1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ አጣብቂኝ፦ ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን ማዳከም ወይስ…?

Eshete Bekele
እሑድ፣ ታኅሣሥ 14 2016

ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን ባለፉት አራት ዓመታት በባንኮችም ይሁን በጎንዮሽ ገበያው ከፍተኛ ለውጥ አሳይቷል። ብር ሲዳከም ለኢትዮጵያ ምን ፈየደ? ለሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ ሁለተኛ ምዕራፍ ዳጎስ ያለ ማስፈጸሚያ የሚሻው መንግሥት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የሚቀነቀነውን ብርን የማዳከም እርምጃ ሊቀበል ይችላል?

የኢትዮጵያ ብር ሽንኩርት እና ድንች ተራ
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ሁለተኛ ምዕራፍ ለሦስት ዓመታት እንደሚዘልቅ አስታውሰው “በዚህ የተራዘመ ሒደት ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓታችን እንዴት ሪፎርም መደረግ አለበት የሚለው የተለያዩ ጥናቶች ተጠንተው ወደፊት የሚታይ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

ውይይት፦ ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን ማዳከም ወይስ…የኢትዮጵያ አጣብቂኝ

This browser does not support the audio element.

በታኅሳስ 2012 በኢትዮጵያ ባንኮች 32 ብር ከ50 ሣንቲም ገደማ የነበረው የአንድ ዶላር ምንዛሪ በዚህ ሣምንት ወደ 57 ብር ገደማ አሻቅቧል። ባለፉት አራት ዓመታት ብር በሽርፍራፊ ሣንቲሞች በዝግታ ሲዳከም ቆይቶ የምንዛሪ ተመኑ የ25 ብር ገደማ ለውጥ ታይቶበታል። በተለምዶ “ጥቁር” እየተባለ በሚጠራው የጎንዮሽ ገበያ ከ51 እስከ 56 ብር ይመነዘር የነበረው የአሜሪካ ዶላር በዚህ ሳምንት ከ110 እስከ 120 ብር መድረሱን ዶይቼ ቬለ ባደረገው ማጣራት ለመረዳት ችሏል።

የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ያሉ ተቋማት የብር የምንዛሪ ተመን ትክክለኛ ዋጋውን አላገኘም በሚለው ጉዳይ ቢስማሙም ችግሩ እንዴት ይፈታ በሚለው ጉዳይ ላይ ወጥ አቋም የላቸውም።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በ2012 ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 2.9 ቢሊዮን ዶላር ለመበደር ሲስማማ በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለመዘርጋት አቅዶ ነበር። ይሁንና የተራዘመ የብድር አቅርቦት እና የተራዘመ የፈንድ አቅርቦት በተባሉ ሁለት ማዕቀፎች የተፈጸመው የብድር ውል በመስከረም 2014 የተቋረጠ ሲሆን የግብይት ሥርዓቱም እንደተባለው በገበያ ፍላጎት የሚመራ አልሆነም።

ለሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ሁለተኛ ምዕራፍ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዳጎስ ያለ ገንዘብ ለመበደር የጠየቀው የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚደራደርባቸው ጉዳዮች አንዱ ይኸው የብር የምንዛሪ ተመን አንዱ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ያምናሉ። የውጭ ምንዛሪ ግብይትን ማስተካከል በሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ሁለተኛ ምዕራፍ ከተካተቱ ዐበይት ሥራዎች አንዱ ነው።

መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲከወን ያደርግ እንደሁ በብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ የተጠየቁት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ “በዚህ ረገድ የተደረገ አዲስ ውሳኔም፤ ለውጥም” የለም ሲሉ ተናግረዋል። 

የሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ሁለተኛ ምዕራፍ ለሦስት ዓመታት እንደሚዘልቅ ያስታወሱት አቶ አሕመድ “በዚህ የተራዘመ ሒደት ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓታችን እንዴት ሪፎርም መደረግ አለበት የሚለው የተለያዩ ጥናቶች ተጠንተው ወደፊት የሚታይ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።  በጉዳዩ ላይ የተሰሩ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን “በጣም የተሳሳተ” ሲሉ ነቅፈዋል።  

ለመሆኑ ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን ሲዳከም ለኢትዮጵያ በተለይም ለወጪ ንግድ ምን ፈየደ? የኢትዮጵያ መንግሥት ለሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ሁለተኛ ምዕራፍ ማስፈጸሚያ የሚሻውን የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ብርን ማዳከም እንደ ቅድመ-ሁኔታ ቢቀመጥ ተግባራዊ ያደርጋል? ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን የበለጠ ቢዳከም በኢትዮጵያ ገበያ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያሳድራል?

በዚህ ውይይት የገንዘብ አስተተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ፣ በዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ ሆነው በመስራት ላይ የሚገኙት ዶክተር ቀልቤሳ መገርሳ እና በጀርመን የልማት እና ዘላቂነት ጥናት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪው ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም ተሳትፈዋል።

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW