ብድር ይውሰድ ማለትም ዐይደለም” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ወጪ እና ገቢውን ያጣጥም፤ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ክፍተቱን ይቀንስ ማለት ነው” ሲሉ አስረድተዋል። “ወጪ እና ገቢ ሳይጣጣም መንግሥት [ብር] ማተም ካቆመ ከሀገር ውስጥ በግምጃ ቤት ሰነድ መበደሩ አይቀርም። ያ ደግሞ ከፍተኛ ወለድ እንዲከፈል ያደርጋል” የሚል አቋም አላቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት የተከተለው አካሔድ ለራሱ ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን የግሉን ዘርፍ ጭምር ሊጎዳ የሚችል ነው። ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት ከገበያው “መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ ሲበደር ለግሉ ዘርፍ የሚቀርበው ይቀንሳል።” በዚህ ምክንያት ለግሉ ዘርፍ ለሚቀርበው ብድር የሚከፈለው ወለድ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ያደርጋል።
መንግሥት ከሀገር ውስጥ የሚበደረውን ጨምሮ የግሉ ዘርፍ ኢንዱስትሪ እና ግብርና ለመሳሰሉ ሥራዎች የሚፈልገው ከቀነሰ ልማትን ያዳክማል። የመንግሥት የበጀት ጉድለት፣ ዕዳ እና የሚከፍለው ወለድ በሌሎች ሃገራት “አጨቃጫቂ” ጉዳይ እንደሆነ የሚናገሩት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው በኢትዮጵያም በቅጡ ውይይት ሊደረግበት የሚገባ እንደሆነ ያምናሉ።
መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ የጤና ኬላ እና ሆስፒታል የመሳሰሉ መሠረተ-ልማቶች ሊሠራበት የሚገባ ገንዘብ ለወለድ ክፍያ ሲውል የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቸል ብሎ ሊመለከት እንደማይገባ ዶክተር አብዱልመናን ተናግረዋል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው “ፓርላማ ‘ከዚህ በላይ መሔድ የለብንም’ ብሎ በጣም ሊወያይበት የሚገባ ነው። የበጀት ጉድለት እና የግምጃ ቤት ሰነድ ጉዳይ በጣም በጣም ሊያጨቃጭቅ፣ ሊያወያይ የሚገባ ነው” ሲሉ ለጉዳዩ ተገቢው የሆነ አትኩሮት እንዲሰጥ አሳስበዋል።
አርታዒ ሸዋዬ ለገሠ