1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ እና የጀርመን ቢዝነስ ፎረም በበርሊን ተካሔደ

ረቡዕ፣ ኅዳር 17 2018

የኢትዮጵያ እና የጀርመን ኩባንያዎችን ከመንግሥት ባለሥልጣናት እና ከልማት ድርጅቶች የሚያገናኘው የቢዝነስ ፎረም በበርሊን ተካሒዷል። መርሐ-ግብሩ በታዳሽ ኃይል፣ በግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ እና በዲጂታላይዜሽን ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎች የተጋበዙበት ነው።

የኢትዮጵያ እና የጀርመን የቢዝነስ ፎረም በበርሊን
የኢትዮጵያ እና የጀርመን የቢዝነስ ፎረም የሁለቱን ሀገራት ኩባንያዎች፣ ከመንግሥት ባለሥልጣናት እና ከልማት ድርጅቶች አገናኝቷል። ምስል፦ Afrika-Verein der deutschen Wirtschaft e. V.

የኢትዮጵያ እና የጀርመን ቢዝነስ ፎረም በበርሊን ተካሔደ

This browser does not support the audio element.

የአሜሪካው ኤክሰለረንት ሶሉሽንስ ኩባንያ በኢትዮጵያ ቢሮ ከፍቶ ሥራ ከጀመረ ገና ጥቂት  ዓመታት ቢቆጠሩም በዓመት ጠቀም ያለው የውጭ ምንዛሪ ለሀገሪቱ ማስገባት የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ኤክሰለረንት ሶሉሽንስ  የሶፍትዌር ኢንጂኔሪንግ ኩባንያ ነው። ኩባንያው የተሰማራበት ቢዝነስ “በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠር አይደለም። ትንሽ ነው” የሚሉት የኤክሰለረንት ሶሉሽንስ የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ መላኩ በሻሕ “ነገር ግን ገቢው ከፍተኛ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

“ከ23 ኩባንያዎች 35 ፕሮጀክቶች ነበሩን። በእነዚህ ውስጥ 292 ኢንጂኔሮች ይሳተፉ ነበር” የሚሉት አቶ መላኩ “በዓመት ከ6 እስከ 7 ሚሊዮን ዶላር በውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ እናስገባለን” ሲሉ አስረድተዋል። ኤክሰለረንት ሶሉሽንስ “በሦስት ዓመት ውስጥ ከ300 ከፍተኛ ግብር ከፋዮች መካከል ተመራጭ” ሆኖ ለሽልማት እንደበቃ የሚናገሩት መላኩ በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ቁጥር ቢጨምር የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ አላቸው።  

አቶ መላኩ በበርሊን ከተማ የተጀመረው የኢትዮጵያ እና የጀርመን የቢዝነስ ፎረም ተሳታፊ ናቸው። ወደ በርሊን ብቅ ያሉት “ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ሀገራቸውን ሳይለቁ እዚያው ሆነው ለጀርመን ኩባንያዎች እንዲሰሩ ዕድል ለማመቻቸት ነው።” የኢትዮጵያ አውትሶርሲንግ ማኅበር ወክለው በስብሰባው የሚሳተፉት አቶ መላኩ በመጀመሪያው ቀን መርሐ-ግብር በኢነርጂ ዘርፍ የተሠማራ ኩባንያ ከሌሎች ተጋባዦች ጋር ጎብኝተዋል።

አራት የኩባንያ መሪዎች የመሰረቱት የኢትዮጵያ አውትሶርሲንግ ማኅበር በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶችን የማስተባበር እና የማገዝ ዓላማ አለው። በአሜሪካ እና አውሮፓ ያሉ ኩባንያዎች ሥራዎቻቸውን ለኢትዮጵያውያን ሰጥተው እንዲያሰሩ ማነጋገር ሌላው የማኅበሩ ዓላማ ነው። በበርሊን ያደረጉት ጉብኝት በቀጥታ ከዚሁ የማኅበራቸው ዓላማ ጋር የተገናኘ ነበር።

የጎበኙት የኢነርጂ ተቋም ኃላፊዎች እንደ ኤክሰለረንት ሶሉሽንስ አይነት ኩባንያዎች ለሚያቀርቡት አገልግሎት “በጣም ፍላጎት” እንዳላቸው ተረድተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በውይይታቸው “ጀርመን ተጋላጭነትን ማስወገድ የምትፈልግ” ሀገር መሆኗን ተገንዝበዋል። የተጀመረው ውይይት ግን በሒደት ወደ ፍሬያማ የሥራ ዕድል ሊለወጥ ይችላል የሚል ዕምነት አላቸው።

አቶ መላኩን ጨምሮ በዘንድሮው የኢትዮጵያ እና የጀርመን ቢዝነስ ፎረም በታዳሽ ኃይል፣ በግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ እና በዲጂታላይዜሽን ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎች ተጋብዘዋል። ከኢትዮጵያ 18 ከጀርመን ከ100 በላይ ኩባንያዎች መጋበዛቸውን ዶይቼ ቬለ ከአዘጋጆቹ ለመገንዘብ ችሏል። የጀርመን አፍሪካ ቢዝነስ ማኅበር፣ የጀርመን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት፣ ኮንራድ አደንአወር ፋውንዴሽን እና የጀርመን ፌድራል የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ሚኒስቴር ያዘጋጁት ነው።

ከስብሰባው አዘጋጆች መካከል አንዱ የሆነው የጀርመን አፍሪካ ቢዝነስ ማኅበር የምሥራቅ አፍሪካ ክፍል ኃላፊ አስማው ኒታርዲ ሁሉም የጀርመን ኩባንያዎች ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከመገኘቷ የዘለለ ዝርዝር መረጃ ላይኖራቸው እንደሚችል ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ስለዚህ አፍሪካን እንደ አንድ ሀገር ለሚያስቡ የጀርመን ኩባንያዎች ኢትዮጵያን ነጥሎ ማስተዋወቅ አንደኛው ዓላማ ነው።

“ኢትዮጵያን እንደ ቢዝነስ መዳረሻ እንዴት ማሳየት እንችላለን? በዚያ ምን አለ?” በሚለው ጉዳይ ላይ ውይይት እንደሚደረግ የገለጹት አስማው ኒታርዲ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለውጭ ኩባንያዎች ስትከፍት የተፈጠረውን ዕድል በፎረሙ ለጀርመን ኩባንያዎች ማስተዋወቅ ሌላው ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በአውሮፓ የግዙፉ ኢኮኖሚ ባለቤት ከሆነችው ጀርመን ኢንቨስተሮችን ለመሳብ በተደጋጋሚ ጥረት ያደርጋሉ። ምስል፦ Rainer Jensen/dpa/picture alliance

ኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት ተዘግተው በቆዩት ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክ ሥራኢነርጂ እና ሎጂስቲክስ የመሳሰሉ ዘርፎች የውጭ መዋዕለ-ንዋይ ትፈልጋለች። በደቡብ ምዕራብ ጀርመን በምትገኘው ሽቱትጋርት ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ፎረም የተዘጋጀ ሲሆን ከኢትዮጵያ የመጡ እንግዶች በበርሊን፣ ብራንደንቡርግ እና ባደን ቩርተምበርግ የሚገኙ ኩባንያዎችን እየተዘዋወሩ ይጎበኛሉ።

“በበርሊንም ይሁን በሌላ ቦታ ያካሔድናቸው እና እነዚህን ኩባንያዎች ያገናኘንባቸው ስብሰባዎች አንዳች ውጤት እንዲያመጡ ሁልጊዜም ተስፋ እናደርጋለን” የሚሉት አስማው ኒታርዲ “ወዲያውኑ፤ ከአንድ ወር በኋላ መሆን አለበት ማለት አይደለም። የተወሰነ ጊዜ ይወስዳል” ሲሉ አስረድተዋል። ይሁንና የኢትዮጵያ እና የጀርመን ኩባንያዎችን በማገናኘት “በዚያ ምን አለ?” “ምን ሊደረግ ይችላል?” በሚሉ ጉዳዮች ላይ ማወያየት አስማው ኒታርዲ እንደሚሉት “በጣም ጠቃሚ የመጀመሪያ እርምጃ ነው።”

የዘንድሮው የሁለቱን ሀገራት ኩባንያዎች ከመንግሥት ባለሥልጣናት እና የልማት ድርጅቶች የሚያገናኘው ዓመታዊ ስብሰባ ዘንድሮ ኢትዮጵያ እና ጀርመን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩበት 120ኛ ዓመት ጋር ተገጣጥሟል።

ጀርመን ከኢትዮጵያ ሸቀጦች በተለይም ቡና እና የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች ትሸምታለች። ኢትዮጵያ በአንጻሩ ከጀርመን ግዙፍ ማሽኖች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ኬሚካሎች እና መድሐኒቶች ትገዛለች። በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና በእርሻ ሥራ የተሰማሩትን ጨምሮ የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የሚገኙ ቢሆንም በገበያው ያላቸው ድርሻ ያን ያክል ትልቅ የሚባል አይደለም።

“የጀርመን ኩባንያዎች አብረዋቸው ቢዝነስ መሥራት የሚችሉ ተዓማኒ አጋር ይፈልጋሉ” አስማው ኒታርዲ የመጀመሪያው “እርምጃ ሁልጊዜም የንግድ ልውውጥ” እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት የጀርመን ኩባንያዎችን ቀልብ ለመሳብ በሚደረጉ ስብሰባዎች እየተገኙ ሀገሪቱ ልታቀርብ የምትችለውን የመዋዕለ ንዋይ እና የገበያ ዕድል ባለፉት ዓመታት ሲያብራሩ ቆይተዋል። በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በስብሰባዎቹ የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያግባቡት የመንግሥት ባለሥልጣናት ብቻ ነበሩ። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን የግሉን ዘርፍ የሚወክሉ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች መሳተፍ ጀምረዋል።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጀርመንን ጨምሮ የአውሮፓ ኩባንያዎችን ገንዘብ፣ እውቀት እና ልምድ አጥብቀው ቢፈልጉም ሀገሪቱ የገጠማት የቀውስ አዙሪት ግን ለኢንቨስትመንት የሚመች አይደለም። በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሔደው ጦርነት ግጭት በማቆም ሥምምነት ቢገታም በተፈራራሚዎቹ መካከል የተፈጠረው መቃቃር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የሚካሔዱ ግጭቶች የውጭ ኩባንያዎችን እና ባለወረቶችን የሚያሸሹ ናቸው።

በበርሊን በሚካሔዱ የቢዝነስ ፎረሞች ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የጀርመን ኩባንያዎች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ሲያግባቡ ቆይተዋልምስል፦ Eshete Bekele/DW

የጀርመን አፍሪካ ቢዝነስ ማኅበር የምሥራቅ አፍሪካ ክፍል ኃላፊ አስማው ኒታርዲ “ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ሥጋት ያለው ከባቢ የላትም” ሲሉ የሀገሪቱ የፖለቲካ እና የጸጥታ ሁኔታ ለንግድ እና ኢንቨስትመንት አመቺ እንዳልሆነ ተናግረዋል። የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ግጭት በማቆም ሥምምነት ቢገታም “እስካሁን ድረስ አካባቢያዊ ግጭቶች እና ከጎረቤት ሀገር ጋር ጭምር ፖለቲካ ውጥረቶች አሉ” ሲሉ አስረድተዋል።

ይሁንና የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ በዓለም ባንክ እና ጀርመንን በመሳሰሉ የሁለትዮሽ አጋሮች ድጋፍ ተግባራዊ የሚያደርገው ማሻሻያ እና “ከቀጠናዊ አማካኝ በላይ” የሚያድገው ኢኮኖሚ ለጀርመን ኩባንያዎች ዕድል ሊሆኑ እንደሚችሉ ያምናሉ። “ለኩባንያዎች ይህ ማለት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዕድል ያለባት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ተጋላጭነትም ያላት ሀገር መሆኗን ያሳያል” ሲሉ ተናግረዋል።

ዶይቼ ቬለ በበርሊን በመካሔድ ላይ በሚገኘው ስብሰባ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም። አስማው ኒታርዲ ግን የጀርመን ኩባንያዎች “በሥራ ፈጠራ፣ በኢንቨስትመንት እና በእውቀት ሽግግር” ለኢትዮጵያ መረጋጋት “በተወሰነ መንገድ” የራሳቸውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ያምናሉ።

ጀርመን የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት የተፈራረሙትን ግጭት የማቆም ሥምምነት አተገባበር እና በግጭት የተጠቁ አካባቢዎችን ለማረጋጋት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ላይ እንደምትገኝ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሔዱ “ፖለቲካዊ ግጭቶችን ለማሸማገል እየረዳች” መሆኑን መሥሪያ ቤቱ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረበትን 120ኛ ዓመት በማስመልከት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የአውሮፓ ትልቁ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ጀርመን ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ሰብአዊ ርዳታ ከሚሰጡ ሀገራት መካከል ትገኝበታለች።

አርታዒ ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW