1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአይነቱ የመጀመርያ የሆነ አዉሮፕላን ተረከበ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 26 2017

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ በአይነቱ የመጀመሪያው ነው የተባለውን ኤይርባስ A350-1000 የተሰኘውን አዲስ አውሮፕላን ተረክቧል፡፡ አየር መንገዱ በፈረንሳይ ቱሉስ በተከናወነው ስነስርዓት ከአውሮፕላን አምራቹ ኤርባስ ኩባንያ የተረከበውን የመጀመሪያውን አውሮፕላን ዛሬ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለማቀፍ አየር ፣ማረፊያ አስተዋውቋል፡፡

አዲሱ ኤይርባስ A350-1000 የተሰኘውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን
አዲሱ ኤይርባስ A350-1000 የተሰኘውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንምስል Seyoum Mekonnen/DW

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ በአይነቱ የመጀመሪያው ነው የተባለውን ኤይርባስ A350-1000 የተሰኘውን አዲስ አውሮፕላን ተረክቧል፡፡ አየር መንገዱ በፈረንሳይ ቱሉስ በተከናወነው ስነስርዓት ከአውሮፕላን አምራቹ ኤርባስ ኩባንያ የተረከበውን የመጀመሪያውን አውሮፕላን ዛሬ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለማቀፍ አየር ፣ማረፊያ አስተዋውቋል፡፡ አቪየሽን ሳንስ ፊሮንተርስ ከኤርባስ ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ አየርመንገዶች ፋውንዴሽን የተበረከተውን በ100 ሺህ ዩሮ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ተሸክሞ በአየርመንገዱ ባለስልጣናት ከሰዓቱን አዲስ አበባ የደረሰው አውሮፕላኑ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ዲፕሎማቶች በተገኙበት በደማቅ ስነስርዓት አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

በአውሮፕላኑ አቀባበል ስነስርዓት ወቅት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ዛሬ አየር መንገዱ የተቀበለው ኤይርባስ A350-1000 አውሮፕላን አየር መንገዱ ካዘዘው አራት አውሮፕላኖች አንዱ ነው፡፡ ዋና ስራ አስፈጻሚው በዚሁ ወቅት እንዳሉትም “ዛሬ እዚህ የተገናኘነው በአፍሪካ በአይነቱ ቀዳሚ የሆነውን አየር መንገዳችን የተረከበውን ኤይርባስ A350-1000 አውሮፕላን ለመቀበል ነው፡፡ ይህ ለአየር መንገዳችን የስኬት አዲስ ምዕራፍ አመላካች ነው፡፡ ይህ ሁነት በአቪየሽን ኢንደስትሪ መሪነታችንንም የሚሳይ ነው፡፡ በቢዝነስ ክላሽ ብቻ 46 እንግዶችን ማስተናገድ የሚችለው ይህ አውሮፕላን አጠቃላይ በአንድ በረራ 395 እንግዶችን ማጓጓዝም ይችላል” ብለዋል፡፡

አውሮፕላኑ በአየር ብክለትን በመቀነስ አኳያም አይነተኛ ሚና ያለው የአየር ትራንስፖርት የሚያሳልጥ ነው ተብሏል፡፡ “ባለ ሁለት ሞተር ከሆኑ ቀደምት መሰል አውሮፕላኖች አንጻር ይህ አውሮፕላን በነዳጅ ፍጆታው 25 በመቶ ቅናሽ አለው፡፡ በካርቦን ልቀትም እጅግ በተሻለ መልኩ ትንሽ መጠን ያለው በመሆኑ ከምንከተለው ውጥን ጋር የሚጣጣም ነው፡፡ ይህ አውሮፕላን ላቅ ያሉ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት ከመሆኑም ባሻገር ለደንበኞቻችን ምቾች ብለን በቀዳሚነት ያዘዝነው ነው” ሲሉም ገልጸዋል፡፡ በአውሮፕላኖች ጥራትና መጠን እራሱን እያሳደገ እንደሚገኝ የገለጸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ የቦሌ ዓለማቀፍ አየር ማረፊያን አቅም በአራት እጥፍ የሚያሳድ አየር ማረፊያ ቢሾፍቱ አከባቢ መገንባት መጀመሩን ማሳወቁም ይታወሳል፡፡

ሥዩም ጌቱ 

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW