1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ እና የኦ.ነ.ሰ. መልስ

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ መጋቢት 11 2017

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጅባት ወረዳ በርካታ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) አባላት መገደላቸውንና በርካቶች ደግሞ ከበርካታ ወታደራዊ ቁሳቁሶች ጋር መማረካቸውን የመንግስት ምንጮች አመለከቱ፡፡ ተወሰደ በተባለው ወታደራዊ ኦፕሬሽን በርካታ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ እንዲሁም የተለያዩ ዓይነት ተተኳሾች በቁጥጥር ስር ዉለዋል

ፎቶ ማህደር፤ ኦሮምያ ክልል
ፎቶ ማህደር፤ ኦሮምያ ክልል ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ እና የኦ.ነ.ሰ. መልስ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ እና የኦ.ነ.ሰ. መልስ
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጅባት ወረዳ በርካታ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) አባላት መገደላቸውንና በርካቶች ደግሞ ከበርካታ ወታደራዊ ቁሳቁሶች ጋር መማረካቸውን የመንግስት ምንጮች አመለከቱ፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በበኩሉ በምዕራብ ሸዋ እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች አከባቢ በመንቀሳቀስ ባደረገው ወታደራዊ ኦፕሬሽን በርካታ የታጣቂው ቡድን አባላት በመደምሰስ 60 የሚሆኑትን መማረኩን በይፋዊ ማህበራዊ ገጹ አመልክቷል። ታጣቂ ቡድኑ በፊናው ጥቃቱን ሳያስተባብል መሰል ወታደራዊ እርምጃዎች ብቻቸውን ዘላቂ እልባት እንደማያመጡ ነው የገለጸው፡፡ 


የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በይፋዊ ማህበራዊ ገጹ ላይ እንዳመለከተው “በምዕራብ ሸዋና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖችና አካባቢዎች የተሰማሩት የማዕከላዊ ዕዝ የህዳሴ ኮርና የጋሻ ኮር አባላት” ያሏቸው የሰራዊቱ አባላት “የሸኔ ቡድን” ባላቸው ታጣቂዎች ላይ ተወሰደ ባለው የጥምረት ወታደራዊ እርምጃ “ከፍተኛ ድል” ማስመዝገቡን ነው የገለጸው፡፡
ተጠናክሮ በቀጠለ በተባለው በዚህ ወታደራዊ እርምጃ በታጣቂ ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ መድረሱን የገለጸው መከላከያ፤ በተወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ወይም ኦፕሬሽን በቁጥር ባልተጠቀሱ “በርካታ” በተባሉ የታጣቂው ቡድን አባላት በመደምሰስ 60 የሚሆኑትን ደግሞ መማረካቸውን አስረድቷል። በዚሁ ተወሰደ በተባለው ወታደራዊ ኦፕሬሽን በርካታ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ እንዲሁም የተለያዩ ዓይነት ተተኳሾች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም በመግለጽ ይህንኑን በምስል አሳይቷል።

 የኬንያ ፖሊስ እርምጃ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ላይ


ዶይቼ ቬለ ከሰሞኑ መነጋገሪያ በሆነው በዚሁ በመንግስት ተወሰደ በተባለው ወታደራዊ እርምጃ ላይ ዝርዝር ጉዳዮቹ ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅ ከትናንት ጀምሮ ዛሬም በተደጋጋሚ ለምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ እንዲሁም ለኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ የስልክ ጥሪን ጨምሮ መልእክት ብልክም ጥረቱ ለጊዜው አልሰመረም፡፡
ተወሰደ ስለተባለው ወታደራዊ እርምጃ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) በኩል አስተያየታቸውን የሰጡን የቡድኑ አዛዠዥ አማካሪ አቶ ጅሬኛ ጉዴታ ግን ጉዳዩን ሳያስተባብሉ ታጣቂዎቻቸው በአከባቢው መንቀሳቀሳቸው እንደቀጠለ መሆኑን ግን አስረድተዋል፡፡ “ጦርነት ባለበት መሰዋትና ማጥቃት ይኖራል” ያሉት አቶ ጅሬኛ በሰራዊቶቻቸው ላይ ስለደረሰው ጉዳት ለጊዜው በቁጥር መጥቀስ እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ታጣቂዎቻቸው በአከባቢው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አለመገታቱን ነው ያመለከቱት፡፡ “መፋለም ባለበት መሰዋት ይኖራል” ያሉት አቶ ጅሬኛ የደረሰባቸውን የጉዳት መጠን ከሰራዊቶቻቸው አመራር አለመስማታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሱሉልታ፦ በኦነግ-ኦነሰ አዲስ ጥቃት ያጠላው ስጋት


አቶ ጅሬኛ አክለውም መሰል ወታደራዊ እርምጃዎች ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ግን አያመጡም በማለት አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡ “ይሄ ለአገሪቱ ምንም መረጋጋትም ሰላምም የሚያመጣ ጉዳይ አይደለም” ያሊት አቶ ጅሬኛ፤ መፍትሄው ለፖለቲካው ጥያቄ በመመካከር እልባት መስጠት ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ታጣቂዎቹ በሰላም እንዲገቡ የሚሉ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎች በመገናኛ ብዙሃን ስስተጋቡ ተሰምተዋል፡፡ መንግስት በተደጋጋሚ በሚሰጣቸው መግለጫዎችም በሺዎች የሚቆጠሩ ያሏቸው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላት የሰላም ጥሪ ተቀብለው መግባታቸውን በማስረዳት የሰላም ጥሪውን ባልተቀበሉት ላይ ግን የሚወሰድ ወታደራዊ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲል ተሰምቷል፡፡ 

ፎቶ ማህደር፤ ኦሮምያ ክልል ምስል፦ Seyoum Getu/DW

በኦሮሚያ ክልል በታጣቂዎች መመለስ ነዋሪዎች ምን አሉ?
የኦነሰ አዛዥ አማካሪው አቶ ጅሬኛ ጉደታ እንደሚሉት ግን የሚቀርቡ የሰላም ጥሪዎች ቁርጠኝት የሚስተዋልባቸው መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግስት ለሰላም ባለው ቁርጠኝነት ላይ ጥያቄ ያነሱት አቶ ጅሬኛ፤ “ለሰላም እንቅፋት የሆነው የፖለቲካ ጥያቄ አለ፡፡ ይህ ደግሞ በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በአማራ፣ በትግራይ እና ሌሎችም ክልሎች ነውና ለነዚህ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ እልባት መስጠት ይሻል” ሲሉ ሰራዊታቸው በኦሮሚያ በስፋት በምንቀሳቀስበት ባሁን ወቅት ወታደራዊ እርምጃዎች ዘላቂውን መፍትሄ እንደማያመጡ ገልጸዋል፡፡ 


ሥዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ 
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW