የኢትዮጵያ ቡና የውጪ ገቢ እመርታ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 3 2017
በ2017 ዓ.ም. የምርት ዘመን ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ምርት 2.65 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አሳወቀ። እንደ ባለሥልጣኑ ማብራሪያ አምና ከቡና የወጪ ንግድ ከተገኘው 1.4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር አኳያ የዘንድሮ 2017 ዓ.ም. ገቢው በ1.2 ቢሊዮን ዶላር ያህል ብልጫ አለው። እንደ ባለሥልጣኑ ገለጻ ዘንድሮ ከተመረተው ቡና ወደ ውጪ ገቢያ የተላከም 50 በመቶው ግድም ሲሆን፤ ቀሪው 50 በመቶው ለአገር ውስጥ ፍጆታ ውሏል።
«ፍላጎቱ በጣም አለ፤ ከአገር ውጪም ሆነ ከአገር ውስጥ በነበረው ፍላጎት ቡና ዘንድሮ ሽሚያ ነበር» ያሉት የጂማ ዞን ጎማ ወረዳ አጋሮ ዙሪያ የቡና አምራችና ላኪ አርሶ አደር ሙስጠፋ መሃመድ ዘንድሮ ከቡና ያገኙት ገሚ ከየትኛውም ጊዜ የላቀ መሆኑን አስረድተዋል።
ቡናን በማምረት በአከባቢያቸው ከሚገኙ የቡና አምራች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን ቡናን ወደ ውጪ ገቢያ በቀጥታ የሚልኩት ሙስጠፋ «በእጅጉ ተቸበቸበ» ያሉት ቡና ከወዲሁ አዲስ ምርት ሳይደርስ መጋዘኖች ሁሉ ባዶያቸውን ቀርተዋል ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል። «ቡና በደንብ ነበር፤ ደሞም በደንብ ነው የተሸጠው» ያሉት የቡና አምራች አርሶአደሩ አዲሱ ምርት እስኪደርስም መጋዘኖቹ በሙሉ ባዶያቸውን ቀርተዋልም ነው ያሉት። ቡናን በቀጥታ እንደ ጀርመን እና እንግሊዝ ላሉ አገራት እንዲሁም በዋናነት ለፈረንሳዩ ቤልኮ ኩባንያ በደንበኝነት ይዘሰው እንደሚልኩ የገለጹት ሙስጠፋ በደረጃ አንድ የሚያዘጋጁትን ቡና በቀጥታ ለውጪ ገቢያው መላካቸውም እጅጉን ተጠቃሚ አድርጓቸዋል።
እናም ይላሉ የቡና አምራች አርሶአደሩ፤ ከአምና አንጻር ከቡና የተገኘው ገቢ በዶላርም ሆነ በብር ስመነዘር እጅግ የላቀ ነው። «ከአምና አንጻር እጅግ የላቀ ነው» በማለትም የውጪ ምንዛሪው ከኢትዮጵያ ብር አኳያ እጅጉን ጭማሪ ማሳየቱ የወጪ ንግዱን አበረታቷል። «አምና 56 ብር ገደማ የነበረው የአንድ ዶላር ምንዛሪ አሁን ወደ 130 ከፍ ማለቱ ገቢችንን አሳድጓል» የሚሉት አምራቹ ምርቱን ካዘጋጁት ወደ ውጪ ከመላክ የሚገድባቸው አንዳችም ምክንያት እንደሌሌም ነው ያስረዱት።
በ2017 ዓ.ም. የምርት ዘመን ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ምርት 2.65 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን፤ እንደ አገር ከቡና የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ተጨባጭ ውጤት እንዳስገኘ ገልጿል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንደሚሉት በ2017 በጀት ዓመት 326 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት በእቅድ ተይዞ ሲሠራ ቢቆይም፤ በበጀት ዓመቱ 470 ሺህ ቶን የቡና ምርት ወደ ውጭ በመላክ ከ2.6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የላቀ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል። «በ12 ወር በዓመቱ አጠቃላይ 470 ሺህ ቶን ቡና ልከን አጠቃላይ ወደ 2.65 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ አግኝተናል፤ አሁንም የተገኘው ገቢ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ የቡና አምራች እና የቡና ላኪ አገር የሚደርጋት ውጤት ነው የተገኘው» ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ካመረተችው ቡና ከፊሉን በአገር ውስጥ ፍጆታ ተጠቅማ ከፊሉን ብቻ ለዓለም ገቢያ የላከችው ኢትዮጵያ ከዓለምም የሶስተንነት ደረጃ ስለመያዟ ነው የተገለጸው። «ኢትዮጵያ ካመረተችው 50 በመቶውን አገር ውስጥ ተጠቅማ 50 በመቶውን ብቻ በመላክ 2.6 ቢሊየን ዶላር ማግኘት ማለት ከአፍሪካም ባሻገር ከብራዚል እና ቬይትናም በመቀጠል ሦስተኛዋ ቡና አምራች እና ቡና ላኪ አገር ለመሆን ሆናለችም» ያሉት ኃላፊው አቅራቢና ላኪው ተግባብተው ምርት መረካከብ እንዲችሉ በማድረግ የምርት መጠንና ጥራት እንዲጨምር መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ወደ ውጪ ከተላከ ቡና የየተገኘ ገቢ 1.4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ግድም መሆኑ ይታወሳል። እናም የዘንድሮ 2017 ዓ.ም. አፈጻጸም ከአምናው በ1.2 ቢሊዮን ዶላር ያህል ብልጫ ያለው ስለመሆኑም ነው የተገለጸው።
በቡና ውጪ ገቢው ላይ ለመጣው እምርታ የአርሶ አደሮች ቡናን በቀጥታ ለውጭ የሚያቀርቡበት ሥርዓት መመቻቸት የበኩሉን አንተዋጽኦ የተጫወተ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የቡና አቅራቢዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በቡና ዋጋ ላይ ያላቸው የመደራደር አቅም ከፍ ማለቱም ከቡና የሚገኘው ገቢ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም ተብሏልም።
እንደ የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር አዱኛ ገለጻ፤ የቡና ምርት ጥራት ቁጥጥር ተግባራትን በማከናወን ባለፉት ዓመታት በርካታ የቡና ችግኞች መተከሉ ደግሞ ከዘርፉ ወደፊትም ልገኝ የሚችለውን ተስፋ አመርቂ ያደርገዋል። «ባለፉት አምስት ዓመታት ከ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ የቡና ችግኝ ተተክለዋል» በማለትም ከሦስት-አራት ዓመታት በፊት የተተከሉ የቡና ችግኞች ዘንድሮ ወደ ምርት ገብተው ከአምና አንጻር የ200 ሺህ ቶን ብልጫ መገኘቱንም አስረድተዋል። ከተጨማሪ 200 ሺህ ቶን ምርት ውስጥም 170 ሺህው ለውጪ ገቢያ ተልኳል ነው ያሉት።
በዘንድሮ የችግኝ ተከላ መርሃግብር ከሁለት ቢሊዮን በላይ የቡና ችግኞችን ለመትከል ግብ መያዙንም ባለሥልጣኑ አሳውቀዋል። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር በቡና ምርት እና የገቢው አፈጻጸም ላይ ጥብቅ መንግስታዊ ክትትል ስደረግ መቆየቱን መግለጻቸውም ይታወሳል።
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ