1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ማስጠንቀቂያ

ሰኞ፣ መስከረም 13 2017

ፕሬዝዳንቱ ፌዴሬሽኑ የሚጠበቅበትን ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነቱንም መወጣቱን አስታውሰው “ሁሉም ወጪ ግን በኛ ብቻ ሊሸፈን አይገባም” በማለት ለትራንስፖርት ሚኒስቴር አቤት ማለታቸውንም ገልጸዋል፡፡በጭነት ተሸከርካሪዎች አገልግሎት ወደ 200 ሚሊየን ብር በህዝብ ማመላለሻም 100 ሚሊዮን ብር ገደማ አልተከፈለም ብለዋል፡፡

Bildergalerie Äthiopien | Flucht aus der Region Tigray
ምስል Baz Ratner/REUTERS

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ማስጠንቀቂያ

This browser does not support the audio element.

የክፍያው መዘግየት የፈጠረው ቅሬታ

ከሁለት ዓመታት በፊት ባበቃው የሰሜን ኢትዮጵያው የትግራይ ጦርነት ወቅት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር የዱቤ ስምምነት ተፈራርመው አገልግሎቱን ከሰጡት አገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳቢ ተሽከርካሪዎች የሚገኙበት መሆኑን የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኔ ዘሩ በወቅቱ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ሂደቱን አስተባብሮትም ነበር ብለዋል፡፡ አቶ ብርሃኔ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ በስምምነቱ መሠረት ከተከፈለ የተወሰነ ሂሳብ ውጪ ወደ 300 ሚሊየን የሚሆን ያልተከፈለ ክፍያ መኖሩ በአሁኑ ጊዜ አባላቱ ላይ ክፉኛ ቅሬታ ማስነሳቱንም አስገንዝበዋል፡፡የመቀሌውዝርፊያ፤የመንግሥት መግለጫና የህወሓት መልስ

“አደረጃጀታችን በትራንስፖርት ሚኒስቴር ስር እንደመሆኑ በወቅቱ መንግስት የተሽከርካሪዎቹን አገልግሎት ስፈልግ በሚኒስቴሩ አስተባባሪነት ፌዴሬሽኑም ተሳትፎበት ተሽከርካሪዎቹን አቀረብን” የሚሉት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት በተጠየቀው መሰረት ተሽከርካሪዎቹ አገልግሎቱን ከሰጡ በኋላ ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ የተጠራቀመውን ክፍያ መክፈል አስቸጋሪ ሆኗል ብለዋል፡፡ “ለአገር መከላከያ ተቋም ትልቅ ክብር አለን” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ፌዴሬሽኑ የሚጠበቅበትን ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነቱንም መወጣቱን አስታውሰው “ሁሉም ወጪ ግን በኛ ብቻ ሊሸፈን አይገባም” በማለት ጉዳዩን ላስተባበረው ትራንስፖርት ሚኒስቴር በተለያየ መልኩ አቤት ማለታቸውንም ገልጸዋል፡፡በጭነት ተሸከርካሪዎች በተሰጠው አገልግሎት የተወሰነ ያሉት ክፍያ ቢከፈልም፣ ያልተከፈለ ወደ 200 ሚሊየን ብር ሲሆን በህዝብ ማመላለሻም 100 ሚሊየን ገደማ አልተከፈለም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴርምስል Seyoum Getu/DW

የክፍያው መዘግየት ያሳደረው ተጽእኖ

ፌዴሬሽኑ እንዳመለከተው “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለአውቶቡስና የጭነት መኪና ባለቤቶች ባቀረበው ጥያቄ መሠረት አገልግሎቱን ሲያገኝ ቆይቷል፡፡” በብሔራዊ ጥሪ ግዳጅ ከተከናወነ አገልግሎት በተጨማሪ፤ በተገባው ስምምነት ሊከፈል ከሚገባው ክፍያ የተፈጸመው ጥቂት በማለትም እነዚህ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ባለቤቶች የሚያስተዳድሩት ቤተሰቦች ያላቸው እንደመሆኑ፤ አንዳንዶቹ ክፍያውን ባለመቀበላቸው ስራቸውን ለመቀጠል እስከ መፈተን ደረጃ ላይ ይገኛሉም ነው ያለው፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት በዚህ ላይ በሰጡን ማብራሪያም ይህንኑን የክፍያ ጥያቄ በየደረጃው ላሉ አመራሮች ብያቀርቡም ክፍያው አዎንታዊነት ምላሽ አለማግኘታቸው ገልጸዋል፡፡ “በተለይም ታች አመራሮች ጋር በአዎንታዊ አለማስተናገድና ማስፈራሪያ ጭምር ይደርስብናልም” ነው ያሉት።

በትግራዩ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች በትግራይ አቢ አዲምስል Ben Curtis/AP Photo/picture alliance

በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር የመከላከያ ሠራዊት ተሰማራ

ክፍያው ካልተፈጸመ የፌዴሬሽኑ ቀጣይ እቅድ ምንድነው?

በውሉ መሰረት ወደ አገልግሎቱ የገቡት የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከ6 ሺህ በላይ መሆናቸው ተገልጿል። በብዙ ማህበራት የታቀፉ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችም በቁጥር 500 ግድም የሚሆኑ ናቸው ተብሏልም፡፡ ክፍያውን የሚጠባበቀው አባሉ ማህበሩ ላይ ባሳደረው የይከፈለን ጥያቄ መበርታት ፌዴሬሽኑ ከሰሞኑ ጉባኤ ጠርቶ መምክር እንዳስፈለገውም ገልጸው፤ ገንዘቡ በጊዜው አለመከፈሉ ተጽእኖ ማሳደሩንም አስረድተዋል፡፡ የፌፌሬሽኑ ውሳኔም ክፍያው እንዲፈጸም እስከ ክስ መመስረት የሚሄድ ሊሆን እንደምችል አንስተዋል፡፡ “ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማናገር ጨምሮ ሌሎች አማራጮችን እየተመለከትን ነው፡፡ በዚያ ካልሆነ ግን ጉዳዩን ለዓለም የስራ ድርጅት ለማቅረብና ፍርድ ቤትም ለመሄድ እንገደዳለን” ነው ያሉት፡፡

ዶይቼ ቬለ ስራውን በማስተባበር ቅሬታ ለቀረበበት ለትራንስፖርት ሚኒስቴር ጥያቄውን ለማቅረብ ጥሯል፡፡ የሚኒስቴሩ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አመለወርቅ ህዝቅኤል ግን ማብራሪያውን ለመስጠት ዛሬ አመቺ ስፍራ ላይ አለመሆናቸውን በመግለጻቸው አስተያየታቸውን በዚህ ዘገባ ላይ ለማካተት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን በፀጥታ ችግር በሹፌሮች እገታ፣ በክልሎች አለአግባብ በሚጠየቅ ክፍያ፣ በመንገድ መዘጋትና ሌሎችም ችግሮች ከፍተኛ አደጋ እንደተጋረጠበትም በሰሞነኛው ጉባኤው አቤቱታውን አሰምቷል፡፡

ስዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW