1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ስምምነት ፣ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 2016

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ስምምነቱን ውድቅ የሚያደርግ ነው ያሉትን ሕግ በፊርማቸው ማጽደቃቸውን ተናግረዋል። የፈረሙትን ሕግ ዓላማውን "አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን ብሎም የግዛት አንድነታችንን ለመጠበቅ" ያለመ ብለውታል። ዛሬ ፕሬዝዳንቱ ከፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር ለመምከር ወደ ኤርትራ ተጉዘዋል"

በሶማሌላንድ እና ኢትዮጵያ መካከል የተፈረመዉን መግባብያ ስምምነት ተከትሎ የድጋፍ ሰልፍ በድሬዳዋ
በሶማሌላንድ እና ኢትዮጵያ መካከል የተፈረመዉን መግባብያ ስምምነት ተከትሎ የድጋፍ ሰልፍ በድሬዳዋ ምስል Mesay Tekelu/DW

ፕሬዝዳንቱ "በሁለቱ ወንድማማች ሀገራት የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ከፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር ለመምከር ወደ ኤርትራ ተጉዘዋል"

This browser does not support the audio element.

ሶማሊያ የሉዓላዊ ግዛቷ አካል አድርጋ ከምትቆጥራት ሶማሌላንድ ጋር ኢትዮጵያ ያደረገችው ስምምነት የቃጣናው ዐቢይ አለምአቀፍ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል። ለኢትዮጵያ ወታደራዊ እና የንግድ እንቅስቃሴ ለማከናወን የሚያስችላትን የባሕር በር የሚያስገኝላት ነው የተባለው ስምምነት ከተፈረመ ከአንድ ወር በኋላ ሂደቱ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ መግባባት ላይ የተደረሰበት ሲሆን ሶማሌላንድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አልያም በቴሌኮም ዘርፍ ድርሻ ልታገኝ የምትችልበት ነውም ተብሏል። የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐመድ ይህንን ስምምነት ውድቅ የሚያደርግ ነው ያሉትን ሕግ ትናንት በፊርማቸው ማጽደቃቸውን ተናግረዋል። የፈረሙትን ሕግ ዓላማውን "አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን ብሎም የግዛት አንድነታችንን ለመጠበቅ" ያለመ ብለውታል።

አወዛጋቢው የመግባቢያ ስነድ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች

የፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት ዛሬ እንዳስታውቀው ደግሞ ፕሬዝዳንቱ "በሁለቱ ወንድማማች ሀገራት የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ከፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር ለመምከር ወደ ኤርትራ ተጉዘዋል"

 ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ፕሮፌሰር መረሳ ፀሐዬ ስምምነቱ ከኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ያለፈ ፣ አዲስ የአፍሪካ ቀንድ የኃይል አሰላለፍ ያስከተለ የሚመስል መሆኑን ገልፀዋል። አክለውም ኢትዮጵያ ያንን ስምምነት የመተግበርም ሆነ ያለመተግበር አጠብቂኝ ውስጥ የመግባት እጣ እንዳይገጥማት ሥጋታቸውን ገልፀዋል። የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ የዚህ ሁሉ ችግር መነሻ ያልሰመረ ያሉት የቀድሞው የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ፎርማጆ፣ የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግንኙነት መሆኑን ጠቅሰዋል። 
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት የኤርትራ ጉዞ 

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐመድ ይህንን ስምምነት ውድቅ የሚያደርግና "አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን ብሎም የግዛት አንድነታችንን ለመጠበቅ" የሚውል ያሉትን ሕግ ትናንት አጽድቀዋል። ይህ ክስተት ከተፈጠረ ወዲህ ፕሬዝዳንቱ የመጀመርያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝታቸውን ሠራዊታቸውን ስታሰለጥንላቸው ወደከረመችው ኤርትራ ዛሬ አድርገዋል። ኢጋድን ጨምሮ ፣ አፍሪካ ሕብረት ፣ አረብ ሊግ ፣ የአውሮጳ ሕብረት እንዲሁም ሀገራት በተናጠል የሶማሊያ ሉዓላዊ ግዛት እንዲከበር ሳምንቱን በመግለጫ እና በአቋም መግለጫ አጨናንቀውታል።

የድሬደዋ አስተዳደር የጠራው የድጋፍ ሰልፍ
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ይህንን ስምምነት በሀገራቸው ነፃነት፣ ሉዓላዊነት ፣ የግዛት አንድነት ላይ የተቃጣ ጥቃት አድርገው ገልፀውታል።
በሌላ በኩል የሶመሌላንድ መከላከያ ምኒስትር ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የተፈራረሙንትን የመግባቢያ ሠነድ በመቃወም ከሶማሊያ ወግነው ከሥልጣን በፈቃዳቸው መልቀቃቸው ተነግሯል። የሀገራቸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስለስምምነቱ እውቅና እንዳልነበረውና ጉዳዩን በብዙኃን መገናኛዎች መስማታቸውንም አያይዘው በ ኤክስ ገልፀዋል።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቱ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ፕሮፌሰር መረሳ ፀሐዬ "እኛ [ኢትዮጵያ] የፈለግነውን ነው እየፈፀምን ያለነው ወይስ እያስፈፀምን ነው ያለነው" በማለት ጉዳዩ አለም ዐይኑን ከፍቶ የሚመለከተው መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ እውቅናን የተመለከተ ስምምነት ቋጥራለችን ?

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ባለፈው ሳምንት ለዴቼ ቬለ ያጋሩ አንድ የአለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ ባለው አለም አቀፍ የዲፕሎማሲ አሰላለፍ ሶማሌላንድ እንደ ሀገር የምትታወቅ ባለመሆኑ በስምምነቱ ምክንያት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ሶማሊያም ይሁን ከአፍሪካ ሕብረት ጋር ያላትን ግንኙነት እንዳያሻክር ኢትዮጵያ "በተለይ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ወደ ጎን የምትተውበትን እድል እንዳይፈጥር" ሥጋታቸውን ገልፀው ነበር።
ኢትዮጵያ ከኤርትራ የባሕር በር የማግኘት ጥረቷ አለመሳካቱን ወይም በታሰበው ጊዜ አለመሄዱን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ማብራሪያ ገልፀዋል። ከሶማሌላንድ ጋር በተደረገው ፊርማ የእውቅናው ጉዳይ "ስምምነት ሆኖ አልተረከብንም" ሲሉም ተደምጠዋል። 
"ከኤርትራ ጋር ሰላም ለማውረድ በተደረገው ጥረት ውስጥ አንዱ የንግግር መስክ የነበረው ምጽዋንም ፣ አሰብንም ሌላ አማራጭም ካለ በተለያዩ አማራጮች ፣ ኤርትራ አልምታ ኢትዮጵያ እንድትጠቀም ወይም በጋራ አልምተን ለመጠቀም ይሁን ሌላ ሶስተኛ ወገን አልምቶ መጠቀም" መርህ ሥራዎች ተጀምረው መንገድ እስከመስራት ተደርሶ ነበር።

ሶማሌላንድ የባህር ወደብ ምስል Brian Inganga/Ap Photo/picture alliance

የኢትዮጵያ እና የሶማሌ ላንድ የወደብ ስምምነት፤የኮንጎ የምርጫ ውጤት ውዝግብ
ሆኖም "ሁኔታዎቹ በተለያየ መንገድ በተፈለገው ፍጥነት እና መልክ ስላልሄዱ ሌሎች አማራጮችን ደግሞ መፍጠር ነበረብን" ሲሉ እቅዱ አለመስመሩን ገልፀዋል። 

የስምምነቱ ዐበይት ጭብጦች 

"በሶማሌላንድ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚሊቴሪ ቤዝ - ወታደራዊ ሠፈር እና ኮሜርሻል ማሪታይም- የባሕር መርከብ ሠፈር እንዲኖራት ይፈቅዳል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በይዘቱ በሊዝ የሚታሰብ ይሆናል፣ ለ ሃምሳ አመት እና ከዚያ በላይ ደግሞ በማስፋፊያ የሚካሄድ እንዲሆን ያደርጋል" የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ እንደሚሉት በአፍሪካ ቀንድ እየተፈጠረ ያለው ሁኔታ መነሻው የሦስቱ ጎረቤት ሀገራት ያልሰመረ ያሉት ግንኙነት ነው። 

ከሶማሊያ እየተሰጡ ያሉ አስተያየቶች እና የደቀኑት ሥጋት 

የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድን ስምምነት ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቴን ተጋፍታለች በሚል ለዓለም አቤት ብሏል። በፕሬዝዳንቱ የፀደቀና ስምምነቱን ውድቅ የሚያደርግ ሕግም መፈረሙ ቀላል እንድምታ ያለው አይደለም። ከዚሁ ስምምነት ማግስት ሶማሊያ ውስጥ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የኦሮሞ ማኅበረሰብ አባላት ስደተኞች ላይ አደጋ መጋረጡን መረጃ እንዳለው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አስታውቋል።
ወትሮውንም በጦርነትና ግጭት፣ በአለመረጋጋት ፣ በድህነትና ኋላቀርነት ፣ በድርቅና ስደት የሚታወቀው ግን ደግሞ የአለም የምመርከብ ምልልስ እና የንግድ ማሳለጫ መስመር መገኛ የሆነው የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባሕር ከባቢ ይህ አዲስ ክስተት ምን ይዞ ይመጣ ይሆን የሚለው ሌላ ትኩረት የሳበ አጀንዳ ሆኗል።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW