የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከቆቦ መውጣቱን መንግሥት ገለጸ
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 21 2014
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ከምትገኘው የቆቦ ከተማ ለቆ መውጣቱን የፌድራል መንግሥት ገለጸ። የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 21 ቀን 2014 ባወጣው መግለጫ መከላከያ ሠራዊት ከቆቦ ለቆ ለመውጣት የተገደደው ህወሓት ከጀመረው ጥቃት በኋላ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት "የሰው ኃይል ማዕበልን በመጠቀም የቆቦ ከተማ ከውጭ በብዙ አቅጣጫ እያጠቃ ነው" በማለት ህወሓትን ወንጅሏል። የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት "አሸባሪ" እያለ በመግለጫው የጠቀሰው ህወሓት "የከተማ ውስጥ ውጊያ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል" ብሏል።
"የሕዝብን ከፍተኛ ፍጅት ለማስወገድ ሲባል የመከላከያ ኃይል የቆቦ ከተማን በመልቀቅ" መውጣቱን የገለጸው የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ጦሩ አፈግፍጎ "ለመከላከላከል የሚያስችለውን ወታደራዊ ይዞታዎችን ለመያዝ" እንደተገደደ ገልጿል። ጥቃቱ ካልቆመ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት "ሕጋዊ፣ ሞራላዊ እና ታሪካዊ ግዴታውን ለመወጣት" እንደሚገደድም አትቷል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቆቦን ለቆ መውጣቱ ከመገለጹ በፊት ትግራይን የሚያስተዳድረው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ "ኃይል አሰባስቦ ወደ አማራ እና አፋር ክልል አዋሳኞች እየተንቀሳቀሰ መሆኑን" የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ገልጾ ነበር።
እስካሁን ከህወሓት ባለሥልጣናት በኩል በጉዳዩ ላይ የተባለ ነገር የለም። የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት የሚመራው የትግራይ አስተዳደር "ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም" መወሰናቸውን ካሳወቁ በኋላ ጋብ ብሎ የነበረው ውጊያ እንደገና ያገረሸው ባለፈው ነሐሴ 18 ቀን 2014 ነው።
ቆቦ ከአዲስ አበባ 569 ኪሎ ሜትር የምትርቅ ሲሆን የአማራ እና የትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ የምትገኝ ነች። የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር መቀመጫ የሆነችው የወልድያ ከተማ ከቆቦ በ50 ገደማ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ናት።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ በአማራ ክልል ከሚገኙ ከተሞች በህወሓት ኃይሎች እጅ ሥር ከገቡ መካከል ቆቦ እና ወልድያ ይገኙበታል። የኢትዮጵያ መንግሥት ቆቦ እና ወልድያን ጨምሮ በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙ አካባቢዎችን መልሶ መቆጣጠሩን የገለጸው ታህሳስ 9 ቀን 2014 ነበር።
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ