1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ እገታ ወንጀል የኢሰመኮ ዝርዝር መግለጫ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 28 2016

ወንጀሉ በአብዛኛው እንደ ገቢ ማስገኛ የተወሰደ መሆኑን የሚጠቅሰው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ድርጊቱ "በተደጋጋሚ፣ በተንሰራፋና በተደራጀ መልኩ እንደሚፈጸም፤ አልፎ አልፎም እንደ በቀል፣ ለፖለቲካ ዓላማ ወይም የታገተ ሌላ ሰውን ለማስለቀቅ በሚል በአጸፋ መልኩ የሚፈጸም መሆኑን" ስለመረዳቱ አመልክቷል።

ኢሰመኮ መንግሥት ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት ውጤታማ ያላቸውን እርምጃዎችን እንዲወስድ ጠይቋል።
ኢሰመኮ መንግሥት ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት ውጤታማ ያላቸውን እርምጃዎችን እንዲወስድ ጠይቋል።ምስል Ethiopian Human Rights Commission

አስፈሪ ሁኔታ የፈጠረው የሰዎች እገታ ወንጀል

This browser does not support the audio element.

መንግሥት በተስፋፋ ሁኔታ የሚፈጸም የሰዎች እገታን ሊያስቆምና ተጠያቂነትንም ሊያረጋግጥ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ ነሐሴ 28 ቀን ባወጣው መግለጫ ጠየቀ። ኮሚሽኑ "የሰላም መደፍረስ እና የትጥቅ ግጭት" ለሰዎች እገታ መነሻና አባባሽ ምክንያት መሆኑን አስታውቋል።
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች "የተፈጠረ የሕግ ማስከበር እና የመንግሥት መዋቅር መላላት" ችግሩ ጎልቶ እንዲታይ ማድረጉን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ኢሰመኮ በኢትዮጵያ አሳሳቢ ሆኖ የቀጠለውን ይህንን የእገታ ድርጊት በዘላቂነት ለማስቆም መነሻ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መፍታትን ጨምሮ መንግሥት ውጤታማ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።

ስለ እገታ ወንጀል የኢሰመኮ ዝርዝር መግለጫ 
 
በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከተራዘሙ የትጥቅ ግጭቶች ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የሕግ ማስከበር እና የመንግሥት መዋቅር መላላት ሳቢያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ "በታጣቂ ኃይሎች፣ ለዘረፋ በተደራጁ ቡድኖች እንዲሁም በአንዳንድ የመንግሥት የጸጥታ አካላት አባሎች" የሚፈጸሙ እገታዎች ተባብሰውና ተስፋፍተው የቀጠሉ መሆኑን ኢሰመኮ በክትትልና ምርመራ ውጤት ማረጋገጡን አስታውቋል።

አጋቾች ሰላማዊ ሰዎችን በአብዛኛው በጉዞ ላይ እያሉ አንዳንዴም ከመኖሪያ ቤታቸው ወይም ከሥራ ቦታቸው አግተው ወዳልታወቀ ቦታ በመውሰድ ከፍተኛ የማስለቀቂያ ገንዘብ ክፍያ ይጠይቃሉ ያለው ኢሰመኮ "ገንዘብ መክፈል ያልቻሉ በርካታ ታጋቾች ግድያን ጨምሮ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተፈጽሞባቸዋል" ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል።

በእነዚህ ክልሎች የተመረጡ የእገታ ወንጀሎችን ለማሳያነት መጥቀሱን የገለፀው ኢሰመኮ "በርካታ ጉዳዮችን በእገታ ሥር ለሚገኙ ተጎጂዎች እንዲሁም ከእገታ ለተለቀቁ ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸው ደኅንነት ሲባል" ይፋ ከማድረግ መቆጠቡንም ገልጿል። በኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ሚዛኔ እባተ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት ኮሚሽኑ ይህ ችግር እንዲቆም በተደጋጋሚ በመግለጫ የጠየቀ ቢሆንም ይልቁንም ተባብሶ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ድርጊቱ "በተደጋጋሚ በተደራጀ መልኩ እንደሚፈጸም፤ አልፎ አልፎም እንደ በቀል፣ ለፖለቲካ ዓላማ ወይም የታገተ ሌላ ሰውን ለማስለቀቅ በሚል በአጸፋ መልኩ የሚፈጸም መሆኑን" ስለመረዳቱ አመልክቷል።ምስል Nataliya_Dx/Pond5 Images/IMAGO

በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው የእገታ ወንጀል ማሳያ

ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ ከተማ አካባቢ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት
ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በመቶዎች የሚቆጠሩ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ማገቱን የገለፀው ኮሚሽኑ "ይህ ሪፖርት ይፋ እስከተደረገበት ዕለት ድረስ ስንት ተማሪዎች በእገታ ሥር እንደሚገኙ እንዲሁም ምን ያህሉ እንደተለቀቁ ለማረጋገጥ አልተቻለም" ብሏል። በዚሁ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ደብረ ሊባኖስ ወረዳ፣ ምሥራቅ ወለጋ ዞን ዲጋ ወረዳ ሌሎች እገታዎች መፈፀማቸውንም በሪፖርቱ ጠቅሷል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ ሜጫ ወረዳ በፋኖ ቡድን አባላት 17 የአካባቢው ነዋሪዎችን ይዘው አንበርክከው እንዲጓዙ እንዳደረጓቸውና የተወሰኑት ስለመገደላቸው፣ በባሕር ዳር ከተማ፣ በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ፣ በምዕራብ ጎንደር ዞን ልዩ ልዩ እገታዎች እና ግድያዎች መፈፀማቸውንም አስታውቋል።

ወንጀሉ በአብዛኛው እንደ ገቢ ማስገኛ የተወሰደ መሆኑን የሚጠቅሰው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ድርጊቱ "በተደጋጋሚ፣ በተንሰራፋና በተደራጀ መልኩ እንደሚፈጸም፤ አልፎ አልፎም እንደ በቀል፣ ለፖለቲካ ዓላማ ወይም የታገተ ሌላ ሰውን ለማስለቀቅ በሚል በአጸፋ መልኩ የሚፈጸም መሆኑን" ስለመረዳቱ አመልክቷል።

መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ ስለመጠየቁ 

መንግሥት ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት ውጤታማ ያላቸውን እርምጃዎችን እንዲወስድ፣ ለወንጀሉ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ፣ የጥበቃና ቁጥጥር ሥራዎችን ከማከናወን በተጨማሪ የታጋቾችን ደኅንነት በጠበቀ መልኩ የማስለቀቅ ሥራዎችን እንዲያጠናክር እንዲሁም ታጣቂ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕጎችን እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች መርሆችንና ድንጋጌዎችን እንዲያከብሩ፣ ከእገታ ድርጊቶችም እንዲታቀቡ ኮሚሽኑ አሳስቧል። መሰል የእገታ ድርጊት በተለይ ጎንደር ከተማ እና አካባቢው እጅግ አሳሳስቢ በሚባል ደረጃ ላይ ስለመድረሱ እየተነገረ ነው።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW