1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ይዞታ የጥናት ውጤት

ዓርብ፣ ነሐሴ 20 2014

ኢትዮጵያ ውስጥ በሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ግለሰቦች እና ድርጅቶች ላይ በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት እና ግለሰቦች የሰብአዊ መብቶችን የማስጠበቅ ሥራቸውን ስላከናወኑ ብቻ ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው ነው ተባለ።

Präsentation Ethiopian Human Rights Defenders (EHRDC)
ምስል Solomon Muchie/DW

ተሟጋቾች ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው ነው

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ውስጥ በሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ግለሰቦች እና ድርጅቶች ላይ በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት እና ግለሰቦች የሰብአዊ መብቶችን የማስጠበቅ ሥራቸውን ስላከናወኑ ብቻ ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው ነው ተባለ። በሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ላይ የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶች ሁሉም በሚባል ደረጃ ትክክለኛ እና ተገቢ ምርመራ ተደርጎባቸው እንደማያውቅም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል በጉዳዩ ዙሪያ ከ2010 ዓ.ም ጀሞሮ ያደረገውን የዳሰሳ ጥናት ውጤት ትናንት ይፋ ሲያደርግ ተናግራል። 

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በሥራቸው ምክንያት ግድያ፣ ድብደባ፣ የዘፈቀደ እሥራት፣ የግድያ ዛቻ እና ማስፈራራት እንዲሁም ስም የማጥፋት ዘመቻዎች እየተከፈቱባቸው የመንቀሳቀስ፣ ሀሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀትና የመሰብሰብ መብቶቻቸው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እየተገደቡባቸው ነው ተብሏል። 

ከተመሠረተ አንድ ዓመት ከመንፈቅ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ያደረገው የዳሰሳ ጥናት በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት «የሚያስደንቁ የሕግ ማሻሻያዎች ቢደረጉም ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የተሟጋችነትን ሥራ ወንጀል አድርገው የሚያስቀምጡ ሕጎች ወጥተዋል» ይላል። ሕጎቹ በተሟጋቾች ላይ ፍርሃትን በማስረጽ ገደብ ስለመጣላቸውም ይጠቅሳል። 
የተቋሙ ዋና ሥራ አሥኪያጅ አቶ ያሬድ ኃይለማርያም በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት የተስተዋለው የመብት ጥሰት ዓይነትና ደረጃ «እጅግ አስከፊ የሚባል ነው» ብለዋል።

ምስል Solomon Muchie/DW

በሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ከባድና መጠነ ሰፊ ጥቃቶች መድረሳቸው የጉዳቱ ሰለባዎችን ምስክርነት ያካተተው የጥናቱ ውጤት «እነዚህን የመብት ተቆርቋሪዎች ዒላማ ያደረጉ ግድያዎች፣ ድብደባዎች፣ የዘፈቀደ እሥራቶች እና የስም ማጥፋት ወንጀሎች ተፈጽሞባቸዋል» ሲል ይዘረዝራል። ይህም በመሆኑ ያመንቀሳቀስ ፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቶቻቸውን ከመነፈጋቸው ባለፋ በሀሰት ክሶችና ውንጀላዎች የኢ- ፍትሓዊ ፍርድ ተጠቂዎች መሆናቸው ተዘርዝሯል።

ጥናቱን ያቀረቡት በማዕከሉ ከፍተኛ የመብት ተሟጋች ሆነው የሚሠሩት አቶ በፍቃዱ ድሪባ ስለ ግኝቱ ለ ዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ «የተወሰኑ መሻሻሎች ማለትም የሕግ እና የተቋም ማሻሻያዎች ቢኖሩም ሥርዓቱ ወደ ኋላ እንዲመለስ የሚያደርጉ የአፈፃፀም ችግሮች አሉ» ብለዋል።

የጥናቱ ግኝት በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ግለሰቦች እና ድርጅቶች እነማን ናቸው የሚለውን መለየት አስቸጋሪ ነው ሲል ይዳስሳል። ለዚህም እንደ ችግር ሆነው የቀረቡት የሰብዓዊ መብት አንቂነት ከፖለቲካ አንቂነት እና ከማኅበራዊ ገዳይ አቀንቃኝነት ጋር መቀላቀሉ አንድ፣ እየሰፉ የመጡ ያላቸው ግጭቶች የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ሀገርን ከመፍረስ ማዳን ቀጥሎ የሚመጣ ጉዳይ ነው የሚል አስተሳሰብ መፈጠሩ እና ይህም ለመብት ተሟጋቾች አስቸጋሪ መሆኑ የሰብዓዊ መብት እሴቶች ወደ ጎን የተተውበት ጊዜ መሆኑ ሁለት፣ እና ብሔርን መሠረት ያደረገው የፖለቲካ ትርክት የሀገሪቱን ፖለቲካ እና ለሰብዓዊ መብቶች ያለን አረዳድ ማዛባቱ ሦስት፣ በምክንያትነት ቀርበዋል። አቶ ያሬድ ይህ በሂደት ይታረማል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በጥናት ግኝቱ ወቅት ከተሳተፉ ሰዎች መካከል አንደኛው ለጥፋቶች ሁሉ «የተጠያቂነት አለመኖር ጥሰቶችን ማባባሱን» ተናግረዋል። በዳሰሳ ጥናቱ መንግሥት ያሉበትን የሰብዓዊ ምብቶችን የመጠበቅ እና የማስጠበቅ ኃላፊነቶቹን በአግባቡ እንዲወጣ፣ የሰብዓዊ ማብቶች ታሟጋቾች ደግሞ ሥራዎቻቸውን በገለልተኝነት እና ግልፅነት እንዲያከናውኑ ተጠይቋል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW