1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የአጀንዳ መረጣ ሊያካሒድ ነው

ዓለምነው መኮንን
ሰኞ፣ መጋቢት 22 2017

በአማራ ክልል ከመጋቢት 27 ቀን 2017 ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ሊያከናውን መሆኑን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ በፈደራል ደረጃ ለሚደረገው ውይይት ተወካዮችንም እንደሚያስመርጥ አመልክቷል።

መስፍን አርዓያ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽነር
ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የሚመሩት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የአጀንዳ መረጣ ሊያካሒድ ነውምስል፦ Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የአጀንዳ መረጣ ሊያካሒድ ነው

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአገሪቱ ውስጥ በህዝቦች መካክል ሲነሱ የነበሩ አሉታዊ ትርክቶችን ከጦርነትና ከግጭት ባለፈ በውይይትና በምክክር እልባት እንዲያገኙ እየሰራ ያለ ተቋም ነው፡፡ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዮናስ አዳዬ ሰሞኑን ከዶይቼ ቬሌ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኮሚሽኑ ዓላማዎች የምክክር ባህልንና ልምድን ማዳበርና ማጎልበት፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካክል እምነት መፍጠርና አገራዊ መግባባት ማምጣት መሆኑን ገልጠዋል፡፡

እነኚህን ዓላማዎች በአትዮጵያ ውስጥ ለማሳካት ኮሚሽኑ በተለያዩ ክልሎች የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሆነ የኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡ ካለው የፀጥታ ችግር አኳያ በአማራ ክልል የአጀንዳ ልየታና በፌደራል ደረጃ በሚዘጋጀው ኮንፈረንስ የሚሳተፉ ወኪሎችን የማስመረጥ ሥራዎች ሳይካሄዱ መቆየታቸውን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥበቡ ታደሰ ጠቁመው፣ ይሁን እንጂ እንኚህን ሥራዎች ከመጋቢት 27/2017 ዓም ጀምሮ በተከታታይ ለ8 እና 9 ቀናት ለማከናወን ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ተናገረዋል፡፡

በ259 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ መራጮች ተለይተዋል

በክልሉ ከሚገኙ 267 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በ259ኙ በአጀንዳ መረጣ የሚሳተፉ ተወካዮች መመረጣቸውን አቶ ጥበቡ አመልክተው ሌሎች ወኪል ያላስመረጡ ሌሎች 8 ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች በቀሩት ጥቂት ቀናት ወኪሎቻቸውን አስመርጠው በአጅንዳ መረጣው እንዲሳተፉ የሚያደርጉ እንደሚሆኑ የሕዝብ ግ ንኙነቱ ኃላፊ አቶ ጥበቡ አስረድተዋል፡፡

ሐገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል እስረኞች እንዲፈቱ መጠየቁን

ከማሀበረሰቡ ከተመረጡ አካላት በተጨማሪ በአማራ ክልል ያሉ ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሠዎች፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች፣ ከአማራ ክልል መንግሥት የሚወከሉና ዝግጁ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲ ተዎካዮች በአጀንዳ መረጣው እንደሚሳተፉ አብራርተዋል፡፡

የፋኖ ታጣቂዎች ከመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች ውጊያ የሚያደርጉበት የአማራ ክልል የጸጥታ ሁኔታ የኢትዮጵያ ምክክር ኮሚሽን ያቀደውን ሥራ እንዲስተጓጎል አድርጓል። ምስል፦ Mariel Müller/DW

የአጀንዳ መረጣና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሳተፉ ተወካዮችን ለማስመረጥ በባሕር ዳር ክልላዊ መድርክ ለማዘጋጅት የሎጅስቲክና ተያያዥ ተግባራት ዝግጅቶች እየተካሄዱ መሆኑናቸውን ያስረዱት አቶ ጥበቡ፣ መድረኩ ክ8 እስከ 9 ቀናት ሊወስድ እንደሚችል ገልጠዋል፡፡

በአማራ ክልል ሁለት አበይት ተግባራት ሲፈፀሙ ሌሎች ሁለት ይቀራሉ

በአማራ ክልል እስካሁን ሁለት ተግባራት መከናዎናቸውን የገለፁልን ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዮናስ በሚቀጠለው ሳምንት በሚደረገው ውይይት ደግሞ ቀሪ ሁለት ተግባራት እንደሚከናወኑ አብራርተዋል፡፡

ክልሉ በፀጥታ ችግር ውስጥ ቢሆንም ሁለት አበይት ሥራዎች በስኬት ተጠናቀቀዋል ብለዋል የመጀመሪያው በክልሉ የሚሳተፉ ተሳታፊዎችን ከየዞኑ፣ ከየወረዳው መምረጥ ሲሆን፣ ሌላው የተከናወነው ተግባር ደግሞ የአጀንዳ መነሻ ሀሳቦችን መሰብሰብ እንደሆኑ ገልጠዋል፡፡

ዕድሜው በአንድ ዓመት የተራዘመው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተስፋ እና ሥጋት

“የሚቀረን በክልል ደረጃ ልክ በኦሮሚያ፣ በአዲስ አበባ፣ በደቡብ፣ በሶማሌ፣ በአፋር እንዳደረኘው፣ አማራ ክልል የሚከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብና በሀገራዊ ኮንፈረንስ በፌደራል ደረጃ የሚሳተፉት ተወካዮችን ተወካዮች ማስመረጥ ነው” ብለዋል፡፡

እነኚህ ተግባራት ደግሞ ሰሞኑን በባሕርዳር በሚደረገው ምክክር ምላሽ እንደሚያገኙ ነው ኃላፊዎቹ ያመለከቱት፡፡ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቅርቡ በባሕር ዳር ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በነበረው ውይይት በአማራ ክልል ከመንግሥት ጋር በትጥቅ ትግል የሚዋጉ አካላት ወድ አገራዊ ምክክሩ እንዲመጡ የተኩስ አቁም እንዲደረግና የታሰሩ የፖለቲከኛ እስረኞች እንዲፈቱ ጥያቄ ማቅረቡና መልካም ምላሽ እንዳገኘ ኮሚሽኑ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡

ዓለምነው መኰንን

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW