1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ኹኔታ ጦርነት ሳይሆን «የትጥቅ ግጭት» በሚል የሚገለጽ ነው: ኢሰመኮ

ሰለሞን ሙጬ
ዓርብ፣ መስከረም 29 2019

በትግራይና አዋሳኝ የአማራና የአፋር ክልሎች ያለውን ኹኔታ እስካሁን ባለው ደረጃ «የትጥቅ ግጭት» አድርጎ እንደሚመለከተው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገለፀ። ኮሚሽኑ በተለይ በትግራይና አማራ ክልሎች ያለውን ኹኔታ በዓለም አቀፍ ብያኔ «ጦርነት» ሳይሆን «በግጭት ዐውድ ላይ የሚገኙ አካባቢዎች» አድርጎ እንደሚወስዳቸው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አርማ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚኅን ዓመታዊ ዘገባ፤

This browser does not support the audio element.

 

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ እና አዋሳኝ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ያለውን ኹኔታ እስካሁን ባለው ደረጃ «የትጥቅ ግጭት» አድርጎ እንደሚመለከተው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለፀ። ኮሚሽኑ በተለይ በትግራይ እና አማራ ክልሎች ያለውን ኹኔታ በዓለም አቀፍ ብያኔ «ጦርነት» ሳይሆን «በግጭት ዐውድ ላይ የሚገኙ አካባቢዎች» አድርጎ እንደሚወስዳቸው አስታውቋል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ይህንን ያሉት ዛሬ ዓርብ በጽሕፈት ቤታቸው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ኹኔታ ዘገባ ሲያቀርቡ ከዶቼ ቬለ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው። ኤርትራ በሰሜን ኢትዮጵያ ያላት ተሳትፎ ምን እንደሆነ የኮሚሽኑን ምልከታ የተጠየቁት ዋና ኮሚሽነሩ«መረጃ በማሰባሰብ ላይ መሆናቸውን» ጠቅሰው፣ ያም ሆኖ በግጭቶቹ ውስጥ «ንጹሐን ኢላማ ተደርገው» እንደሆን መለየት እንጂ «ማን ከማን ነው» የሚለው ላይ መረጃ ልንሰጥ አንችልም ብለዋል። 


የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያለፈውን አንድ ዓመት ማለትም ከሰኔ 2017 እስከ ሰኔ 2018 ዓ.ም የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብቶች ኹኔታ ዓመታዊ ዘገባ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርጓል። ኢሰመኮ 2018 በሕይወት የመኖር መብት ኹኔታ «አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን የሚያሳዩ በርካታ» ያላቸው «ክስተቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተስተውለዋል፤» ብሏል። 
በአፋርና በአማራ ክልል አጎራባች ወረዳዎች የነበሩ ግጭቶች መቀነስ፣ በጋምቤላ ክልል በተከሰቱ ግጭቶች የተሳተፉ የተባሉ የፖሊስ አባላት ላይ የአስተዳደር እና የወንጀል ተጠያቂነትን ለማስፈን ምርመራ መጃመሩ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታጣቂዎች ከመንግሥት ጋር እርቅ መፈፀማቸው በአዎንታ የሚጠቀሱ ለውጦች ናቸው ብሏል። 


ኮሚሽኑ አደረግኹት ባለው የውትወታ ሥራ በከባድ ወንጀሎች ተከሰው ፍርድ ቤት ውሳኔ የሰጠባቸው ሰዎች እና በክስ ሂደት ላይ እያሉ በቅድመ ኹኔታ በይቅርታ የወጡ ሰዎች መኖር ሌላው ተጠቃሽ ሥራ መሆኑን አመልክቷል። በዚህም መንገድ እስካሁን 729 ሰዎች ከእሥር እንዲለቀቁ መደረጉም ተጠቅሷል። 
ኮሚሽኑ በትግራይ እና በአማራ እንዲሁም በትግራይ እና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ችግሮች «የትጥቅ ግጭቶ» በሚል የሚፈረጁ መሆኑን ገልፆ  የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን የሚያስከትሉ በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሔ እንሰጥባቸው በቅርቡ መግለፁ ይታወሳል። ዶቼ ቬለ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ብያኔ አንፃር በእነዚህ ክልሎች ወይም በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ኹኔታ አሁንም «የትጥቅ ግጭት ወይስ ጦርነት» ሊባል የሚችለው በሚል ጥያቄ ያቀረበላቸው ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ኮሚሽኑ«በግጭት ዐውድ ላይ የሚገኙ አካባቢዎች» አድርጎ እንደሚወስደው መልሰዋል። የኤርትራ ተሳትፎ ምን እንደሆነም ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ መረጃ በማሰባሰብ ላይ መሆናቸውን ከመግለፅ የዘለለ ዝርዝር ነገር አልጠቀሱም።  

ብርሃኑ አዴሎ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Seyoum Getu/DW


ኮሚሽኑ ባደረገው ምርመራ በሌሎች ክልሎችም በታጣቂዎች፣ በተደራጁ ቡድኖች እና ማንነታቸው በውል ባልታወቁ አካላት በተፈፀመ ጥቃት በንጹሐን ላይ የሕይወት መጥፋት ወንጀል ደርሷል። በተጨማሪም ታጣቂ ቡድንን ትደግፋላችሁ የሚል ሕገ ወጥ እሥር በታጣቂዎችም ሆነ በመንግሥት የፀጥታ ኃይላት መፈፀሙን፣ እገታ መቀጠሉን፣ እንቅስቃሴ ገደብ አሳሳቢ ሆኖ በመቀጠሉ ምክንያት የመንቀሳቀስ መብት ላይ የሚደርሰው ጉዳት እንደቀጠለ አብራርተዋል። 
ኮሚሽኑ በሰሜን ኢትዮጵያ አለ ባለው የግጭት ዐውድ የሲቪል ዜጎች ጉዳትን በሚመለከት መረጃ እየሰበሰበ ይገኛል። በትግራይ ክልል የተባባሰ ኹኔታ እንዳለ የጠቀሱት ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፣ በክልሉ ያለው ጽሕፈት ቤቱ ባለፉት ሳምንታት በተፈጠረው የቴሌኮም አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት ተዘግቶ እንደነበርና ይህም በዚህ ሥራቸው ላይ ችግር መፍጠሩን አልሸሸጉም። 


«በግጭቱ ውስጥ ንጹሐን እና የሲቪል ተቋማት ኢላማ ተደርገዋል ወይ?» በሚለው ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚመረምሩም ገልፀዋል። በዓመት የዘፈቀደ እሥር እና የፍርድ ቤት ትዕዛዛትን አለማክበር «በስፋት» መስተዋሉንም ገልፀዋል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ሌላው ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው ጥያቄ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላን በተመለከተ የኮሚሽኑን የምርመራ ግኝት የተመለከተው ነው። እንዲህ ያለው ወንጀል አስቀድሞ እንደተገለፀው በ ትግራይ ክልል በተደጋጋሚ መፈፀሙን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ይሁንና የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመደበኛነት ከሚከተለው የምልመላ ሥርዓት ውጪ ያደረገው የግዳጅ ምልመላ ስለመኖሩ ማረጋገጥ እንዳልቻሉ መልሰዋል። 


ኢሰመኮ በግጭት ዐውድ ውስጥ በቆዩ ወይም በግጭት ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎች፣ በየአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች፣ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች በሰዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ደርሷል፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በተራዘሙየትጥቅ ግጭቶች ሳቢያ ደግሞ የሕይወት መጥፋት ተመዝግቧል ሲል በተለይ በሕይወት የመኖርና የአካል ደኅንነት መብትን በሚመለከተው የምርመራ ግኝቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልሎች ተፈፀመ ያለውን ዝርዝር ግድያ እና ሞትን የሚመለከት የምርመራ ውጤት በቀን፣ በቦታ፣ ማን እንደፈፀመው፣ ኹኔታው ጭምር በሚያሳይ መልኩ ሰንዷል። 
ሰሜን ኢትዮጵያ የቀጠለውን ግጭት ተከትሎ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ 36 የሰብአዊ መብት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ግጭት በሚያደርሰው የመብት ጥሠት ጥልቅ ምርመራ እንዲደረግ አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ እንዲጠራ ሰሞኑን ጠይቀዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW