1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሠራተኞች አማካኝ ገቢ ከመኖሪያ ደመወዝ በ2000 ብር ያነሰ ነው

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ሰኔ 26 2016

በኢትዮጵያ አማካኝ ወርሀዊ ደመወዝ 3000 ብር እንደሆነ ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (ILO) ይፋ አድርጓል። ይኸ ለመሠረታዊ ፍላጎቶች ከሚያስፈልገው መኖሪያ ደመወዝ (Living Wage) እጅግ ያነሰ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤቶቿ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ካልደነገጉ የመጨረሻዎቹ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ናት።

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሚገኝ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሠራተኛ
የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ጥናት የውጭ ኩባንያዎች ንብረት ከሆኑ የጨርቃ ጨርቅ ማምረቻዎች 48 በመቶ ሠራተኞች በደመወዝ ማነስ ምክንያት ሥራ መልቀቃቸውን ይፋ አድርጓል። ምስል DW/Tesfalem Waldyes

የኢትዮጵያ ሠራተኞች አማካኝ ገቢ ለመሠረታዊ ፍላጎቶች ከሚያስፈልገው የመኖሪያ ደመወዝ በ2000 ብር ያነሰ ነው

This browser does not support the audio element.

በዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (ILO) ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ አማካኝ ወርሀዊ ደመወዝ 3000 ብር ነው። ይኸ አማካኝ ወርሀዊ የደመወዝ መጠን ግን የሠራተኞችን መሠረታዊ ፍላጎት እንኳ ለመሙላት የሚችል አይደለም።

የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት የደመወዝ ባለሙያ ጊዮም ዴሎርት በ2018 በሠራንው ጥናት በኢትዮጵያ የመኖሪያ ደመወዝ በወር 5,000 ብር ገደማ እንደሆነ ደርሰንበታልሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ይኸ ሠራተኞች መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለመሙላት ከሚያስፈልጋቸው በ2000 ብር ዝቅ ያለ ነው።

የመኖሪያ ደመወዝ (Living Wage) የቤት ኪራይ፣ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የመጓጓዣ፣ የጤና አገልግሎት የመሳሰሉ የሠራተኞች መሠረታዊ ወጪዎች ተሰልተው የሚሰራ የገቢ መጠን ነው። በሚያዝያ 2015 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 33.5 በመቶ ገደማ ደርሶ የነበረ በመሆኑ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚያስፈልገው የገቢ መጠን በዚያው ልክ መጨመሩ አይቀርም። ዓለም አቀፍ አሠራሮችን በመከተል የኢትዮጵያ መንግሥት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ቢወስን እንኳ መሠረታዊ ፍላጎት ለመሙላት ከሚያስፈልገው የመኖሪያ ደመወዝ ጋር የሚስተካከል አይሆንም።

3000 ሺሕ ብር አማካኝ ደመወዝ ነው። የአማካኙ ሁለት ሦስተኛ ሁለት ሺሕ ብር ይሆናልየሚሉት ጊዮም ዴሎርት  ባደጉት ሀገሮች ከሞላ ጎደል ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ተደርጎ የሚደነገገው የአማካኝ ደመወዝ ሁለት ሶስተኛ እንደሆነ ይናገራሉ። የአማካኝ ደመወዝ ሁለት ሦስተኛው ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ቢሆን ከሠራተኞች ቁጥር አኳያ በአንጻራዊነት ጠንካራ ይሆናል። ነገር ግን ለቀጣሪዎች በደመወዝ ክፍያ የተወሰነ ነውየሚሉት ባለሙያው ከመኖሪያ ደመወዝ (Living Wage) አኳያ እጅግ ዝቅተኛ ነው የሚል አቋም አላቸው።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሠራተኞችን ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን እንዲያሻሽል ግፊት የሚያደርጉ ድምጾች በአለፍ አገደም ባለፉት ዓመታት ሲሰሙ ቆይተዋል። የኑሮ ውድነት የሚፈታተነውን ሠራተኛ ለመታደግ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን የሚወስነውን ቦርድ የሚያቋቁም ደንብ እንዲያወጣ ግፊት በማድረግ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ነው። ቦርዱ እንዲቋቋም የሚፈቅደው የአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ የጸደቀው ከአምስት ዓመታት በፊት ነው።  

ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ መንግሥት የደመወዝ ወለል እንዲደነግግ በአለፍ አገደም ግፊት ሲደረግ ቆይቷል። ምስል MICHELE SPATARI/AFP

የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ባልደረባ የሆኑት ጊዮም ዴሎትር ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን መደንገግ እንዳለባት ይስማማሉ። ይሁንና ባለሙያው የኢትዮጵያ መንግሥት ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለመሙላት ከሚያስፈልገው የገቢ መጠን ዕኩል ማድረግ ይችላል የሚል እምነት የላቸውም።

ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን መወሰን ብቻ ሳይሆን በሌሎች መስኮች ለምሳሌ የቢዝነሶችን ምርታማነት መጨመር፤ ተጋላጭ የሆኑ ማኅበረሰቦችን የሚያግዙ የማኅበራዊ ጥበቃ ስልቶች ተግባራዊ ማድረግ የመሳሰሉ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ ሲሉ ጊዮም ዴሎትር ተናግረዋል።

ዝቅተኛ ደመወዝ 2000 ወይም 3000 ብር ቢደረግ ዝቅተኛ ደመወዝ በሚከፈልባቸው እንደ ግብርና ያሉ ዘርፎች ጠቃሚ ቢሆንም ፋይዳው በሌሎች ዘርፎች እጅግ በጣም አነስተኛ ይሆናል የሚል እምነታቸውን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው ሣምንት ለ2017 በተዘጋጀው ረቂቅ በጀት ላይ ከተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ከተነሱ አንዱ ይኸው የደመወዝ ጉዳይ ነበር። የመንግሥት ሠራተኞች ምግብ እና የቤት ኪራይ ወጪዎቻቸውን መሸፈን እንደተቸገሩ የገለጹት ከፌድራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የተወከሉት አቶ ደጀኔ ደቦጭ የ2017 በጀት መፍትሔ ያበጅ እንደሁ ጠይቀው ነበር።

ከፌድራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ተወክለው በውይይቱ የታደሙት  አቶ ደጀኔ ደቦጭ የበታች ሆኖ እየኖረ ያለው [ሠራተኛ] ቤት ኪራይ ተከራይቶ መኖር እየቻለ አይደለም፤ ተመግቦ እየኖረ አይደለምሲሉ ተደምጠዋል። አቶ ደጀኔ መነሻ የደመወዝ ወለል ካልተሻሻለ ሠራተኛ ባለህበት ሒድ ነው የሚሆነውሲሉ ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወጪውን ለመሸፈን ነባር የገቢ መሰብሰቢያ ግብሮችን ሲያሻሻሽል እና እንደ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ እና የንብረት ግብር የመሳሰሉትን ሥራ ላይ ሲያውል ጫናው ዝቅተኛ ደመወዝ በሚከፈለው ሠራተኛ ላይ ይበረታል የሚለው በውይይቱ የተነሳ ሌላ ሥጋት ነው።

አቶ አሕመድ ሽዴን ጨምሮ የገንዘብ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ደመወዝን የተመለከተ ጥያቄ ሲቀርብላቸው በተደጋጋሚ “እያጠናን ነው” የሚል ምላሽ ይሰጣሉ። ምስል Eshete Bekele/DW

ከፍትኅ ሚኒስቴር ተወክለው በውይይቱ የተሳተፉት አቶ የኋላሸት አግዝ ደመወዝ አገሪቱ ባላቅ አቅም፣ አሁን ባለው ምጣኔ ባይቻል እንኳ ከታች ያሉት እርከኖችን፣ ከታች ያሉትን የደረጃ ዕድገቶች ለምን አይስተካከሉም ሲሉ ጠይቀዋል። የደረጃ ዕድገት ለምን አይሰጥም? የእርከን እድገት ለምን አይሰጥም? የሚል ጥያቄ ሲቀርብ ሲቪል ሰርቪስ የበጀት ጉዳይን እንደሚያነሳ የገለጹት የኋላሸት አማራጭ መፍትሔዎችን እየወሰድን ቢያንስ ትንንሾቹን ክፍተቶች መፍታት የለብንም ወይ?ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ በተሳተፉበት ውይይት ላይ ጠይቀዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኚ ሰኔ 25 ቀን 2016 በተካሔደ በተካሔደ ሌላ ውይይት ተመሳሳይ የደመወዝ ጥያቄ የቀረበላቸው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይየሆነው ሠራተኛ ኑሮ እንደከፋበት አምነዋል። የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተለያዩ አማራጮች እያጠና ይገኛልያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ ይኸ ጥናት በሚያልቅበት ጊዜ በሪፎርም ማዕቀፍ የሚታይ እና ወደፊት ውሳኔ የሚያገኝ ነውየሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት እየተደረገበት የሚገኘው የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ የሜሪት እና የደመወዝ ቦርድን ያቋቁማል። ቦርዱን በሰብሳቢነት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰብሳቢነታቸው ባሻገር ምክትል ሰብሳቢውን ጭምር የመሾም ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። ቦርዱ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር፣ የገንዘብ ሚኒስትር፣ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እና የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነርን ጨምሮ ከስምንት በላይ አባላት ይኖሩታል።

በረቂቅ አዋጁ “የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ስኬል ማስተካከያ፣ የደመወዝ ጭማሪ፣ የክፍያ እና ጥቅማ ጥቅም እና ማትጊያ ወይም ማበረታቻ ጥናትን ተመልክቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረብ ያለበትን የኮሚሽኑን ውሳኔ ሀሳብ” የማረጋገጥ ኃላፊነት ለዚህ ቦርድ የተሰጠ ነው።

በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ቢደነገግ እንኳ እየተከታተሉ በየጊዜው የሚያስተካክሉ ተቋማት ያስፈልጋሉ። ምስል Jeroen van Loon

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን “የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ የመንግስትን የፋይናንስ አቅም፣ የህዝቡን አጠቃላይ የኑሮ ሁኔታ፣ የዋጋ ደረጃዎች፣ ግሽበት እና አግባብነት ያላቸውን ሌሎች ሁኔታዎች ባገናዘበ መንገድ በየጊዜው እያጠና” ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ የማስወሰን ኃላፊነት አለበት።

“የሥራ ደረጃ መነሻ ዝቅተኛ ደመወዝ እና ከፍተኛ ደመወዝ ጣሪያ በየአራት አመቱ አጥንቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ” የማስወሰን እና አፈጻጸሙን የመቆጣጠር ሥልጣን በአሁኑ ወቅት መኩሪያ ኃይሌ ለሚመሩት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ተሰጥቷል።

ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤቶቿ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ እና ደቡብ ሱዳን ዝቅተኛ የደመወዝ መጠንን ካልደነገጉ የመጨረሻዎቹ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ናት። ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በሕግ ዝቅተኛውን የደመመወዝ መጠን በሕግ ደንግገዋል፤ አሊያም ሠራተኞች ከቀጣሪዎቻቸው ተደራድረው መብታቸውን የሚያስከብሩበት ሥልት አበጅተዋል።

ጊዮም ዴሎትር በ2021 በኢትዮጵያ ደመወዝ የሚከፈላቸው ከአጠቃላይ ሠራተኞች 30 በመቶ ብቻ ናቸው። ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በራሳቸው ሥራ የተሰማሩ ወይም በቤተሰቦቻቸው የተቀጠሩ ደመወዝ የማይከፈላቸው ናቸውሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

ዝቅተኛ ደመወዝ ለመወሰን አሁን ትክክለኛው ጊዜ ነው። ምክንያቱም የሀገሪቱ ኢንዱስትሪ እያደገ ነው፤ የደመወዝ ክፍያም እየጨመረ ነውየሚሉት የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ባልደረባ ዝቅተኛ ደመወዝን መወሰን ከአሁን ይልቅ ከአምስት ዓመታት በኋላ በእርግጠኝነት የበጠለ ከባድ ይሆናል ሲሉ ይሞግታሉ።

ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ካልደነገገች የአውሮፓ ኩባንያዎች ኅብረቱ ባወጣው ሕግ ምክንያት አማራጭ ሊፈልጉ ይችላሉምስል Jeroen van Loon

ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል አለመደንገግ በሠራተኞች ሕይወት ላይ ካስከተለው ብርቱ ጫና ባሻገር የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የሚፈታተን ጣጣ አስከትሏል። በዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ጥናት መሠረት የውጭ ኩባንያዎች ንብረት የሆኑ የጨርቃ ጨርቃ ማምረቻ ፋብሪካዎች ሠራተኞች 48 በመቶው በዝቅተኛ ክፍያ ምክንያት ሥራቸውን ለቀዋል።

የሠራተኞችን ምርታማነት እና የሥራ አፈጻጸም ለማሳደግ፣ በገበያው ከሚገኙ ሌሎች ተዋናዮች ለመወዳደርካስፈለገ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መደንገግ እንደሚኖርባት የገለጹት ጊዮም ኢትዮጵያ በጨርቃ ጨርቅ አምራችነት ቪየትናም እና ካምቦዲያን ከመሳሰሉ ሀገሮች ለመፎካከል ካሻት ጥሩ ደመወዝ መክፈል እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።

ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው ቆይተው አዳዲስ ክህሎቶች እንዲማሩ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ግን ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን መወሰን ብቻውን በቂ አይደለም። የክፍያው መጠን በየወቅቱ መስተካከል ይኖርበታል። ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል በአመት አንድ ጊዜ ቢስተካከል ጥሩ ነው። የዋጋ ግሽበትን መሠረት በማረግም ማስተካከል ይቻላልሲሉ ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ስንት መሆን እንዳለበት በሕግ ካልደነገገ በኢትዮጵያ የሚገኙ የውጭ ኩባንያዎች በተለይ አውሮፓውያን አማራጭ ለመፈለግ ሊገደዱ ይችላሉ። የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የሚሰሩ ኩባንያዎች የሰብአዊ መብቶች እና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮችን በቅጡ እንዲያጤኑ የሚያስገድድ ሕግ ከሁለት ወራት በፊት አጽድቋል።

ሕጉ ሥራ ላይ የሚውለው በመጪዎቹ ዓመታት ቢሆንም ኩባንያዎቹ የግዢ ሥርዓታቸውን ከመኖሪያ ደመወዝ እና ገቢ ጋር እንዲያጣጥሙ የሚያስገድድ ነው። የአውሮፓ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ሲያደርጉ፤ ወይም ከኢትዮጵያ ሲሸምቱ በሕጉ የተቀመጠውብ ቅድመ-ሁኔታ ለማሟላታቸው እርግጠኛ ካልሆኑ ወደ ሌላ ሀገር ይሔዳሉሲሉ ጊዮም ዴሎትር ያሳስባሉ።

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW