1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ እና የሶማሌ ላንድ የወደብ ስምምነት፤የኮንጎ የምርጫ ውጤት ውዝግብ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 27 2016

በኢትዮጵያ እና እንደ ሀገር ዕውቅና ባላገኘችው የሶማሌላንድ መካከል የተፈረመው የወደብ የመግባቢያ ሰነድ በዚህ ሳምንት ትኩረት ከሳቡ የአፍሪቃ ጉዳዮች አንዱ ነው።በሌላ በኩል በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በቅርቡ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በስልጣን ላይ ያሉት ፊሊክስ ሼሴኬዲ በድጋሜ ማሸነፍ ሀገሪቱን እያወዛገበ ነው።

የሶማሌላንድ የበርበራ ወደብ
የሶማሌላንድ የበርበራ ወደብ ምስል MUSTAFA SAEED/AFP

የኢትዮጵያ እና የሶማሌ ላንድ የወደብ ስምምነት፤የኮንጎ የምርጫ ውጤት ውዝግብ

This browser does not support the audio element.


በኢትዮጵያ እና እንደ ሀገር ዕውቅና ባላገኘችው የሶማሌላንድ መካከል የተፈረመው የወደብ የመግባቢያ ሰነድ በዚህ ሳምንት ትኩረት ከሳቡ የአፍሪቃ ጉዳዮች አንዱ ነው።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለወራት  የባህር በር ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።  ንግግራቸው ከጎረቤት ኤርትራ ጋር አዲስ አለመግባባት ያመጣል የሚል ስጋት አሳድሮ የነበረ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ሞቃዲሾ የሚገኘው የሶማሊያ መንግስት ብዙም ቁጥጥር በማያደርግባት ከሰሜን ምዕራብ ተገንጣይ ግዛት ከሶማሌላንድ ጋር በጎርጎሪያኑ በአዲስ አመት 2024 መባቻ  ስምምነታቸውን ሲፈጽሙ ግርምትን ፈጥሯል።
የስምምነቱ ማዕከል የሆነው የበርበራ የንግድ ወደብ ሲሆን፤ በቅርቡ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚገኘው የወደብ ሎጂስቲክስ ኩባንያ ዲፒ ወርልድ በከፍተኛ ደረጃ እንዲስፋፋ ተደርጓል።
ኢትዮጵያ ወደቡን ለዓለም አቀፍ ንግድ ከመጠቀሟ በተጨማሪ የባህር ኃይል የምትገነባበትን መሬት ከሶማሌላንድ ማግኘት ትፈልጋለች።
ሶማሊላንድ በምላሹ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አክሲዮን እኩል ዋጋ ታገኛለች። በተጨማሪም የዓብይ መንግስት «ሶማሌላንድ እውቅና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ አቋም ለመውሰድ ጥልቅ ግምገማ ለማድረግ» ቃል ገብቷል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ከሶማሌላንድ መሪ ጋር የመግባቢያ ሰነድ በአዲስ አበባ ሲፈራረሙምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

የስምምነቱ ቃላቶች ለትርጓሜ ክፍት ቢሆኑም፤የሶማሊላንድ ጉዳይ ግን በምንም አይነት ዲፕሎማሲያዊ ግምገማ ቢሆን ሞቃዲሾ የሚገኘውን የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት የሚዋጥ አይደለም።በኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ሥምምነት የተቆጣችው ሶማሊያ ፊቷን ወደ ግብጽ አዙራለች
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ሱራፌል ጌታሁን ለDW እንደተናገሩት ይህ የመግባቢያ ስምምነት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ዚያድ ባሬ የአስተዳደር ዘመን ያሻግራል።
«ይህን የመግባቢያ ሰነድ መፈራረም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ከሲያድ ባሬ አስተዳደር ዘመን ያሻግራል። ይህም ቀጠናውን ወደ ከፍተኛ ቀውስ ያመራል።  በቀጣናው ባሉት ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነትም አደጋ ላይ ይጥላል።»ብለዋል።
 እስከ ጎርጎሪያኑ 1991 ዓ/ም ድረስ ለ22 ዓመታት ስልጣን ላይ በነበረው በአምባገነኑ የሲያድ ባሬ  አገዛዝ ዘመን ሶማሊያ ፤የኢትዮጵያን ግዛት ኦጋዴን ለመቆጣጠር ሞከራ አልተሳካላትም።
በጎርጎሪያኑ ከ1977-78 ከተካሄደው አጠቃላይ ጦርነት በተጨማሪ ሶማሊያ አማፂ ሚሊሻዎችን በአሁኑ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልም ውስጥ አሰማርታ ነበር።በለንደን ኪንግ ኮሌጅ እና በፓሪስ ኢንስቲትዩት ዴስ ሞንዴስ አፍሪካንስ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር መድኃኔ ታደሰ በበኩላቸው ስምምነቱ ከጎረቤት ሶማሊያ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ሊያመጣ  ይችላል ይላሉ።
«በእርግጥ ግብፅን ጨምሮ እንደ ገልፍ ሃይሎች ካሉ ሀገራት ጋር በመተባበር የማተራመስ ስልት ውስጥ ሊሳተፉ ይችላሉ። ምን አልባትም የኢትዮጵያ ታጣቂ ቡድኖች መግቢያ መሆንን ይደግፉ ይሆናል። በዋናነት ግን ዋና ወኪላቸው ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።»ሲሉ ለDW ተናግረዋል። ሶማሊያ የግዛት አንድነቷን ከሚደግፉት የአውሮፓ ህብረት፣ የአሜሪካ እና የአፍሪካ ህብረት ድጋፍ አግኝታለች።
ኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጋር የጀመረችው አዲስ አጋርነት
እንደ ፕሮፌሰር መድህኔ ታደሰ ገለጻ፣ ጉዳዩ  ከቀጠናዊ  ጂኦፖለቲካ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ሲሆን፤ ይኸውም ከሌሎች የቀይ ባህር ሀገሮች ጋር በመሆን በሳውዲ አረቢያ  መሪነት በጎርጎሪያኑ 2020 ዓ/ም የተመሰረተው የፀጥታ ትብብር ነው።እሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ የዚህ አካል አይለችም።
«የተባበሩት አረብ ኢምሬቶችም እና ኢትዮጵያ ሁለቱም የዚህ አካል አይደሉም።ሌሎቹ አሉ።በሳውዲዎች መሪነት በሁለቱ ትልልቅ ጎራዎች መካከል በሂደት ለውጥ ታይቷል። እና ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አንድ ጎራ ውስጥ አይደሉም።በእርግጥ እነሱ በተቃራኒ ጎራ ውስጥ ነበሩ።» ሲሉ  ጠቁመዋል። 
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በሳዑዲ አረቢያ መራሹ የየመን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ንቁ ሚና እየተጫወተች ነው።

በየመን የርስበርስ ጦርነት የተጎዳው የአደን ከተማ ምስል SALEH AL-OBEIDI/AFP

የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ከበርበራ ወደብ በስተደቡብ 250 ኪሎ ሜትር (155 ማይል) ርቆ በሚገኘው የየመን በደቡባዊ ክፍል በተለይም በአካባቢ ቡድኖች ላይ ተፅዕኖ አላት።ከሌላ አጋር ጋርም የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በቀይ ባህር እና በስዊዝ ካናል በኩል በዓለም አቀፉ የንግድ መስመር  በኤደን ባህረ ሰላጤ ያላቸውን ተፅዕኖ ያሳድጋል፣ከኢትዮጵያ ጋር መተሳሰርም እንደ ፕሮፈሰር መድህኔ ለሀገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች ትርጉም አለው።
"ያንን መሬት ይፈልጉ ነበር። ያንን መዳረሻ ይፈልጉ ነበር። ከዚያ በላይ ግን የፀጥታ አካልም ጭምር ነው።ህብረት መፍጠርም ነው። ለኤምሬትስ ለጥቅማቸው ከኢትዮጵያ ጋር መስራት ቀላል ነው።የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትርም ቢሆኑ በማንኛውም ዋጋ ስልጣናቸውን መጠበቅ ይፈልጋሉ።ስለዚህ  የገንዘብ ድጋፍ ይሻሉ። እናም ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ማግኘት ይችላሉ።»
ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር የኢሚሬትስ ገንዘብ እና ትጥቅ እያሽቆለቆለ ባለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጀርባ  ላይ ስልጣናቸውን ለማጠናከር መሳሪያ ሊሆን እንደሚችል ፕሮፌሰር መድህኔ ያምናሉ።
በዚህ ሁኔታ የተሻሻለ የባህር ንግድ ተጠቃሚነትም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ሸቀጦችን በጅቡቲ በኩል መላክ የነበረባት ቢሆንም፤ ጅቡቲ በጎርጎሪያኑ 2018 ዓ/ም ፈቃዱን ሰርዛለች።ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአረብ ኤሚሬትቶቹ ዲፒ ወርልድ ይመራ በነበረው፤ በጅቡቲ ወደብ ጉዳይ  ለበርካታ ጊዜ በፍርድ ቤት ክርክር ተደርጓል።
ለሶማሌላንድ እውነተኛ ነፃነት ትኬት?
የዚህ ውስብስብ የሃይል ጨዋታ ዋና ተጠቃሚ ሶማሌላንድ ልትሆን ትችላለች።  በጎርጎሪያኑ1991ዓ/ም የአንድ ወገን የነጻነት አዋጅ ካወጀች በኋላ፣ ከተቀረው የሶማሊያ ግዛት የበለጠ ጠንካራ የአስተዳደር መዋቅሮችን ዘርግታለች።ፕሮፌሰር መድህኔ፤«የሶማሊላንድን እውቅና የሚቃወም ምንም አይነት ክርክር የለም። ነገርግን ማንም ሀገር ቀዳሚ መሆን አልፈለገም።»ብለዋል።አወዛጋቢው የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ የመግባቢያ ሰነድ
የሶማሊላንድ መሪ ሙሴ ቢሂ አብዲ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ይህን አቋም ባለመምረጣቸው  አድንቀዋል።አብይ ቃል የገቡት «ጥልቅ ግምገማ» በመጨረሻ የሚፈለገውን የሶማሌላንድ እውቅና ያመጣ እንደሁ ግን ወደፊት የሚታይ ይሆናል።

ሌላው በዚህ ሳምንት ትኩረት ከሳቡ የአፍሪቃ ጉዳዮች አንዱ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ነው። 
በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን (CENI) በአወዛጋቢው የታኅሣሥ 20 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ  ፌሊክስ ሺሴኬዲ ለሁለተኛ ጊዜ አሸናፊ መሆናቸውን አውጇል።

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፊሊክስ ሽሴኬዲ ምስል Pool Vlad Vanderkelen/Belga/picture alliance

ኮሚሽኑ በጊዜያዊው ውጤት መሰረት የወቅቱ ፕሬዚዳንት  73.34% ድምጽ ማግኘታቸውን ገልጿል።ነገር ግን ውጤቱን  የሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ማረጋገጥ አለበት።የ2023 የኮንጎ ምርጫ ታሪካዊነትና የተወዳዳሪዎች ብዛት
ያም ሆኖ የፕሬዚዳንቱ ሁለተኛ የስልጣን ዘመን ብዙ ተግዳሮቶች ያሉት ነው። ከነዚህም መካከል የደህንነት ማጣት እና  የኢኮኖሚ ችግር ይገኙበታል። በአገራዊ አንድነትና ክልላዊ ትብብር ላይም ፕሬዚዳንቱ መስራት ይኖርባቸዋል።
ፕሬዚዳንቱ ዋበመጀመርያው የስልጣን ዘመናቸው መጀመሪያ ላይ፣ በምስራቅ ኮንጎ በተለይም በሰሜን ኪቩ ግዛት ያለውን ሁከት ለማስቆም ቃል ገብተው ነበር። በወቅቱም «ሰላም እንዲመለስ ህይወቴን ለመስዋት ዝግጁ ነኝ» ሲሉ ተደምጠው ነበር።  ከአምስት ዓመታት በኋላ ግን ሁኔታው ከመባባስ በቀር የተለወጠ ነገር የለም።
የታጠቁ ቡድኖች እና የሚሊዮኖች መፈናቀል 
ሀገሪቱ ምንም አይነት የፖለቲካ አላማ በሌላቸው ወደ 200 በሚጠጉ የታጠቁ ቡድኖች በግጭት ስትታመስ የነበረች ሲሆን፤ ኪንሻሳ  ዛሬም ከ M23 አማፂ ቡድን ጋር ተፋጣለች።ቡድኑ ሰፊ ቦታዎችን በመያዝ የሰሜን ኪቩ ዋና ከተማ የሆነችውን ጎማን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየዛተ ነው።
 ሌሎች የታጠቁ ቡድኖችም በምስራቅ ኮንጎ እየተንቀሳቀሱ ነው።በሰላማዊ ዜጎች ላይ በሚሰነዘረው ጥቃትም በርካቶች የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሆነው በመጠለያ ካምፖች እንዲኖሩ ተገደዋል ይላሉ፤ በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ  የኮንጎ የምርምር ድርጅት (GEC) ዳይሬክተር የሆኑት ጄሰን ስቴርንስ። 
«ዛሬ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተፈናቀሉ ዜጎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ቁጥራቸው ከፍ ያለ ሲሆን፤ ወደ 7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በተፈጠረው አስቸጋሪ የፀጥታ ሁኔታ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሆነዋል።የመንግስት ተጠያቂነት ሳይጠናከር በምስራቅ ኮንጎ ውስጥ የትኛውንም ዘላቂ የሰላም መፍትሄ ማሰብ አይቻልም።»ሲሉ ስቴርንስ አስጠንቅቀዋል።

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወታደሮች በቅኝት ላይ ምስል Alain Uaykani/Xinhua/IMAGO

ሺሴኪዲ፣ ሁሉንም የሚሊሻ ቡድኖች ትጥቅ ለማስፈታት የሚያስችል አጠቃላይ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንዳለባቸው ስቴርን ያምናሉ።
በኦታዋ፣ ካናዳ በሚገኘው በሴንት ፖል ዩኒቨርሲቲ የግጭት ጥናት ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ኢቮን ሙያ፣ ግን ፕሬዚዳንቱ በምስራቅ ኮንጎ ያለውን ስር የሰደደ የጸጥታ ችግር ማስቀደም አለባቸው ይላሉ። 
«እሱ አፋጣኝ መልስ መስጠት አለበት። ወይም ቢያንስ በኪቩ አውራጃዎች የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የሚያስችል ስልት እንዳለው ለኮንጎ ህዝብ  ያሳይ።»
 በፖለቲካ ጥላቻ የሀገር አንድነት አደጋ ላይ መውደቅ
የታኅሣሥ 20 አጠቃላይ ምርጫ  በፖለቲካ ባለድርሻ አካላት እና ተፅዕኖ ፈጣሪዋን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ በሲቪል ማኅበራት መካከል፣ ያለመተማመን መንፈስ የሰፈነበት ነበር።
ለአንድ ወር የዘለቀው የምርጫ ቅስቀሳ በጎሳ የጥላቻ ንግግሮች የተሞላ ነበር።እንደ ኢቮን ሙያ፣ ያሉ ተንታኞች እንደሚሉት ሽሴኬዲ የተከፋፈለውን ህዝብ መልሰው የሚያገናኙበት መንገድ በአስቸኳይ መፈለግ አለባቸው።
«ፕሬዚዳንት ሺሴኪዲ  በህብረተሰቡ ላይ እምነት ለመፍጠር እና እያንዳንዱ የኮንጎዋዊ  የአንድ ሀገር ዜጋ   እንደሆነ እንዲሰማው ለማድረግ የሚያስታርቅ  ቋንቋ የመጠቀም ግዴታ አለባቸው።» ብለዋል ሙያ።
ተንታኙ ይህን ይበሉ እንጅ ጉዳዩ  ጉዳዩ ቀላል አይመስልም። ምክንያቱም ተቃውሞ ከሚያዘጋጁ የፖለቲካ ባላንጣዎች በተጨማሪ፣በሀገሪቱ አዲስ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ጥምረት ተፈጥሯል።
በቀድሞው የምርጫ ኮሚሽን ኃላፊ በኮርኔይል ናንጋአ የተቋቋመው አሊያንስ ፍሌቭ ኮንጎ (ኤኤፍሲ) በበኩሉ ሺሴኬዲን በጠመንጃ እንደሚያስወግድ ዝቷል።
በክልሉ  እየጨመረ ያለው ውጥረት
በሌላ በኩል  ሽሲኬዲ በኮንጎ እና በምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ/ EAC/ አጋሮች መካከል እያደገ የመጣውን አለመግባባት ለመቅረፍ አዲስ ክልላዊ የትብብር ስልት መንደፍ ይኖርባቸዋል።
ከኤም 23 አማፂያን ጋር በሚደረገው ውጊያ የቡድኑ ወታደሮች ሃላፊነት ከሩዋንዳ ጋር አለመግባባት በኮንጎ እና በኬንያ መካከል ደግሞ ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል ። በኮንጎ እና በኡጋንዳ መካከልም ውጥረት አለ።ሙያ እንደሚሉት በምስራቃዊ ኮንጎ ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት  አባል ሀገራቱን ማረጋጋት ይጠይቃል።

የኮንጎ ፕሬዚዳንት ሽሲኬዲ በኮንጎ እና በምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ/ አጋሮች መካከል እያደገ የመጣውን አለመግባባት ለመቅረፍ አዲስ ክልላዊ የትብብር ስልት መንደፍ ይኖርባቸዋል

«የምስራቅ አፍሪቃን የፀጥታ ችግር ለመፍታት የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ አባል ሀገራት ማረጋጋትን ይጠይቃል። ያም ሆነ ይህ፣ ከኤም 23 እውነተኛ መሪዎች ጋር መደራደር አስፈላጊ ከሆነ፣ የኮንጐ መንግሥት ከሩዋንዳ ጋር ድርድር መቀጠል እንዳለበት ያውቃል።»
 ሀብታም ሀገር፣ ድሃ ዜጎች
ለተመራጩ ፕሬዚዳንት የኢኮኖሚ ድቀትም ሌላው ፈተና ነው።ፕሬዚዳንት ፊሊክስ ሽሴኬዲ በአንድ ወቅት ኮንጎን "የአፍሪካ ጀርመን" ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር። ነገር ግን በእሳቸው አስተዳደር የኮንጐ ፍራንክ ዋጋ ማሽቆልቆሉን ቀጥሏል። ይህም የአብዛኛውን ዜጋ የኑሮ ደረጃ እንዲያሽቆለቁል አድርጓል።።
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት  የኑሮ ውድነት እና የስራ አጥነት ጉዳዮች ሲነሱ፣ ቲሺሴኬዲ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ 6.2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እና የዓለም ባንክ 21 በመቶ አካባቢ የገመተውን፤ የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ቃል ገብተዋል።

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፊሊክስ ሼሴኪዲ በሀገሪቱ መዲና በኪንሻ ምስል Arsene Mpiana/AFP/Getty Images

የኮንጎ ምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት እስራኤል ሙታላ በማዕድን በበለፀገችው ኮንጎ  የኢኮኖሚ እድገት የዓለም ባንክ በ2023 ከገመተው የ 7%  ይልቅ በሁለት አሃዝ መሆን ነበረበት ይላሉ።
« ትሽኬዲ በማዕድን ዘርፍ ላይ ብቻ ሳያተኩር ኢኮኖሚውን ማስፋት አለበት። ግብርናን ማስተዋወቅ፣ የሀይል መሠረተ ልማት ግንባታ እና የየብስ ትራንስፖርት በተለይም የመንገድና የባቡር መስመርም መዘርጋት አለበት።»  ሲሉ ሙታላ ለDW ተናግረዋል።»
 የማህበራዊ አገልግሎት ፖሊሲ ስኬት
በማህበራዊ አገልግሎት ሺሴኬዲ ካስገኟቸው ድሎች መካከል ነፃ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እና .ሴቶች በመንግስት ሆስፒታሎች በነፃ እንዲወልዱ የሚያስችል ነፃ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና አገልግሎት መስጠት ናቸው። .ነገር ግን 20 ሚሊዮን ኮንጎዋዉያንን ከአስከፊ ድህነት ለማውጣት   በፓርቲያቸው /UDPS/ የተቋቋመው የ«ህዝብ  ይቅደም» መፈክር ትልቅ ህልም ሆኖ ነው የቀረው።
ከኮንጎ ህዝብ ሩብ ያህሉ ለረሃብ እና ለምግብ እጦት የተጋለጠ ሲሆን፤ 62% የሚሆኑት ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ። ሀገሪቱ እስከ 40,000 ሜጋ ዋት ሃይል የሚያመነጨው እና አንድ ሶስተኛውን የአፍሪቃን  የኤሌክትሪክ ፍላጎት መሸፈን  የሚችለው  የኢንጋ ግድብ ባለቤት ብትሆንም፤  ከሀገሪቱ ህዝብ  15 በመቶው ብቻ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኛል።
እንደ ምጣኔ ሀብት ባለሙያው እስራኤል ሙታላ ገለጻ፣ በኢኮኖሚ ስኬታማ ለመሆን፣ ሺሴኪዲ የዲፕሎማሲያዊ ትኩረታቸውን መቀየር አለባቸው።
«ከጦርነት ወይም ከሰላም ዲፕሎማሲ ባሻገር ብዙ የውጭ ባለሃብቶችን መሳብ የሚችል የልማት ዲፕሎማሲ ያስፈልገናል። መዋቅራዊ ፕሮጄክቶችን ለመደገፍ  ከሁለትዮሽ እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ዲፕሎማሲም ያስፈልገናል። » ሲሉ ሙታላ ለDW ተናግረዋል።

ፀሀይ ጫኔ 
ዮሀንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW