የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ የዘንድሮ ዝግጅት
ረቡዕ፣ ሐምሌ 13 2014የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ የዘንድሮ ዝግጅት ኢትዮጵያዊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ደምቆ የታየበት እንደነበር ተገለጸ።
የፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያዩ ዘነበ ለዶይቸ ቨለ እንደተናገሩት፣የፌዴሬሽኑ 39ኛው ዓመት ዝግጅት ኢትዮጵያውያንን ከማቀራረብና አንድነት በመፍጠር በኩል ግቡን ያሳካ ነበር።
ፌዴሬሽኑ፣ኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖችና ለፈራረሱ መሠረተ ልማቶች መልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥልም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ዐቢይ ኑርልኝ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ፣39ኛውን ዓመታዊ ዝግጅት በቅርቡ በሜሪላንድ ኮሌጅ ፓርክ አካሄዷል።
ፌዴሬሽኑ በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን መኻከል መቀራረብና አንድነትን ለመፍጠር ከቆመለት ዓላማ አኳያ ዝግጀቱ የተሳካ እንደነበር የፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያዩ ዘነበ ይናገራሉ።
"ቀንጆ ነበር።ሰው ሁሉ ያለበት ሁኔታ አንድ ላይ መሰባሰቡን ፈልጎታል።እና ይሄ ጥሩ አጋጣሚ ነበረ።ይሄ ትልቅ አጋጣሚ እየፈጠረ ስለሆነ ምንም የሚከስም ነገር አይደለም፤እያደገ እያደገ የመጣ ነገር ነው።ዘንድሮ ያየነው ደግሞ በጣም በጣም ኢትዮጵያዊነት ደምቆ የታየው በወጣቱ ላይ ነው።ወጣቱ በሚገርም ሁኔታ ነው ተሣትፎውን ያየነው።ይህ ትልቅ የሚያበረታታና ጎሽ የሚያሰኝ ነገር ነው፤እናም የምንፈልገውን ግባችንን አሳክተናል እንላለን።"
የፌዴሬሽኑ የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ ከበዓል አዘጋጅ ኮሚቴው ጋር በመረባረብ፣በአጭር ጊዜ የተዋጣለት ፌስቲቫል ለማካሄድ መብቃታቸውን ያወሱት አቶ እያዩ፣ለተጫዋቾች፣ለንግዱ ማኀበረሰብና አጠቃላይ በዝግጅቱ ላይ ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
"ዋናው ተጫዋቾቻችን ናቸው።በአጭር ጊዜ በዚህ በትኬት ውድነት እስከመጨረሻው ጊዜ ድረስ ወደሜሪላንድ መሄዳችን አልተወሰነም ነበር።ወደ ቨርጂኒያ ነበር ቦታ እየተፈለገ የነበረው ትልቅ ምስጋና ለተጨዋቾቹ እና ለቡድን መሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝግጅት አድርገው ቡድናቸውን በማምጣታቸው ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል።የንግድ አጋሮቻችንም በየሄድንበት እየተከተሉ የሚያደምቁልን ዐዳዲስ ነገሮች እያቀረቡ የተሳካ እንዲሆን ትልቅ አስተዋፅዖ ያደርጋሉና ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል።ደጋፊዎቻችንም ፌዴሬሽኑ የእኛ ነው ብለው በየሄድንበት ቦታ ድርጅቱን አቅፈውና ደግፈው መሰባሰቢያ ያደረጉ ድርጅቶች፣ቀድሞ በአንድ ትምህርት ቤት የተማሩ፣ትልልቅ ድርጅቶችም እየመጡ ስብሰባ የሚያደርጉት እዛ ነው።የቤተሰብ ስብሰባ እንኳን በዚያ የሚደረግበት ጊዜ ተፈጥሯል አሁን፤ኳስ ላይ እንገናኝ ነው የሚባለው።"
በዝግጅቱ ላይ ከስፖርት ውድድሩ ጎን ለጎን፣የኢትዮጵያን ባህልና ቅርሳ ቅርሶች፣ባህላዊ ምግቦችና ቅርሳ ቅርሶች የሚያስተዋውቁ በርካታ ዝግጅቶች ቀርበዋል።
የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ፣ባለፉት 39 ዓመታት ኢትዮጵውያንን በማሰባሰብ፣የሀገርን ሁኔታ በመከታተል እንዲሁም ዕርዳታ በሚያስፈልግበት ጊዜ ቀድሞ ሲደርስ መቆየቱ ታውቋል።
አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖችና ለፈራረሱ መሠረተ ልማቶች መልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ዐቢይ ኑርልኝ አመልክተዋል።
"የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ፣ለተጎዱ ቤተሰቦች ለፐራረሱ ትምህርት ቤቶችና መልሰው መገንባት የሚኖርባቸው የትምህርት ተቋማት ቃል በገባነው መሰረት በመጀመሪያው መቶ ሺህ ብር ከዚያ በመቀጠል ደግሞ 250 ሺህ ብር በየዓመቱ እየከፈልን ዕርዳታችንን እንደምንቀጥል ከዚህ ቀደም መግለጫ ላይ አውጥተን ነበር፤አሁንም በድጋሚ በአንተም አድማጮች ስም ለጠቅላላ ደጋፊዎችም ይህንን ማስተላለፍ እንፈልጋለን።"
ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዳስታወቀው፣ዝግጅቱን 65 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ከመላው የአሜሪካ ግዛቶችና ከሌሎች የዓለም ክፍሎች በመገኘት የታደሙበት ነበር።
ታሪኩ ኃይሉ
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሀመድ