1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አምስት ተጨማሪ ኩባንያዎች እያቋቋመ ነው

ረቡዕ፣ ኅዳር 10 2018

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የመማሪያ መጻሕፍት አታሚ ድርጅት እና የወጣቶች የኢንቨስትመንት ባንክ ጨምሮ በዚህ ዓመት አምስት ኩባንያዎች እንደሚያቋቁም አሳውቋል። ከሁለት የሩሲያ ኩባንያዎች ጋር የመግባቢያ ሥምምነቶች የተፈራረመው ተቋም ከ2011 ጀምሮ የስኳር ፋብሪካዎች ለመሸጥ ሲደረግ የነበረው ጥረት አቋርጧል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና ሩሳል የተባለ ግዙፍ የሩሲያ ኩባንያ የአልሙኒየም ማቅለጫ ለመገንባት ያቀደ የመግባቢያ ሥምምነት ባለፈው ሣምንት መፈራረማቸውን ሲያሳውቁ
ሩሳል ከተባለ የሩሲያ ኩባንያ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ሥምምነት ተግባራዊ ከሆነ በዓመት 500,000 ቶን አልሙኒየም የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ በኢትዮጵያ ይገነባል። ምስል፦ Ethiopian Investment Holdings

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አምስት ተጨማሪ ኩባንያዎች እያቋቋመ ነው

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና ሩሳል የተባለ ግዙፍ የሩሲያ ኩባንያ የአልሙኒየም ማቅለጫ ለመገንባት ያቀደ የመግባቢያ ሥምምነት ባለፈው ሣምንት መፈራረማቸውን አሳውቀዋል። ሥምምነቱ ተግባራዊ ከሆነ በዓመት 500,000 ቶን አልሙኒየም የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ በኢትዮጵያ ይገነባል። ይህ ዕቅድ እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ ፍላጎት ለማሟላት እና ሀገሪቱ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ እንደሚያስችል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አሳውቋል።

ከ3 እስከ 4 ዓመታት ባለው ጊዜ ግንባታው ይጠናቀቃል የተባለው ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ አንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቅ ነው። ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ዕቅዱን “ለመደገፍ ከፍተኛ ፍላጎት ባሳዩ” አበዳሪዎች የሚሸፈን እንደሚሆን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።

የመንግሥት የመዋዕለ-ንዋይ ክንፍ የሆነው ተቋም ከሩሳል በተጨማሪ ዋይልድቤሪስ ከተባለ የሩሲያ የኤሌክትሮኒክ ግብይት አገልግሎት አቅራቢ ኩባንያ ጋር ሌላ የመግባቢያ ሥምምነት መፈራረሙን አሳውቋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆንዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ እና የዋይልድቤሪስ አቻቸው ሮበርት ሚርዞያን የተፈራረሙት ሥምምነት የኢትዮጵያን የኤሌክትሮኒክ ግብይት ሥነ-ምኅዳር ለማልማት ያቀደ ነው ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ እንደ አሜሪካው አማዞን እና እንደ ቻይናው አሊባባ ሸቀጦች የሚሸጥበት ዲጂታል ገበያ ባለቤት የሆነው ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ እና ሰፊው የአፍሪቃ ገበያ ለመግባት የያዘውን ዕቅድ ይህ የመግባቢያ ሥምምነት እንደሚደግፍ ተገልጿል።

በ2014 የተመሠረተው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ባለፉት ወራት በሽርክና አብረውት የሚሠሩ የውጭ ኩባንያዎችን የሚመለምልበትን ስልት ለውጧል። ባለፈው ሣምንት የተቋሙ የ2018 የመጀመሪያ መንፈቅ የሥራ አፈጻጸም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ሲቀርብ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በዓለም አቀፍ ገበያ የተመሰከረላቸው ኩባንያዎች ለሽርክና መመልመል እንደጀመረ የተቋሙ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ መለከት ኃይሉ ተናግረዋል።

ተቋሙ “የተመሰከረ የሥራ ልምድ ያላቸው ልክ እንደ ዳንጎቴ አይነት ያሉ ትላልቅ ተቋማትን አፈላልጎ” የካበተ ልምድ ባዳበሩባቸው ዘርፎች “ሊስፋፉ የሚችሉ ከፍተኛ ኢንቨስትመንቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ይሻላል” የሚል ስልት ከዚህ ዓመት ጀምሮ እየተከተለ እንደሚገኝ አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የመረጠው አካሔድ “ውጤታማ ሆኖ” እንደተገኘ ያብራሩት መለከት ከዚህ ቀደም “ፍላጎት ዐሳይተው የመጡ ኢንቨስተሮችን ለማጥራት፤ ምርመራ በመሥራት የምናጠፋውንም ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶልናል” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከተቋቋመ አራት ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን በሥሩ 40 ኩባንያዎች ይገኛሉ። ይሁንና የተቋሙ ኃላፊዎች በተያዘው ዓመት ብቻ ተጨማሪ አምስት ኩባንያዎች የመመሥረት ዕቅድ አላቸው። የመማሪያ መጻሕፍት አታሚ ድርጅት እና ዳንጎቴ ጎዴ ዩሪያ ማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ በተያዘው ዓመት ከሚመሠረቱ መካከል ይገኙበታል።

የኢትዮጵያን የኤሌክትሮኒክ ግብይት ሥነ-ምኅዳር ለማልማት ያቀደ ነው የተባለ የመግባቢያ ሥምምነት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና ዋይልድቤሪስ በተባለ የሩሲያ ኩባንያ መካከል ምስል፦ Komsomolskaya Pravda/Russian Look/IMAGO

የደንበኞች አገልግሎት፣ የፋይናንስ እና የሰው ኃይል አስተዳደር ሥራዎችን ለሌሎች ተቋማት የሚያከናውን (Business process outsourcing (BPO) ኩባንያ በሽርክና በ21 ሚሊዮን ዶላር የማቋቋም ውጥን እንዳለ ምክትል ሥራ አስፈጻሚዋ መለከት ኃይሉ ገልጸዋል። ፓስፖርት ለማምረት የተመሰረተውን ቶፓን ግራቪቲ ኢትዮጵያ የተባለ ኩባንያ በ85 ሚሊዮን ዶላር በማስፋፋት የታክስ ቴምብር እንዲሠራ ለማድረግ ተቋማቸው በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም አሳውቀዋል። ሌላው ከአፍሪቃ ልማት ባንክ ጋር ሊመሠረት የታቀደው የወጣቶች የኢንቨስትመንት ባንክ ነው።

“በእነሱ በኩል 10 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ይሰጠናል ብለን ነው የምንገምተው። እኛ ደግሞ እሱን የሚስተካከል ገንዘብ በብር አዋጥተን የአስተዳደር ኩባንያ እናቋቁማለን” ያሉት መለከት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ለኩባንያው በሚቋቋመው ቦርድ ውስጥ ተወካዮች እንደሚኖሩት ገልጸዋል።

“የኢንቨስትመንት ግምገማ እና አጽዳቂ ኮሚቴ ይኖረዋል። በዚያ መሠረት ፍትኃዊ እና ግልጽ በሆነ መልኩ ተስፋ ያላቸውን ኢንተርፕራይዞች፤ ጀማሪ የሆኑ ግለሰቦችንም መደገፍ የምንችልበት ማዕቀፍ ይኖራል” በማለት የሚቋቋመው የወጣቶች ኢንቨስትመንት ባንክ ሊኖረው ይችላል ተብሎ የሚጠበቀውን ሚና አብራርተዋል። 

አዲስ በሚቋቋሙት ኩባንያዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እንደ መንግሥት የልማት ድርጅቶች ሙሉ ባለቤትነት አይኖረውም። ተቋሙ እስካሁን ከነበረው አካሔድ በተለየ በኩባንያዎቹ ከ50 በመቶ በታች ድርሻ እየያዘ አነስተኛ ባለአክሲዮን (minority shareholder) ይሆናል።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር የሚገኙ ተቀጥላ ድርጅቶች በ2017 በጀት ዓመት 2.05 ትሪሊዮን ብር ገቢ ማስገባታቸውን ዶክተር ብሩክ ታዬ የሚመሩት ተቋም ይፋ አድርጓል። በተያዘው ዓመት የልማት ድርጅቶችን አጠቃላይ ገቢ 2.75 ትሪሊዮን ብር የማድረስ ዕቅድ አለው።

በ2018 የመጀመሪያ መንፈቅ ብቻ 671 ቢሊዮን ብር ገደማ ገቢ እንዳገኘ ቢገለጽም ሁሉም ተቀጥላ ድርጅቶች ግን ዕኩል ውጤታማ አይደሉም። ለምሳሌ ያክል የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን 21% እንዲሁም መተሐራ ስኳር ፋብሪካ 37% ገቢያቸው እንደቀነሰ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የቀረበላቸውን ሰነድ ዋቢ አድርገው ተናግረዋል።

የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለዓለም ገበያ የሚያቀርበውን የተፈጥሮ ሙጫ ከሚያገኝባቸው ቦታዎች መካከል በመተማ አካባቢ ባለው “የሰላም እጦት” እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሥራ ላይ በዋለ “የፖሊሲ ለውጥ ምክንያት” ገቢው እንደቀነሰ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከፍተኛ አመራሮች አንዷ የሆኑት አስማ ረዲ አብራርተዋል።

የግብርና ሚኒስቴር በአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት ረገድ ያደረገው ለውጥ በኮርፖሬሽኑ ገቢ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ኮርፖሬሽኑ ለገበሬዎች እና ግብርና ላይ ለተሠማሩ ኢንቨስተሮች ለማቅረብ ወደ ኢትዮጵያ ያስገባቸውን “በርካታ የግብርና ማሽነሪዎች” የውጭ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲወሰን ሲደረግ “የአርሶ አደሩ የመግዛት አቅም ስለቀነሰ” መሸጥ ሳይችል እንደቀረ ቺፍ ፖርቶፎሊዮ ኦፊሰር የሆኑት አስማ ረዲ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮ-ኢንጂኔሪንግ ግሩፕ፣ የስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ እና የኢንዱስትሪ ግብዓቶች አቅራቢ ድርጅት በኦዲት ሪፖርት ረገድ ችግሮች እንዳሉባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተችተዋል።ምስል፦ picture-alliance/Photoshot/Xinhua/S. Ruibo

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በሥሩ የሚገኙ የልማት ድርጅቶች “ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ተቋማት እንዲሆኑ በዘመናዊ የኮርፖሬት አስተዳደር እና ፋይናንስ ሥርዓት መመራታቸዉን” የማረጋገጥ ሥልጣን እና ኃላፊነት ተጥሎበታል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነበረው ውይይት ከቀድሞው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ እና አስተዳደር ኤጀንሲ ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከተዘዋወሩ መካከል አሁንም ውስብስብ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ መኖራቸውን በግልጽ አሳይቷል።

“አብዛኞቹ የልማት ድርጅቶች በደርግ ጊዜ የተወረሱ እና በመንግሥት የተቋቋሙ” መሆናቸውን ያስታወሱት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ሐብታሙ ኃይለሚካኤል “የማምረት አቅማቸው በየጊዜው እየወረደ ይሔዳል። ሁለተኛ አንዳንዴም በብልሽት ምክንያት ረዥም ጊዜ ቆመው እየታደሱ የመጡ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል። አዳዲስ መሣሪያዎች በመግዛት ጭምር “በተቻለ መጠን በየጊዜው አቅማቸው እያደገ እንዲሔድ ጥረት እየተደረገ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

ከተቋማቱ መካከል የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮ-ኢንጂኔሪንግ ግሩፕ፣ የስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ እና የኢንዱስትሪ ግብዓቶች አቅራቢ ድርጅት በኦዲት ሪፖርት ረገድ ችግሮች እንዳሉባቸው የምክር ቤቱ አባላት ተችተዋል። የድርጅቱ የፋይናንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ረድዔት ጌታቸው ግን “አንዳንዶቹ ድርጅቶች እስከ ዐሥር ዓመት የሚደርስ የኦዲት ውዝፍ ሥራ ነበረባቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የፋይናንስ ባለሙያዎችን “በጣም የከፋ ችግር” ባለባቸው የልማት ድርጅቶች በመመደብ፣ እገዛ እንዲሰጡ በማድረግ እና “የድርጅቶቹን የፋይናንስ ባለሙያዎች በማብቃት የኦዲት ውዝፉን እንዲያጠሩ ከፍተኛ ሥራ” መከናወኑን ረድዔት ጌታቸው ተናግረዋል። “ከኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በስተቀር ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተቀላቀሉት ሁሉም የኦዲት ሪፖርታቸውን ማከናወን እንዲችሉ እና እንዲያዘምኑ ተደርጓል” በማለት አብራርተዋል።

በቅርቡ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ እና አስተዳደር ኤጀንሲ ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተቀላቀሉ ስምንት ድርጅቶች “ውዝፍ ኦዲት በምን እንደተፈጠረ ችግሮቻቸውን በመለየት እነሱን በማገዝ ላይ ነን” ሲሉ ተደምጠዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በተፈራረመው የብድር ሥምምነት በገባውግዴታ መሠረት እስከ ሁለት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ሐብት የሚያሳይ የመጀመሪያ የተጠቃለለ የሒሳብ መግለጫ ሪፖርት ተቋሙ እንደሚያወጣ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ መለከት ኃይሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር የሚገኙ ተቀጥላ ድርጅቶች በክልሎች ያሏቸው ይዞታዎች “ያለ ተቋማት ዕውቅና” ለግለሰቦች ተላልፎ መሰጠት ወይም “መምከን” ሌላው ችግር እንደሆነ የተቋሙ ኃላፊዎች አስረድተዋል። ችግሩን በመፍታት ረገድ “በተወሰኑ ቦታዎች መፍትሔ” መገኘቱን የገለጹት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ሐብታሙ ኃይለሚካኤል ጉዳዩ የምክር ቤቱን ትኩረት እንደሚሻ ጠቁመዋል።

“የተቀጥላ ድርጅቶች አሁን ባለው ሀገራዊ ሪፎርም እና ከተሞችንም፣ አካባቢዎችንም ለመቀየር በሚደረገው ሒደት ውስጥ ይዞታቸውን የመቀማት አካሔድ በጣም በሰፊው እየሔደ ነው” ያሉት ዋና የፖርቶፊሊዮ ኃላፊ አስማ ረዲ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካሳ ቢሰጥም በሌሎች ክልሎች ተመሳሳይ እርምጃ እንዳልተወሰደ ገልጸዋል።

መንግሥት ስምንት የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዛወር መንግሥት ለዓመታት በተደጋጋሚ ያደረገውን ጥረት እንዳቋረጠ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ኃላፊዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ አረጋግጠዋል።ምስል፦ Ethiopian Sugar Corporation

ስምንት የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዛወር መንግሥት ለዓመታት በተደጋጋሚ ያደረገውን ጥረት እንዳቋረጠ የተቋሙ ኃላፊዎች ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ አረጋግጠዋል። በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር የሚገኘው የኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በአሁኑ ወቅት 13 ስኳር እና ተያያዥ ምርቶች የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ያስተዳድራል። ከእነዚህ መካከል አራቱ በምርት ላይ የሚገኙ ሲሆን ጣና በለስ፣ ከሰም አንድ፣ አርጆ ዴዴሳ እና ተንዳሖ በሙከራ ላይ ናቸው። ጣና በለስ ሁለት፣ ኦሞ ኩራዝ አንድ እና አምስት እንዲሁም ወልቃይት የስኳር ፋብሪካዎች በአንጻሩ ግንባታቸው ቢጀመርም ከ “ፕሮጀክት” ምዕራፍ ፈቅ አላሉም።

መንግሥት ከ2011 ጀምሮ የስኳር ፋብሪካዎችን እና የሸንኮራ አገዳ ማሳዎችን ጭምር በተናጠል ወይም በጠቅላላ ለመሸጥ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ሒደቱ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተሳተፉበት ነው። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ መለከት ሳኅሉ ፋብሪካዎቹን በጨረታ ለመሸጥ የተደረገው ሙከራ “ውጤታማ ስላልሆነ” “በቀጥታ ድርድር” ለማጠናቀቅ ተሞክሮ እንደነበር ተናግረዋል።

“ፍላጎት ያላቸው የተለያዩ ወገኖች መጥተው ከእነሱ ጋር ውይይት እያደረግን ቆይተን ነበር” ያሉት መለከት ኩባንያዎቹ በተደጋጋሚ ያቀረቧቸው የመግዣ ዋጋዎች መንግሥት ካስቀመጠው “ዝቅተኛው የመጠባበቂያ ዋጋ (minimum reserve price) ያነሱ” በመሆናቸው የስኳር ፋብሪካዎቹን ለመሸጥ የተጀመረው ሒደት መቋረጡን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የስኳር ፋብሪካዎቹ ዋጋ ከተተመነ ሁለት ዓመታት ያለፈው በመሆኑ መከለስ እንደሚያስፈልግ ያስረዱት ምክትል ሥራ አስፈጻሚዋ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የሚሸጡትን እና በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚቆዩትን ወደፊት እንደገና እንደሚለይ አስረድተዋል።

የስኳር ፋብሪካዎቹን ለመግዛት ውይይት ለጀመሩ ኩባንያዎች “ሒደቱን በይፋ እንዳቋረጥን የሚያመላክት ደብዳቤዎችን ልከናል” ሲሉ ተናግረዋል። ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት የታቀዱት ስኳር ፋብሪካዎች እና ሊገነባቸው ውል ወስዶ የነበረው የቀድሞው የብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሀገሪቱን ለከፍተኛ ኪሳራ ከዳረጉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል ናቸው።

አርታዒ ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW