1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲሱ ፕሮጀክት ፋይናንስ ፍለጋ

ሥዩም ጌቱ
ማክሰኞ፣ መስከረም 6 2018

በአፍሪካ ልማት ባንክ በኩል 500 ሚሊየን ዶላር አስተዋጽኦ እንደሚደረግም ከወዲሁ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ አቶ ለማ አሁን የፕሮጀክቱን ቀሪውን 7.5 ቢሊየን ዶላር ከሌሎች ባኮችና የፋይናንስ ድርጅቶች የማፈላለግ ስራ ቀሪው የሚጠበቅ ትልቁ ስራ መሆኑን አስረድተዋልም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሾፍቱ ከተማ ዙሪያ ሊያስገነባ ላቀደዉ ግዙፍ አዉሮፕላን ማረፊያ የሚያስፈልገዉን ገንዘብ በተመለከተ ባዘጋጀዉ የማስተዋወቂያ ሥብሰባ ላይ የተካፈሉ የድርጅትና የፋናናስ ተቋማት ተጠሪዎች
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሾፍቱ ከተማ ዙሪያ ሊያስገነባ ላቀደዉ ግዙፍ አዉሮፕላን ማረፊያ የሚያስፈልገዉን ገንዘብ በተመለከተ ባዘጋጀዉ የማስተዋወቂያ ሥብሰባ ላይ የተካፈሉ የድርጅትና የፋናናስ ተቋማት ተጠሪዎችምስል፦ Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲሱ ፕሮጀክት ፋይናንስ ፍለጋ

This browser does not support the audio element.

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድበ10 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ከአዲስ አበባ 40 ኪ.ሜ. በሚርቀው በቢሾፍቱ ከተማ ዙሪያ ሊያስገነባ ላቀደዉ  ግዙፍ የአየር ማረፊያ ጣቢያ ማስገንቢያ የሚሆን ገንዘብ እያፈላለገ መሆኑን አስታወቀ።አየር መንገዱ እንዳለዉ ለፕሮጀክቱ ከሚያስፈልገዉ ገንዘብ ሁለት ቢሊየን ዶላር ራሱ ይሸፍናል።ቀሪዉን የፕሮጀክቱን 80 በመቶ ወይም  8 ቢሊየን ዶላር እንዲበድሩት የተለያዩ  አበዳሪ ተቋማትን እየጠየቀ ነዉ። ለማግኘት እየጣረ ነዉ።
አየርመንገዱ በዛሬው እለት የአዲሱ ቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ ዓየርማሪፊያ ግንባታን አስመልክቶ አዲስ አበባ ውስጥ የተለያዩ አበዳሪ (የፋይናንስ ተቋማት) እና ግንባታው ላይ ሊሳተፉ የሚችሉ ተቋማትን ጋብዞ ሊገነባ ስለታቀደው አየርማረፊያ አዋጭነት፣ የአገሪቱ ከፍተኛ የፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊዎችም በተገኙበት ስለፕሮጀክቱና ተቋሙ ግንዛቤ አስጨብጧል፡፡

የፕሮጀክቱ የገቢ ምንጭ

በዚሁ ላይ አስተያየታቸውን በተለይም ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የኢትዮጵያ አየርመንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያደቻ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህን ፕሮጀክት ሲሰራ የተለያዩ የፕሮጀክት ፋይናንሲንግ መንገዶችን ተመልክቷል፡፡ “አሁን ለጊዜው የተነሳንበት 20/80 የሚባል ሲሆን 20 በመቶውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይከፍላል፤ 2 ቢሊየን ዶላር አየርመንገዱ ለዚህ ፕሮጀክት ገቢ ያደርጋል የቀረውን 80 በሞውን ደግሞ ከፋይናንስ ተቋማት ይገኛል” ያሉት ሃላፊው በአፍሪካ ልማት ባንክ በኩል 500 ሚሊየን ዶላር አስተዋጽኦ እንደሚደረግም ከወዲሁ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ አቶ ለማ አሁን የፕሮጀክቱን ቀሪውን 7.5 ቢሊየን ዶላር ከሌሎች ባኮችና የፋይናንስ ድርጅቶች የማፈላለግ ስራ ቀሪው የሚጠበቅ ትልቁ ስራ መሆኑን አስረድተዋልም፡፡ ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚመጡ ተቋማትም ብቻቸውን ሳይሆን የፋይናንስ ተቋማትን ይዘው እንደሚመጡ ይጠበቃል ያሉት አቶ ለማ ዛሬ አየርመንገዱ ባዘጋጀው የግንዛቤ መድረክ ላይ በስፋት የታደሙ ዓለማቀፍ የአየር ማረፊያ ግንባታ ድርጅቶች በዚህም ተሳትፈው አዋጭ ያሉት የአየር መንገዱ ግንባታ በተሳካ መንገድ እንደሚሳለጥ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡ 

 

ግንባተውን ለመጀመር የተጠናቀቀው የቅድመ-ፕሮጀክት ስራ

ዛሬ አየር መንገዱ የፕሮጀክቱን አዋጭነት ለዓለማቀፍ የስራ ተቋራጮች እና የፋይናንስ ተቋማት ግንዛቤ ስያስጨብጥ የተገኙ ድርጅቶች በኢትዮጵያ አየርመንገድ እና በአፍሪካ ልማት ባንክ መሆኑንም ያስረዱት ሃላፊው፤ የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ አየርመንገድን ወክሎ ገንዘቡን የማፈላለግ ሃላፊነት እንደሚወጣ ነው የገለጹት፡፡ ፕሮጀክቱን ወደ ተጨባጭ ስራ ለማስገባት የቅድሚያ ስራዎች እየተጠናቀቁም እንደሚገኙ በመጠቆም ከሶስት ወራት በኋላ አርሶ አደሮቹን ወደተዘጋጀላቸው መኖሪያ በማዘዋወር ዋናውን የአየርማረፊያውን ስራ ለመጀመር በቂ ገንዘብም መመደቡን አስረድተዋል፡፡

“ዋናው ፕሮጀክት ከዓመት በኋላ ጥቅምት ላይ ነው የሚጀመረው፡፡ አሁን የመሰረት ስራዎች ከፊታችን ታህሳስ ጀምሮ ወደ ስራ ይገባል፡፡ አሁን ኮንትራክተር ለመምረጥ የጨረታው የመጨረሻ ደረጃ ላይ ነን፡፡ ሰሞኑን አሸናፊዎች ስለሚታወቁ እነሱ ቶሎ በሶስት ወር ውስጥ ወደ ስራ ይገባሉ፡፡ አሁን ገንዘቡ አለን፣ ዝግጅቱ አለ፣ በቦታው ላይ የሰፈሩ አርሶአደሮች ሰብላቸውን ሰብስበው ወደ ተዘጋጀላቸው አዲሱ ቤት መሄዳቸው ብቻ ነው የሚጠበቀው” በማለት ለጊዜው የገንዘብ ችግር አለመኖሩንና እነዚህን የፕሮጀክት ቅድመ ዝግጅት ስራዎች አየርመንገዱ እየሰራ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡ 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው።አቶ መስፍን እንዳሉት አየር መንገዱ ባለፈው አንድ ዓመት 20 ሚሊየን ግድም መንገደኞችን በማጓጓዝ 7.6 ቢሊየን ዶላር ገቢ አግኝቷልምስል፦ Seyoum Getu/DW

ስለሚነሱት አርሶአደሮች

የኢትዮጵያ አየርመንገድቢሾፍቱ አቅራቢ አቡሴራ ከሚባለው የአየርማረፊያው ግንባታ ስፍራ 2 ሺህ 500 ግድም አርሶ አደሮች በ350 ሚሊየን ዶላር ወጪ ተለዋጭ ቤቶች እና የገቢ ምንጭ የሚሆናቸውን ፕሮጀክቶች ማዘጋጀቱን አየርመንገዱ በዛሬው እለት ለዓለማቀፍ ፋይናንስ ተቋማት እና የግንባታ ድርጅት ተወካዮች ማደረገው ገለጻ አስረድቷል፡፡ በ1 ሺህ 539 ካሬ ቦታ ላይ የገበሬዎቹ መኖሪያ ቪላዎች እንዲሁም ለግብርና ማቀነባበሪያ የሚውሉ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን እና ለንግድ ስራ የሚውሉ 10 ባለ ሰባት ወለል ህንጻዎች ቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ስለመዘጋጀታቸውም ተጠቁሟል፡፡ ከዚህም ባለፈ 200 ሄክታር በመስኖ የሚለማ ቦታ በፕሮጀክቱ ለሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መዘጋጀቱ ነው የተነገረው፡፡ 

ዘሬ አዲስ አበባ ውስጥ ዓለማቀፍ የገንዘብ እና ግንባታ ተቋማት በታደሙበት የግንዛቤ መርሃግብር ላይ ለድርጅቶቹ ተወካዮች ስለኢትዮጵያ አየርመንገድ እና አዲሱ ፕሮጀክቱ ገለጻ የሰጡት የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ባለፈው አንድ ዓመት አየርመንገዱ 20 ሚሊየን ግድም መንገደኞችን በማጓጓዝ 7.6 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገልጸውላቸዋል፡፡ አየርመንገዱ ባለፉት 10 ዓመታት ብቻ ገቢውን ከእጥፍ በላይ በማሳደግ በተከታታይ ትርፋማነቱን ማሳየቱንም አመልክተው በ2040 አየርመንገዱ ዓመታዊ የመንገደኞች መስተንግዶ አቅሙን ወደ 40 ሚሊየን ግድም በማሳደግ ዓመታዊ ገቢውንም በአራት እጥፍ በመጨመር 29 ቢሊን ዶላር ለማድረስ ማቀዱንም አስገንዝበዋል፡፡  

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር    
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW