1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያውያን እና ሶማሌ ስደተኞች

ረቡዕ፣ ጥር 23 2010

በየመን ባሕር ሰርጥ አቅራቢያ ባለፈው ሃሙስ የሞቱ ኢትዮጵያውያን እና ሶማሊያውያን ስደተኞች ቁጥር መጨመሩን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን አስታወቀ :: ኮሚሽኑ በተለይ ለዶቼቬሌ እንደገለጸው መርከቡ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በከፈቱት የመሣሪያ ጥቃት የሰጠመ ሲሆን የተጓዦቹም ቁጥር ከ 300 ይበልጣል ::

Überfahrt Mittelmeer Ünglücke Schiffsuntergang Flash-Galerie
ምስል picture-alliance/dpa

በየመን የባህር ዳርቻ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ስደተኞች ሞት

This browser does not support the audio element.

ከ 300 በላይ ስደተኞችን ጭኖ ከየመን ወደ ጅቡቲ ይጓዝ በነበረው መርከብ ላይ ጥቃት የተከፈተበት ባለፈው ሃሙስ ነበር :: ወደ አውሮፓ ለመፍለስ ከሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መርከቡን የሞሉት ተሳፋሪዎች መርከቡን የሸጡላቸው ሕገ ወጥ የስደተኛ አዘዋዋሪዎች ተጨማሪ ብር እንዲከፍሉ ማስገደዳቸው በፈጠረው አለመግባባት መርከቧ በተተኮሰ ጥይት ተመታ ልትሰጥም ችላለች :: ጄኔቫ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ዊልያም ስፒንድለርን በስልክ አግኝተን አነጋግረናቸው ነበር :: ባለፉት ተከታታይ ቀናት አል ቡራ ኢቃ አቅራቢያ በሚገኘው የባሕር ሰርጥ ተጨማሪ አስክሬኖች መገኘታቸው የሟቾቹን ቁጥር ከ 30 በላይ በእጥፍ ሊጨምረው እንደቻለ የኮምሽኑ ቃል አቀባይ ዊልያም ስፒንድለር ጥነግረውናል ::
" በርካታ ሶማልያውያን እና ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በመርከቡ ውስጥ ነበሩ :: በድንገት መርከቡን የሸጡላቸው ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ተጨማሪ ገንዘብ እንዲከፍሉ አስገደዷቸው :: የተጠየቁትን ማድረግ ባለመቻላቸው በመርከቡ ላይ የመሣሪያ ጥቃት ፈጸሙ :: በርካታዎችም በጥይት ተመተው እና ባሕሩ ውስጥ ሰጥመው ሕይወታቸው አልፏል :: "
ዓለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት መረጃ እንደሚጠቁመው እ.ኤ.እ በ 2017 ዓ.ም ብቻ ከ 87 ሺ የሚልቁ አፍሪቃውያን ስደተኞች ለሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪ ደላሎች ገንዘብ በመክፈል ሕይወታቸውን ለአደጋ የሚያጋልጡ አሮጌ መርከቦችን እየገዙ የትውልድ ሃገራቸውን ጥለው በየመን አቆራርጠው ወደ አውሮፓ ለመሻገር ጥረት አድርገዋል :: አብዛኛዎቹም በሕገወጥ ደላሎች አካላዊ ጥቃት ስቃይ እና ግፍ ተፈጽሞባቸዋል :: ገሚሶቹም በሚያሳዘን ሁኔታ የባሕር ሲሳይ ሆነዋል :: ያም ሆኖ ዛሬም አደገኛው የባህር ላይ ፍልሰቱ አልቆመም :: የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ዊልያም ስፒንድለር ሰዎች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥሉት ወደው አይደለም ይላሉ ::
" ሰዎች እንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ አደጋ ላይ ህይወታቸውን የሚጥል ተግባር የሚፈጽሙት ምንም ምርጫ ስለሌላቸው እንደሆነ እናውቃለን :: የትውልድ ሃገራቸውን ጥለው እንዲፈልሱ የሚገደዱት ድህነት ስራ አጥነት የሰብአዊ መብት ጥሰት አፈና ጭቆና እና የእርስ በእርስ ግጭትን ከሃገራቸው በመሸሽ እንዲሁም ነጻነታቸውን በመሻት ጭምር ነው "
ከሊቢያ በሜዲትራኒያን ባሕር በሚደረገው አደገኛ ጉዞም በርካታ አፍሪቃውያን ስደተኞች በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እየታገቱ የባርነት ሰለባ ሆነው ጉልበታቸው እንደሚበዘበዝ ይታወቃል :: ከዚህ ውጭ እስር ግድያ ጥቃት እና የሰውነት አካላቸውን ጭምር በግዳጅ በቀዶ ህክምና እያወጡ የመሸጥ አሰቃቂ ወንጀልም እንደሚፈጸምባቸው በየመገናኛ ብዙኃኑ ተዘግቧል :: የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ቃል አቀባይ ስፒንድለር ከሊቢያም አፍሪቃውያን ስደተኞችን የማውጣቱ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ይናገራሉ ::

" ሊቢያ ውስጥ የሚታየው ሁኔታ እጅግ አስከፊ ነው :: በስደተኞች ላይ የሚፈጸመውን ሰቆቃ በጽኑ ስናወግዝ ቆይተናል :: ያ ብቻ ግን አይበቃም :: በሃገሪቱ በእስር እና በባርነት የሚንገላቱ በአስቸኳይ እንዲወጡ ተጨማሪ ሥራዎችን እያከናወንን እንገኛለን :: በተቻለ ፍጥነት መፍትሄ እንሰጣቸዋለንም ብለን እናምናለን "
በአሁኑ ወቅት ሊቢያ ውስጥ ብቻ ከ 400 ሺህ በላይ ስደተኞች እንዳሉ የተባበሩት መንግስታት የሥደተኞች ኮምሽን መረጃ ያመለክታል :: ድርጅቱ በያዝነው የአውሮፓውያን አመት 30 ሺ ያህሉን በፈቃደኝነት መርሃግብር ወደመጡበት ሀገር የመመለስ ዕቅድ እንዳለውም ታውቋል ::

ምስል picture-alliance/dpa
ምስል Picture-alliance/dpa/E. Morenatti/AP

እንዳልካቸው ፈቃደ 

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW