የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብድር ወለድ ምጣኔ ማሻሻያ ፊቱን ወደ ገበያ ተመን አዞረ
ረቡዕ፣ የካቲት 26 2017
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “መጠነኛ” ያለው “የብድር ወለድ ምጣኔ ማሻሻያ” አርብ የካቲት 28 ቀን 2017 ሥራ ላይ ይውላል። “አጠቃላይ የቁጠባ ማሰባሰቢያ ወጪ ከፍተኛ” መሆን ባንኩ የብድር ወለድን ከከለሰባቸው ምክንያቶች አንዱ ነው። ንግድ ባንክ “ለሚሰጠው የብድር አገልግሎት የሚያስከፍለው የወለድ ምጣኔ በገበያ ላይ ከሚታየው የወለድ ምጣኔ አንጻር ሲታይ በጣም ዝቅተኛ” መሆኑ ሌላው ገፊ ምክንያት ነው። በዚህ ምክንያት በ“ዘላቂ ትርፋማነት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ” እንደፈጠረ የባንኩ መግለጫ ይጠቁማል።
በማሻሻያ ውስጥ እያለፈ የሚገኘው ተቋም ተግባራዊ የሚያደርገው የወለድ ምጣኔ “ንግድ ባንክ በገበያ ወደ ሚመራ ሥርዓት እየሔደ ለመሆኑ ጠቋሚ እንደሆነ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ይናገራሉ። “ለትሬዠሪ ቢል መንግሥት በአማካኝ 16% በሚከፍልበት፣ ብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ ከባንኮች ሲወስድ 15% በሚከፍልበት ሁኔታ ንግድ ባንክ ዝቅተኛ [የብድር ወለድ] የሚያስከፍልበት አንድም ምክንያት የለም” ሲሉ ዶክተር አብዱልመናን አስረድተዋል።
ምን ተለወጠ?
በማሻሻያው መሠረት ንግድ ባንክ የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ ለግብርና ዘርፍ የሚሰጠው የአጭር ጊዜ ብድር 14 በመቶ ወለድ ይከፈልበታል። በግብርና ዘርፍ ለመካከኛ ጊዜ ብድር የሚያስከፍለው ወለድ ከ15.5 በመቶ ወደ 14.5 በመቶ፤ የረዥም ጊዜ ብድር በአንጻሩ ከ16.5 በመቶ ወደ 15.5 በመቶ ዝቅ ብሏል። የወለድ ምጣኔው የቀነሰው የግብርና ዘርፍን ለማበረታታት እንደሆነ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታውቋል።
ባንኩ ባወጣው መግለጫ መሠረት “የሕብረተሰቡን የመክፈል አቅም ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤቶች ብድር የሚከፈለው የወለድ መጠን ባለበት እንዲቀጥል ተወስኗል።” በ10/90 ፣ 20/80 እና 40/60 መርሐ-ግብሮች ለተሰጠው ብድር የሚከፈለው ወለድ በ12 በመቶ ይቀጥላል። የአጭር ጊዜ የንግድ ብድሮች ላይ የሚከፈለው ወለድ ከ14 በመቶ ወደ 15 በመቶ ከፍ ብሏል። የመካከለኛ ጊዜ ብድሮች ወለድ ከ15.5 በመቶ ወደ 15.75 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። የረዥም ጊዜ ብድር ወለድ ግን በነበረበት 16.5 በመቶ ይቀጥላል።
የ20/80 እና 40/60 የኮንዶሚኒየም የንግድ ቤቶች ብድር ወለድ ከ15.5 በመቶ ወደ 16.5 በመቶ ጨምሯል። የአስመጪዎች ቅድመ-ክፍያ (Advance on Import bills) ብድር የወለድ ተመን ከ17 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ ሲል እና የጅምላ ንግድ ብድር በአንጻሩ ከ15.5 በመቶ ወደ 16.5 በመቶ አድጓል። በንግድ ብድሮች ላይ የጨመረው አንድ በመቶ ገደማ ወለድ በገበያው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል ነው። የባንክ ባለሙያው አቶ ባህሩ ያሲን ግን “በጣም ትልቅ አይደለም” የሚል አቋም አላቸው።
ዓላማው ንግድ ባንክ በብድር መልክ የሚሰጠውን ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያወጣው ወጪ “ጭማሪ እያመጣ ስለሆነ እሱን ለመሸፈን ያለመ ይመስላል” ሲሉ ተናግረዋል። “ንግድ ባንክ በብዛት የሚሰጣቸው ብድሮች ትልልቅ ኮርፖሬት ብድሮች ስለሆኑ በቀጥታ በችርቻሮ ንግድ ላይ ይኸን ያህል ተጽዕኖ ይኖራቸዋል ተብሎ አይወሰድም” ሲሉ የባንክ ባለሙያው አቶ ባህሩ አስረድተዋል።
በንግድ ባንክ የወለድ ምጣኔ ማሻሻያ መሠረታዊ ለውጥ የታየው በውጪ ንግድ ዘርፍ በሚሰጠው ብድር ላይ ነው። በወጪ ንግድ ዘርፍ የአጭር ጊዜ ብድር ወለድ ከ8.5 በመቶ ወደ 12 በመቶ ጨምሯል። የመካከለኛ ጊዜ ብድር 13 በመቶ እንዲሁም የረዥም ጊዜ ብድር 14 በመቶ ወለድ ይከፈልባቸዋል። የቅድመ-ጭነት እና የሸቀጦች ብድሮችም ወደ 12 በመቶ ከፍ እንዲሉ ተደርገዋል።
የንግድ ባንክ ከዚህ ቀደም የሚያገኘውን የውጪ ምንዛሪ ለማሳደግ በወጪ ንግድ ለተሰማሩ ደንበኞቹ ጥቅማ ጥቅም ይሰጥ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ባህሩ ኢትዮጵያ ከሰባት ወራት በፊት መከተል በጀመረችው የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ግን ለውጥ ማምጣቱን አስረድተዋል።
“አሁን የውጪ ምንዛሪ ተወዳድረህ ነው የምትገዛው። የተለየ ጥቅማ ጥቅም ለዚያ ኤክስፖርተር መስጠት አይጠበቅብህም” የሚሉት አቶ ባህሩ በውጪ ንግድ የተሰማሩ ባለወረቶች እና ድርጅቶችም ያገኙትን የውጪ ምንዛሪ የሚሸጡት በገበያ ተመን በመሆኑ “የተለየ ጥቅማ ጥቅም መስጠት አለመስጠት የውጪ ምንዛሪ ግኝት ላይ የነበረው ተጽዕኖ አሁን ጠፍቷል” ሲሉ ተናግረዋል።
ንግድ ባንክ የውጪ ምንዛሪ ለሚያስገኙ ድርጅቶች ተቀጣሪዎች ወይም ትልቅ ዋጋ ላላቸው ደንበኞች (Big Value Customers) ለሚሰጠው ብድር የሚያስከፍለው ወለድ ላይም ለውጥ አድርጓል።
ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ባንኮች መኪና እና የመኖሪያ ቤት የመሳሰሉ ቋሚ ንብረቶችን መግዣ የሚጠይቃቸውን የግል ተበዳሪ ከውጪ ምንዛሪ ግኝት ጋር ግንኙነት ካላቸው ደንበኞቻቸው ዕኩል አያስተናግዱም። “ዝም ብለህ ሔደህ ቤት ግዙልኝ፣ መኪና ግዙልኝ ብትል አይገዙልህም” የሚሉት አቶ ባህሩ “ከፍተኛ ቦታ ላላቸው ደንበኞቻቸው” ቅድሚያ እንደሚሰጡ አስረድተዋል።
የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ከተደረገ በኋላ ንግድ ባንክ የብድር ወለድ ምጣኔውን ሲያሻሽል ግን የቀደመውን አሠራር እርግፍ አድርጎ በመተው ወደ ገበያ ተመን ፊቱን አዙሯል። “ምክንያቱም ማንም ሰው የውጪ ምንዛሪውን ለአንተ አምጥቶ የሚሸጥልህ የለም። በገበያ አደራድሮ ነው የሚሸጥልህ” ይላሉ የባንክ ባለሙያው አቶ ባህሩ።
በዚህም መሠረት ንግድ ባንክ የውጪ ምንዛሪ በቀጥታ ወይም በድርድር ለንግድ ባንክ ለሚያቀርቡ ደንበኞቹ የግል ብድር ሲሰጥ የሚያስከፍለውን 7 በመቶ ወለድ ወደ 11 በመቶ እና 12 በመቶ ከፍ አድርጓል። ለድርድር ዝግጁ ያልሆኑ ድርጅቶች በአንጻሩ ከንግድ ባንክ ሲበደሩ የሚከፍሉት ወለድ ከ7 በመቶ ወደ 13 በመቶ ጨምሯል።
ለመኖሪያ ቤት መግዣ ንግድ ባንክ ለሚሰጠው ብድር የሚከፈለው ወለድ ከአርብ ጀምሮ 14 በመቶ ይሆናል። ባንኩ ለተሽከርካሪ ብድር እና ለግል ብድር 15 በመቶ ወለድ የሚያስከፍል ይሆናል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውሳኔ የተቀዛቀዘው የመኖሪያ ቤት እና የተሽከርካሪ ገበያ ሊያነቃቃ እንደሚችል አቶ ባህሩ ተስፋ አላቸው።
አቶ ባህሩ እንደሚሉት “ለቤት መግዣ ይሰጥ የነበረው ብድር ከውጪ ምንዛሪ ግኝት ጋር በቅድመ-ሁኔታ የታሰረ ነበር።” ባንኩ ለቤት መግዣ (Mortgage) እና ለተሽከርካሪ ብድር ሲሰጥ የሚያስከፍለውን ወለድ ሲከልስ የግል ብድር ለማንኛውም ደንበኛ ፈቅዷል። “የዚህ ብድር መፈቀድ በቤት እና በመኪና ዋጋ ላይ ምንም ጥርጥር የለውም አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ንግድ ባንክ ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለአጭር ጊዜ የሚሰጠው ብድር የሚከፈልበት ወለድ ከ11.5 በመቶ ወደ 14 በመቶ ከፍ ብሏል። የመካከለኛ ጊዜ ብድር 14.5 በመቶ፤ የረዥም ጊዜ ብድር በአንጻሩ 15.5 በመቶ ወለድ ይከፈልባቸዋል።
የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እንደ ማኅበራዊ ልማት ማስፈጸሚያ መሣሪያ ተደርገው እንደሚታዩ የሚናገሩት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ የተደረገው ከፍተኛ የወለድ ምጣኔ ጭማሪ ጥያቄ አጭሮባቸዋል።
የመንግሥት አበዳሪው ለንግድ የተቋቋመ ባንክ ተቃርኖ
የደንበኞቹን ተቀማጭ ሰብስቦ የአጭር እና መካከለኛ ጊዜ ብድር የሚሰጠው ንግድ ባንክ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ገደማ የመንግሥት የፖሊሲ ማስፈጸሚያ ሆኖ ቆይቷል። መንግሥት የኃይል ማመንጫዎች፣ የባቡር መጓጓዣዎች፣ የስኳር እና የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካዎች ለመገንባት ሲያቅድ በገንዘብ ሚኒስቴር ዋስትና ብድር ሲሰጥ የቆየው ንግድ ባንክ ነው።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዕዳቸውን መክፈል ተስኗቸው ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ከተዘዋወረው 847 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከ503 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ከመብራት ጋር ለተያያዙ ፕሮጀክቶች የተሰጠ ነው። የባንኩ ፕሬዝደንት አቤ ሳኖ በቅርቡ እንደተናገሩት ንግድ ባንክ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2021 ድረስ ብድር ይሰጥ የነበረው “8 በመቶ እና ከዚያ በታች ወለድ” እያስከፈለ ነበር። ለግል ተበዳሪዎች ቢሆን ኖሮ ግን 16.5 በመቶ ወለድ ያስከፍል ነበር።
አቤ ሳኖ “የትርፍ ቋት” ብለው ያቆላመጡት ንግድ ባንክ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከውጪ ሀገራት የተበደሩት ዕዳ የመክፈያ ጊዜ ሲደርስ ሌላ ብድር የሚሰጥ ተቋም ነበር። ባንኩ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2020 ከሰጠው ብድር ውስጥ መንግሥት 92 በመቶውን ሲወስድ የግሉ ዘርፍ በአንጻሩ 8 በመቶ ብቻ ድርሻ ነበረው። ለመንግሥት በሰጣቸው ብድሮች ከውድቀት አፋፍ የተመለሰው ባንክ በ2016 ከሰጠው አጠቃላይ ብድር ውስጥ 95 በመቶ ለግል የተሰጠ እንደሆነ ፕሬዝደንቱ አቶ አቤ ሳኖ ገልጸዋል።
ንግድ ባንክ ባለፉት ዓመታት ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሲሰጥ የቆየው ርካሽ ብድር የሚያስከትለው ተጽዕኖ ግን በባንኩ ላይ ብቻ የተገደበ አልነበረም። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን ጉዳዩ ለተቆጣጣሪው ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ “እንቅፋት” እንደሚሆን ይናገራሉ።
“ንግድ ባንክ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሰጠው ብድር ላይ [ወለድ] መጨመር ስለማይችል” ተቆጣጣሪው ብሔራዊ ባንክ ወለድ ለመጨመር ቢፈልግ “አጠቃላይ የወለድ አወቃቀሩን” እንደሚያናጋ ዶክተር አብዱልመናን ይናገራሉ። “በገበያ የሚተመን ወለድ ባለበት ሁኔታ ግን ለገንዘብ ፖሊሲውም በጣም ቀላል ነው የሚሆነው። ስለዚህ ንግድ ባንክ በገበያ ወደሚመራ ሥርዓት እየሔደ መሆኑ በደንብ ጠቋሚ ነው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ምን አልባት ከዚህም የበለጠ እየታየ ሊጨምር ይችላል” ሲሉ አስረድተዋል።
የንግድ ባንክ እርምጃ የግል ባንኮችን ይጫናል?
የውጪ ተወዳዳሪዎችን በሚጠብቀው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያ ንግድ ባንክ በአጠቃላይ ሐብት እና በተቀማጭ 47 በመቶ ገደማ ድርሻ አለው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሥራ ላይ ከሚገኙ 32 ባንኮች “ግዙፍ” ብሎ የመደበው ብቸኛ ተቋም ጭምር ነው።
ባንኩ በገበያው ካለው ድርሻ አኳያ የሚያበድርበትን የወለድ ምጣኔ ቢከልስም በገበያው ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖረው አቶ ባህሩ ይናገራሉ።“አሁንም የንግድ ባንክ የማበደሪያ የወለድ ምጣኔ ዝቅተኛ ነው። ስለዚህ [ለግል ባንኮች የማበደሪያ የወለድ ምጣኔያቸውን እንዲያሳድጉ] ገፊ ምክንያት አይሆንም” ሲሉ አስረድተዋል። የግል ባንኮች ለደንበኞቻቸው ሲያበድሩ የሚያስከፍሉትን ወለድ ከልሰው በአሁኑ ወቅት በአማካኝ 20 በመቶ አድርሰዋል።
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ