የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች በየፊናቸው በመቶዎች ገደልን አሉ
ቅዳሜ፣ መጋቢት 13 2017
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች ባለፉት ቀናት በተካሔዱ ውጊያዎች በየፊናቸው በመቶዎች መግደላቸውን አስታወቁ። በርካታ የፋኖ ታጣቂዎች እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት መገደላቸው የተገለጸው በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ውጊያ ሁለተኛ ዓመቱን ሊደፍን በተቃረበበት ወቅት ነው።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል በሁለት ቀናት ከ300 በላይ የፋኖ ታጣቂዎች መግደሉን አስታውቋል። ጦሩ በርካታ የፋኖ አባላትን ገደልኩ ያለው በደቡብ ጎንደር፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በሰሜን ጎጃም፣ በምስራቅ ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃም እና በሰሜን ወሎ ዞኖች ነው።
መከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች “ዘመቻ አንድነት በሚል ስያሜ ትንኮሳ ለመፈጸም የሞከረው ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድን ተደምስሷል” ብሏል።
ጦሩ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ 317 የፋኖ ታጣቂዎች መግደሉን ትላንት አርብ መጋቢት 12 ቀን 2017 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በመግለጫው መሠረት 41 የፋኖ አባላት ሲማረኩ 125 ደግሞ ቆስለዋል።
መትረየስ እና ክላሽን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች፣ የመገናኛ ራዲዮ፣ ተሽከርካሪ እና ሞተር ሳይክል በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መከላከያ ሠራዊት በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል።
አበበ ፋንታሁን የተባሉ የአማራ ፋኖ በወሎ ወይም ቤተ-አማራ ቃል አቃባይ መከላከያ ሠራዊት ሰላሳ ተዋጊዎች እንኳ እንዳልገደለ ለሬውተርስ ተናግረዋል።
ዮሐንስ ንጉሱ የተባሉ የአማራ ፋኖ በጎንደር ቃል አቀባይ በበኩላቸው ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በተደረገ ውጊያ 602 ወታደሮች መገደላቸውን፣ 430 መቁሰላቸውን እና 98 መማረካቸውን ተናግረዋል።
በጉዳዩ ላይ ሬውተርስ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እና የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ አስተያየት ቢጠይቅም ወዲያው ምላሽ እንዳላገኘ አስታውቋል።
የትግራይ ኃይሎች ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ የሆኑት ብርጋዲየር ጄኔራል ምግበይ ኃይለ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የፋኖ ኃይሎች ሞከሩት ላለው “ትንኮሳ” በ“አደራጅነት” ከሷቸዋል።
የአማራ ፋኖ በጎንደር ቃል አቀባይ ዮሐንስ ንጉሱ ግን ክሱን “ሐሰት” ሲሉ ማስተባበላቸውን ሬውተርስ ዘግቧል። ብርጋዲየር ጄኔራል ምግበይ ኃይለ ከፋኖ ታጣቂ ቡድን ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላቸው አቶ ዮሐንስ ንጉሱ ተናግረዋል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል በመከላከያ ሠራዊትም ሆነ በታጣቂ ቡድኑ የቀረቡ የድል አኃዛዊ መረጃዎችን ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ እንዳልቻለ ገልጧል። ዶቼ ቬለም ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በመንግስት እና በታጣቂ ቡድኑ የተገለጡ መረጃዎችን ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ