የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትሩፋትና ተግዳሮቱ
ዓርብ፣ ሰኔ 20 2017
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትሩፋትና ተግዳሮቱ
በኢትዮጵያ በሙሉ አቅጣጫ ስራ ላይ መዋሉ ከተነገረ አንድ ዓመት ሊሞላዉ ጥቂት ጊዜ የቀሩት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤት ፈተና ማስከተሉን የምጣኔ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ የውጪ ምንዛሪን ለገበያው መተውን ጨምሮ በርካታ የማክሮ ኢኮኖሚው ለውጦችን ገቢራዊ ያደረገው ማሻሻያው በተለይም የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን በተፈለገው ፍጥነት ለመቆጣጠር የቀናው አይመስልም የሚሉ አስተያየቶች ከማህበረሰቡ ይነሳል፡፡
መንግስት በፊናው የዋጋ ንረትን መቆጣጠር የሚያስችል ተስፋ መታየቱትንና የዋጋ ግሽበቱ ምጣኔ በመቶኛ እየቀነሰ ስለመምጣቱም ያስረዳል፡፡ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ግን በብዙ መልኩ ለውጥን ያስከተለው የኢኮኖሚ ማሻሻያው እምርታም ሆነ ፈተናን አስከትቷል ባይ ናቸው፡፡
ላለፉት ጥቂት ዓመታት ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር በሰፊው ወደ ትግበራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የውጪ ምንዛሪን ከጥብቅ የመንግስት ቁጥጥርና ውሳኔ በማውጣት ለነጻ ገቢያ መተውን ጨምሮ የካፒታል ገቢያን እስከማስጀመር ደርሷል፡፡ በዚህን ወቅትም በተለይም ከውጪ ምንዛሪው አኳያ የብር የመግዛት አቅም የበለጠ ተዳክሞ ተስተውሏል፡፡ ማሻሻያውን ተከትሎ በእቅዱ የተያዙ ግቦች ተሳክተው ይሆን፤ በሚል የተጠየቁት የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ዘመደነህ ንጋቱ፤ “አገር በቀል ኢኮኖሚክ ሪፎርም ስራ ላይ መዋል ከጀመረ ወዲህ በተናጥል መስፈርቶች ሳይሆን በጥቅል ስታይ ለአገር ጠቃሚ ወደ ሆነ ደረጃ ተሸጋግሯል” የሚል አስተያየት ነው የሰጡን፡፡የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር የሚመሩ ሹማምንት በዋሽንግተን ምን አሉ?
ሌላው መቀመጫቸውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረጉት የምጣኔ ሃብትና ፋይናንስ ባለሙያ አቶ አብዱልመናን መሀመድ የኢኮኖሚው ማሻሻያውን ጉዞ በገመገሙበት አስተያየታቸው፡ “በማሻሻያው የኢትዮጵያ ብር በእጅጉ ተዳክሟል፣ በመደበኛው የባንኮች የውጪ ገንዘብ ምንዛሪ ከትይዩ ገቢያው አንጻር ማጥበብ የታለመ ቢሆንም እሱም በተፈለገው ደረጃ አልተሳካም” ብለዋል፡፡
የዋጋ ንረትን መቆጣጠር የማሻሻያው ፈተና
እንደ አብዛኛው የአገሪቱ ሸማቾች አስተያየት ከአምና አንጻር የምርቶች ዋጋ በብር ስሰላ የማይቀመስ ደረጃ ላይ በመድረሱ ኑሮን ከባድ አድርጎባቸዋል፡፡ እንደ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ አስተያየት ግን፤ “የኑሮ ውድነትን በተመለከተ መንግስትም ችግሩን ተገንዝቦ በማሻሻያውም ትኩረት የሰጠው አንደኛው ጉዳይ ነው” በማለት የዋጋ ንረቱ ካለፉት ሁለት ዓመታት አኳያ በ30 በመቶ ግድም መውረዱን ጥረቶቹን በአዎንታዊነት እንድንመለከተው ያስገድዳል የሚል ሃሳባቸውን ነው ያጋሩት፡፡ በተለይም የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር ብሔራዊ ባንክ በንግድ ባንኮች በብድር መልክ ወደ ገቢያ የሚረጨው ገንዘብ ላይ ገደብ በመጣል የሰራው ስራ ውጤት ማስገኘቱንም ያምናሉ፡፡ከአገራዊው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማግስት አልረጋጋ ያለው ገበያ
የኢኮኖሚ ማሻሻያው መዘዞች
አቶ አብዱልመናን መሀመድ ግን የኢኮኖሚው ማሻሻያው መዘዙም ቀላል እንዳልሆነ ባስረዱበት አስተያየታቸው፤ “የዋጋ ግሽበት አዝማሚያ ብታይም ባጠቃላይ ግን ኑሮ እየተወደደ ነው” በማለት ከማሻሻያው በኋላ የአገሪቱ እዳ ከብር አኳያ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበት፣ በተለይም በውጪ ምንዛሪ እዳ የነበረባቸው እንደ ብሔራዊ ባንክ እና መንግስት ያሉ ተቋማት ከፍተኛ የእዳ ጫና ላይ የወደቁበትና በተቀዛቀዘው ኢኮኖሚ ህብረተሰቡ ላይ ተደራራቢ ታክስ የወደቀበት ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡ ከማሻሻያው በኋላ ኢኮኖሚው በተለያዩ መስኮች ለውጪ ዜጎች ክፍት መሆናቸውና መንግስት ከብሔራዊ ባንክ እየተበደረ የኑሮ ውድነቱን የሚያባብስበትን አግባብ የሚዘጋው ህግ መውጣቱን ደግሞ በበጎ ጎኑ አንስተውታል፡፡ለኢትዮጵያ ከዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ምን አለ?
ባንኮች ላይ የሚጣል የብድር ገደም ጉዳት
የአገሪቱ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ከአንድ ወር ግድም በፊት በሰጡት መግለጫ ካለፉት ዓመታት አኳያ የዋጋ ንረቱ በመቶኛ በእጥፍ ማውረድ መቻሉንና ለሚቀጥለው ዓመት ምጣኔውን ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ መታቀዱን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ባለሙያዎቹ እንዳሉት ለዚህ ውጤት መንግስት የግልና የመንግስት ንግድ ባንኮች የሚሰጡት ብድር ላይ ገደብ በመጣል ቢሆንም ይህ ደግሞ የራሱ የሆነ መዘዝ አለው፡፡ አቶ አብዱልመናን እንዳሉት፤ “የኢትዮጵያ መንግስት ይሄን ቀጥተኛ” ተብሎ የሚጠቀሰውን መፍትሄ ባይጠቀመው እመክራለሁ፤ በማለት ባንኮች የሚሰጡት ብድር ላይ ገደብ መጣል ገቢያውን ከማረጋጋት አኳያ አዎንታዊ ሚና ብኖረውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ግን በመገደብ አሉታዊ አስተዋጽኦን እንደሚስከትል አመልክተዋል፡፡ የዋጋ ንረቱን ወደ ሚፈለግ ደረጃ በማውረድ ግን ገደቡን የማንሳቱ ስራ እንደሚፈጸም ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ዮሃንስ ገብረግዚአብሔር