የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ50 ሚሊዮን ብር ንብረት ተሰረቀበት
ማክሰኞ፣ የካቲት 25 2017
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ባለፉት ሰባት ወራት፣ ከ 50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኃይል መሰረተ-ልማት ሰርቆት እንደተፈፀመበት እና በዋና ከተማዋ አዲስ አበባም ጭምር በጠራራ ፀሀይ፣ በመሰረተልማቶች ላይ የሚፈፀመው ስርቆት ለአገልግሎት መቁዋረጥ ምክኛት መሆኑ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሚኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ታዬ ለዶቸቨለ ሬድዮ ተናገሩ
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሚኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ታዬ ለዶቸቨለ ሬድዮ በሰጡት ቃለመጠይቅ የተቋማቸው ተግባር፣ የኤሌክትሪክ ሀይልን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል በጅምላ ገዝቶ ለደንበኞች ማቅረብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሀይል መሰረተልማቶች ላይ የሚፈፀመው ስርቆት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትልቅ ተግዳሮት እየፈጠረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውም ጉዳት እንደዚሁ እየከፋ መምጣቱንም አመልክተዋል፡፡ ተቋማቸው ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ (የካቲት 24 ቀን 2017)፣ በተያዘው የበጀት አመት ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኃይል መሰረተ-ልማት ስርቆት መፈፀሙን አስታውቋል፡፡ የኮሚኒኬሽን ስራ አስፈፃሚው አቶ መላኩ ታዬ፣ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባም ጭምር በጠራራ ፀሀይ፣ በመሰረተልማቶች ላይ የሚፈፀመው ስርቆት፣ በሀይል ማስተላለፊያ መስመሮች፣ በትራንስፎርመር እና በሀይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ያያተኮረ መሆኑን ገልፀው፣ እነዚህ በውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ሀብቶች በመሆናቸው የሚያስከትለው ጉዳት ትልቅ ነው ብለዋል፡፡ የሰርቆት ድርጊቱ በአገልግሎት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ እንዳለውም አመልክተዋል፡፡
‘በመሰረተልማቶች ላይ በሚደርሰው ጉዳት ምክንያት የሀይል አቅርቦት ሲቋረጥ፣ ተጎጅዎቹ ደንበኞች ብቻ አይደሉም፣’
ተቋሙም ከፍተኛ ጉዳት ያስተናግዳል የሚሉት አቶ መላኩ፣ ይህ ድርጊት ከደንበኞች የምናገኘውን ገቢ ያሳጣናል፣ የወደሙትን መሰረተልማቶች መልሰን ለመጠገን የምናወጣው ወጪም ከፍተኛ ነው በማለት ገልፀዋል፡፡ የስርቆት ድርጊቱን ከመከላከል አኳያ፣ በአሁኑ ጊዜ መጠነኛ መሻሻል አለ የሚሉት የኮሚኒኬሽን ስራ አስፈፃሚው፣ ሆኖም አሳሳቢነቱ በመቀጠሉ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ይህን ችግር ለማስቆምና እነዚህን የሀገር ሀብቶች ከውድመት ለመታደግ ሊተባበሩ ይገባል ብለዋል፡፡
የኤለኤክትሪክ መሰረተልማቱ እየተሰረቀ ያለው ተቀባዮች ስላሉ ነው፣ እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ‘
የሚሉት አቶ መላኩ፣ መንግስትም አጥፊዎችን ለህግ በማቅረቡ በኩል እየሰራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ ባወጣው መግለጫ፣ በዚህ በጀት ዓመት ባለፉት ሰባት ወራት 163 የስርቆት ወንጀሎች መፈፀመቻውንና ወንጀል እንደፈፀሙ በፍርድ ቤት የተረጋገጠባቸው 13 ተከሳሾችም እስከ 10 ዓመት የሚደርስ እስራት እንዲፈረድባቸው አመልክቷል፡፡
ሀና ደምሴ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ