የኢትዮጵያ ሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫ እና የዶቸ ቬለ ጋዜጠኛ የጉዞ ላይ ትዝብት
ቅዳሜ፣ ግንቦት 22 2018
ከአዲስ አበባ የተነሳው የዶቸ ቬለ ጋዜጠኛ ታምራት ዲንሳ በኦሮሚያ ክልል በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን እንዲሁም ወሊሶ እና ወልቂጤን በመሳሰሉ ከተሞች ያለውን የምርጫ ድባብ ታዝቧል። በጉዞው የምርጫ ጣቢያዎችን እንቅስቃሴ ከመመልከት ባሻገር አርሶ አደሮችን እና አሽከርካሪዎችን አነጋግሯል።
በማሳቸው በሬ ጠምደው እርሻ ሲያርሱ ያገኛቸው ገበሬዎች በሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ድምጽ ለመስጠት መመዝገባቸውን ተናግረዋል። ይሁንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ ያላቸው እውቀት አናሳ እንደሆነ መታዘቡን አስረድቷል።
“ከአዲስ አበባ ተነስቼ ወልቂጤ እስክደርስ ድረስ መንገዱ ምንም ችግር አልነበረበትም። የተሽከርካሪ ፍሰትም እንደ ተለመደው ነው” በማለት የታዘበውን በጉዞ ላይ ሳለ በስልክ ባደረገው ቃለ-መጠይቅ ገልጿል። በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የቱሉ ቦሎ ከተማ እና የወሊሶ ከተሞች አካባቢዎች ወታደራዊ መለዮ የለበሱ የጸጥታ አስከባሪዎች በተሽከርካሪዎች ወዲያ ወዲህ ሲንቀሳቀሱ ተመልክቷል።
የምርጫውን ድባብ በተመለከተ ግን የተለየ ድባብ የተመለከተው በወልቂጤ ከተማ ነው። በሌሎች ከተሞች የተለየ ነገር እንዳልተመለከተ የገለጸው ታምራት በወልቂጤ ግን መንገዶች አሸብርቀው እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማዎች ተሰቅለው አይቷል።
ታምራት ዲንሳ ሰባተኛውን የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ለመዘገብ ወደ ኢትዮጵያ ከተጓዙ የዶይቸ ቬለ ባልደረቦች አንዱ ነው። ዶይቸ ቬለ ምርጫ በሚካሔድባቸው የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሚቀጥሉት ቀናት ተከታታይ ዘገባዎች ያቀርባል። ከታምራት ዲንሳ ጋር የተደረገውን ቃለ-መጠይቅ የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።
እሸቴ በቀለ