የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አግልግሎት የታሪፍ ጭማሪ በአዲስ ዓመት
ሐሙስ፣ ነሐሴ 30 2016የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አግልግሎት ከአዲሱ አመት ጀምሮ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍ ጭማሪ ተግባራዊ እንደሚሆን ዐሳወቀ ። የታሪፍ ማሻሻያው የወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍ ማሽሻያ መጽደቁን ተከትሎ ነው ። የታሪፍ ማሻሻያው የተደረገው እንደ ደንበኞች የኃይል አጠቃቀም መሰረት ስሌት ይደረጋል የተባለው የኤሊክትሪክ ፍጆታ ጭማሪ ከመስከረመ 1 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ሽፈራው ተሊላ ታሪፉ የደንበኞችን የኃይል አጠቃቀም መሰረት ያደረገ እና በየደረጃው የመኖሪያ ቤት ደንበኞች፤ የንግድ ተቋማት፤ ዝቅተኛ ኢንዱስትሪ እንዲሁም ከፍተኛ ኢንዱስትሪ በሚል እንደለየ ተናግረዋል ። የኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ ለሆኑ እንደየ ፍጆታ አጠቃቀማቸው መንግስት ድጎማ እንደሚያደርግላቸው ገልጠዋል።
እንደ ተቋሙ ኃላፊ ገለፃ ከሆነ ከሀምሳ ኪሎ ዋት በታች ለሚጠቀሙ ደንበኞች ያለውን ልዩነት 75 በመቶ፤ ከመቶ ኪሎ ዋት በላይ የሚጠቀሙ ደንበኞች 40 በመቶ፤ ከሦስት መቶ ኪሎ ዋት በታች የሚጠቀሙ ደግሞ 4 በመቶ የሚሆነውን ይደጎማሉ ብለዋል ። ከአምስት መቶ ኪሎ ዋት በላይ የሆነ የኤሊክትሪክ ኃይል የሚጠቀሙ ደንበኞች ደግሞ ሌላውን ተጠቃሚ የሚደግፉበት የድጎማ ሥርዓት ተግባራዊ ይደረጋል ያሉት ኃላፊው የታሪፍ ማሻሻያው በአጠቃልይ በኪሎ ዋት 6 ብር መሆኑን ጠቁመዋል ። ይህ ጭዋምሪ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ የሚሆነው በእየ አራት ወር በሚደረግ የጭማሪ ማሻሽያ ሆኖ በ አራት ዓመት የሚጠናቀቅ መሆኑንምዐሳውቀዋል ።
የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ ክፍያው በ16 ዙር በሚደረግ የሂሳብ ማስተካከያ ከመጭው መስከረም ወር ጀምሮ በ2021 ይጠናቀቃል ተብሏል ። ከጊዜ ወደጊዜ እየናረ ከመጣው ከኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት ጋር ተያይዞ ያለው ጫና ተቋማቸው እንዳስጠናው የተናገሩት ሥራ አስፈፃሚ ጭማሪው የሚፈጥረው ጫና 2 ከመቶ አይበልጥም ሲሉ ቢናገሩም፤ ዶቼቪሌ ያናገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሞያ ጭማሪው ተጠቃሚው ላይ ግልጽ እና ቀጥተኛ ጫና እንደሚያሳርፍ ተናግረዋል ።
ሐና ደምሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ