የኢትዮጵያ ምርጫና ተቃዋሚዎች
ሰኞ፣ ሰኔ 21 2013
አብዛኛዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ መረጠ። ዛሬ ሳምንቱ። ትግራይ፣ ሶማሌ፣ ሐረሪ ክልሎችና በሌሎች በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ዞኖች፣ ወረዳዎችና የምርጫ ክልሎች «በፀጥታና በሎጂስቲክ» ምክንያት ምርጫ አልተደረገም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኞ ድምፅ ከመሰጠቱ በፊት እዳስታወቀዉ ከ37 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ድምፅ ለመስጠት ተመዝግቧል።46 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወዳድረዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኞ የተሰጠዉን ድምፅ የመጀመሪያ ደረጃ አጠቃላይ ዉጤት ግን ገና ይፋ አላደረገም። የቅድመ ምርጫዉ፣ የድምፅ አሰጣጡም ሆነ የድሕረ ምርጫዉ የእስካሁን ሒደት ሠላማዊ ነበር። ይሁንና የምርጫዉ ነፃና ፍትሐዊ ወይም ትክክለኛነት ፖለቲከኞችንና የፖለቲካ ተንታኞችን አሁንም እያነጋገረ ነዉ። አነጋጋሪዉ ርዕስ-ርዕሳችን ነዉ።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በድምፅ አሰጣጡ ሒደት «ተፈጠረ» ያሉትን ስሕተት ወይም ጫና እየጠቀሱ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አቤት እያሉ ነዉ።የሲዳማ አንድነት ፓርቲ ደግሞ ከምርጫዉ ሒደት እራሱን ማግለሉን አስታዉቋል።የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ዛሬ በፌስ ቡክ ገፃቸዉ እንደፃፉት ግን ከፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች ጋር ስለምርጫዉ ሒደትና ስላጋጠሙ ፈተናዎች ተነጋግረዋል።የፓርቲ ተወካዮቹን አመስግነዋልም።
ምርጫዉንም ጠቅላይ ሚንስትሩ «ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና የወጣችበት» ብለዉታል።በምርጫዉ የተካፈሉ፣ ያልተካፈሉትንም በጥቅሉ 53 የፖለቲካ ማሕበራትን የሚያስተናብረዉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሔል ባፌ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ሐሳብ ጋር ይስማማሉ።
መንበሩን ዘ ሔግ ኔዘርላንድስ ያደረገዉ ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲና የምርጫ ድጋፍ ሰጪ ተቋም የሕገ-መንግሥትና የዴሞክራሲ ግንባታ አማካሪ ዶክተር አደም ካሴ ምርጫን ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ወይም ትክክለኛ የሚያስብሉ ጥቅል መስፈርቶችን ይጠቅሳሉ።የሰኞዉን ምርጫ ሰላማዊነትም ይመሰክራሉ።
ምርጫዉ በሰላም መጠናቀቁ ዶክተር ራሔል እንደሚሉት ለሚመሩት ምክር ቤት «ትልቅ ድል» ነዉ።ነፃና ትክክለኛ ወይም ፍትሐዊነቱን ግን ዶክተር ራሔል «ያፈፃፀም ችግር» ብለዉታል።የምርጫዉ ነፃና ፍትሐዊነት ለማጠያየቁ ዶክተር አደም፣ እንደ ዶክተር ራሔል «ያፈፃፀም ችግር» ብለዉ አላለፉትም።ሁለት አብነቶችን ይጠቅሳሉ።
በምርጫዉ የተወዳደሩት 45 ተቃዋሚ የፒለቲካ ፓርቲዎች ገሚሶቹ ብሔራዊ፣ ሌሎቹ ክልላዊ ወይም በብሔር ላይ የተመሰረቱ ከመሆናቸዉ ልዩነት ባለፍ ሁሉም ተቃዋሚ ናቸዉ።45ቱ ፓርቲዎች ልዩነታቸዉን አቻችለዉ በጋራ ከመቆም ይልቅ ተለያይተዉ በመወዳደራቸዉ ገዢዉን ፓርቲ የመፎካከር አቅማቸዉ መዳከሙ ግልፅ ነዉ።ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ ላለመቆማቸዉ ዶክተር ራሔል የኮሮና ወረርሺኝና የምርጫ ሕጉን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
ዶክተር አደም ግን ለድምፅ መከፋፈሉተቃዋሚዎች የምርጫዉን ሕግ አጢነዉ አስቀድመዉ አለመዘጋጀታቸዉን ይጠቅሳሉ።ዶክተር አደም አክለዉ እንዳሉት ትግራይ ዉስጥ ምርጫ አለመደረጉ፣ በኦሮሚያ ክልል የገዢዉ ፓርቲ ብርቱ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለዉ የሚጠበቁ ተቃዋሚዎች አለመወዳደራቸዉ የምርጫዉን የመፎካከሪያ መድረክነት ቀንሶታል።ግን ለተቃዋሚዎች አስተማሪም ነዉ።
ከእንግዲሕስ? ዶክተር ራሔል እንደሚሉት እስከ ጵዋግሜ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሌላ ምርጫ ዝግጅት ጊዜ ነዉ።ከጵዋግሜዉ ምርጫ በኋላ ደግሞ «ዥንጉርጉር» ምክር ቤት እናያለን ይላሉ።
ጵዋግሜ ምርጫ የሚደረግባቸዉ አካባቢዎች ብዙዎቹ የፀጥታ ሥጋት ያጠላባቸዉ ናቸዉ።ዶክተር አደም ይመክራሉ።«ጥንቃቄ» መደረግ አለበት እያሉ።ከመንግስት ምሥረታዉ በኋላ ደግሞ ለትግራይ ቀዉስ፣ ለኦሮሚያዉ የፖለቲካ ቅሬታ ሠላማዊ መፍትሔ መፈለግ አለበት።መንግስት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እግዛ ማድረግ አለበትም-እንደ ሕግ ባለሙያዉ።
ሠላማዊነቱ ብዙ የተነገረለት ምርጫ ለዘገባ ወደ ኢትዮጵያ በተጓዙ ጋዜጠኞች ላይ የግድያ ዛቻ የተሰነዘረበት ፣ቢያንስ የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢ የተገደለበት ነበር።በምርጫ ቦርድ ዕቅድ መሰረት ከትግራይ በስተቀር ባለፈዉ ሰኞ ድምፅ ባልተሰጠባቸዉ አካባቢዎች በመጪዉ ጵዋግሜ መጀመሪያ ምርጫ ይደረጋል።በእነዚሕ አካባቢዎች 547 መቀመጫዎች ካሉት ከኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድ አምስተኛዉ ወይም አንድ መቶ አስር ያክሉን መቀመጫዎች የሚይዙ ፖለቲከኞች ይመረጣሉ።ከዚያ በኋላ ነዉ ዥጉርጉርም ተባለ ቀይጥ ወይም ወጥ ምክር ቤት የሚሰየመዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ