የኢሰመጉ አስቸኳይ ዉይይት ይጀመር ጥያቄ እና የረሀብ አድማ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት
ቅዳሜ፣ መስከረም 3 2018
የትጥቅ ግጭቶች በሰላምና በውይይት እንዲፈቱ "ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ግልፅ የሰላም ውይይት በአስቸኳይ እንዲጀመር" ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ጥሪ አደረገ።የመብት ድርጅቱ ዜጎች ከቦታ ቦታ "ያለምንም ሥጋት የሚንቀሳቀሱብት፣ በተለያዩ አካባቢዎች በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች የሚፈጸመው ግድያና ማፈናቀሎች" እንዲቆሙም ጠይቋል። በሌላ በኩል ኢሕአፓ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት "በረሃብ አድማ ላይ የሚገኙ" ያላቸው "የፖለቲካና የኅሊና እስረኞችን" ሕይወት የመታደግ ያለውን አስቸኳይ ሰብዓዊ ጥሪ አድርጓል።በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከሚገኙ እሥረኞች መካከል በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የታሠረ ሰዎች የርሃብ አድማ ላይ ስለመሆናቸው መረጃ እንዳላቸው ከጠበቆቻቸው መካከል አንዱ ዛሬ ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል።//
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ያለፈው 2017 ዓ.ም "ከባድና የተስፋፉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች" የደረሱበት መሆኑን በጠቀሰበት መግለጫው ቁጥር ባይጠቅስም "የበርካታ ሰዎች መገደል፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት"ን በማሳያነት ጠቅሷል።
ኢሰመጉ አዲሱ 2018 ዓ.ም "ሰላም የሰፈነበትና ሰብአዊ መብቶች የሚከበሩበት ዓመት እንዲሆን "በሀገሪቱ ያሉ የትጥቅ ግጭቶች በሰላምና በውይይት እንዲፈቱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ግልፅ የሰላም ውይይት በአስቸኳይ እንዲጀመር" ጠይቋል።ዓመቱ "ዜጎች ከቦታ ቦታ ያለምንም ሥጋት የሚንቀሳቀሱብት፣ በታጣቂ ቡድኖች የሚፈጸሙ ግድያና ማፈናቀሎች የሚቆሙበት፣ በአደረጃጅት እና በመዋቅር ጥያቄዎች ምክንያት የሚፈጸሙ ግድያና ማፈናቀሎች፣ ሕገ-ወጥ እሥሮች ቀርተው" ዘላቂ መፍትሔ የሚበጅበት እና የፍርድ ቤት ውሳኔዎች የሚከበሩበት" እንዲሆን ሁሉም ግዴታውን እንዲወጣም ኢሰመጎ ጥሪ አድርጓል።
በሌላ በኩል በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከሚገኙ እሥረኞች መካከል በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የታሠረ ሰዎች የርሃብ አድማ ላይ ስለመሆናቸው መረጃ እንዳላቸው ከጠበቆቻቸው መካከል አንደኛ ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ዛሬ ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል።"እሥር ቤት ውስጥ የረሃብ አድማ አድርገዋል፣ ወይም ምግብ ስለመብላት አለመብላታቸው ውስጥ ገብቼ ማረጋገጥ ባልችልም የረሃብ አድማ እንዳደረጉ ነው። ይህንን እያደረጉ እንዳለ አስታውቀዋል፣ ለእኛም ለጠበቆች ገለፀዋል።"
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በበኩሉ "ጉልህ የሕግ ጥሰትና የሕጋዊ ሥርዓት ጉድለቶች በታዩበት፣ ኢ-ሰብዓዊ በሆነ አያያዝና ሁኔታ ለዓመታት በቂሊንጦና በሌሎችም እሥር ቤቶች ሲማቅቁ የቆዩ" ያላቸው "የፖለቲካና የኅሊና እሥረኞች ከጷግሜ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በረሃብ አድማ ላይ መሆናቸውን የፓርቲው ፕሬዝዳንት አብርሃም ሃይማኖት ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።"የሚመለከተውም የመንግሥት አካልም አላናገራቸውም፣ እኛ ቦታው ላይ በመሄድ ነው ይህንን የረሃብ አድማ መጀመራቸውን ከራሳቸው ነው ያረጋገጥነው።"
ኢሕአፓ ባወጣው መግለጫ እሥረኞቹ "ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእሥር እንዲፈቱ ግፊት እንዲደረግ ጠይቋል።"ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ አለም አቀፍ አካላትም ከእነዚህ የሕሊና እሥረኜች ጎን ሊቆሙ ይገባል። ስለዚህ ይህ የሰብዓዊ ጉዳይ ስለሆነ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ግፊት ሊደረግ ይገባል።"
በሽብር እና በሌሎች የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው በቂሊንጦ እሥር ላይ ከሚገኙ ሰዎች መካከል ፖለቲከኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ይገኙበታል።
ሰለሞን ሙጨ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ፀሐይ ጫኔ