1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ አሜሪካ የሲቪል ድርጅቶች ጥምረት ጥሪ

ረቡዕ፣ ግንቦት 14 2016

ዩናይትድስቴትስ ኢትዮጵያን በተመለከተ ጦርነት እንዲቆም፣ ማዕቀቦችና ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ላይ ያተኮረ ስትራቴጂ እንድትከተል የኢትዮጵያ አሜሪካ የሲቪል ድርጅቶች ጥምረት ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ አሜሪካ የሲቪል ድርጅቶች ምክር ቤት አርማ
የኢትዮጵያ አሜሪካ የሲቪል ድርጅቶች ምክር ቤት አርማምስል Ethiopian American Civic Council

የኢትዮጵያ አሜሪካ የሲቪል ድርጅቶች ጥምረት ጥሪ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ አሜሪካ የሲቪል ድርጅቶች ጥምረት ለአምባሳደር ማሲንጋ በጻፈው ደብዳቤ፣ በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በትክክል ጠቅለል አድርገው አስቀምጠዋል በማለት አመስግኗቸዋል። የሰፈነው ፍርሃት ጥምረቱ፣ ጠንካራና ልብ የሚነካ ባለው ደብዳቤ አምባሳደሩ «በሚያሳዝን ሁኔታ ኢትዮጵያንን ጨምሮ በመላው ዓለም ያሉ ብዙ ሰዎች ከ87 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያውያን ይደርስባቸው በነበረባቸው ፍርሃታቸው ቀጥለዋል።» ማለታቸውንም ጠቅሷል። እንዲሁም፣ «ሸፍቶች፣ ታጣቂ ቡድኖችና የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች፣ የመኖር የክብርና የመከባበር መብቶችን በመጣስ ለፍትህ ሂደት እና የሕግ የበላይነት ደንታ ቢስ መሆናቸውን ያሳያል።» ማለታቸውን አመልክቷል።

በሌሎች የአሜሪካ ባለሥልጣናት ያልተሞከረ ንግግር

የጥምረቱ ሊቀመንበር አቶ መስፍን መኮንን፣ ይህ የአምባሳደሩን ንግግርከዚህ በፊት በሌሎች የአሜሪካ ባለሥልጣናት ያልተሞከረ መሆኑን ይናገራሉ። «ከዚህ በፊት ማንም የዩናይትድስቴትስ ባለሥልጣን እንደዚህ ዓይነት ንግግር በፍጹም ተናግሮ እንደዚህ ብሎ ያለ የለም፤ ለኢትዮጵያኖች ትልቅ ዕድል ነው።»ም ነው ያሉት።  

ንግግሩ የፖሊሲ ተጽእኖ ለማምጣት ነው

የጥምረቱ አባል ዶክተር አክሎግ ቢራራ በበኩላቸው፣ የአምባሳደሩ ንግግር፣ የአሜሪካ መንግሥት አቋም መሆኑን ገልጸው፣ የፖሊሲ ተጽዕኖ ለማምጣት የተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት በማስቆም፣ ማዕቀቦችንና  የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ላይ ያተኮረ ስትራቴጅ እንድትከተል የጠየቀው ጥምረቱ፣ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም አስቸኳይና ሁሉን አቀፍ ውይይት ያስፈልጋል ብሏል። በንጹሐን ዜጎች ሕይወት ተጠያቂ በሆኑት ወይም የንጹሐን ዜጎችን ሕይወት ሊጠብቁ በማይችሉ የመንግሥት አካላት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ ካልተጣለባቸውም፣የአምባሳደሩ ንግግር እንደ ባዶ ቃላት ይቀራሉ ሲልም አመልክቷል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ምስል Abebe Feleke/DW

አዲስ ሕገ መንግሥት

የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና አስፈላጊ የሆነው አዲስ ሕገ መንግሥት እንዲረቀቅ እገዛ እንዲያደርግም ጥምረቱ ጠይቋል። አቶ መስፍን ስለዚሁ ጉዳይ ሲያስረዱ፤ «በ1994 የወጣው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 ማንኛውም ብሔረሰብ የመገንጠል እና አገር የመመስረት መብት ይሰጣል። ይህ ደግሞ የተራዘመ የእርስ በርስ ጦርነት እንዲፈጥር አድርጓል። ማንኛውም ብሔር የመገንጠል መብት ሲኖረው፣ የማዕከላዊ መንግሥት የማስተዳደር አቀሙም ይዳከማል። አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት የብሔር ብሔረሰብ ግጭት አባብሶ፣ ካልተስተካከለ የኢትዮጵያን አንድነት እንዲበታተን አድርጓል።»  

ዶክተር አክሎግ የሚሉትም፣ ይህንን የፌዴራል አወቃቀር ይዞ ኢትዮጵያን ለመታደግ አይቻልም ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፣ አዲስ አበባ የሚገኙት የዩናይትድስቴትስ አምባሳደር የፖሊሲ ንግግር በሚል በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ መሠረት የሌላቸው ክሶች አሰምተዋል ሲል ከሷል። የፖሊሲ መግለጫው፣ በኢትዮጵያና በዩናይትድስቴትስ መኻከል ያለውን ታሪካዊና ወዳጃዊ ግንኙነት አይመጥንም ማለቱም አይዘነጋም።

ታሪኩ ኃይሉ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW