1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቅዱስ ፓትርያርክ ዐቡነ ማትያስ መልዕክት

ሰኞ፣ የካቲት 25 2016

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ዐቡነ ማትያስ በ11ኛው ዓመት ሲመተ በዓላቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት "በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ የግል ፍላጎትና ዓላማ ለማስፈጸም መሞከር ፍጹም ስሕተት እና ተቀባይነት የሌለው ነው" ሲሉ አሳሰቡ።

ቅዱስ ፓትርያርክ ዐቡነ ማትያስ ንግግር ሲያደርጉ
ፎቶ ከማህደር: ቅዱስ ፓትርያርክ ዐቡነ ማትያስ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡምስል Seyoum Hailu/DW

የቅዱስ ፓትርያርክ ዐቡነ ማትያስ መልእክት

This browser does not support the audio element.

"መንግሥት ለቤተክርስቲያን የሕግ ከለላና ጥበቃ እንዲያደርግ" የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ዐቡነ ማትያስ ተናገሩ። ቅዱስ ፓትርያርኩ በ11ኛው ዓመት ሲመተ በዓላቸው ላይ ባስተላለፉት መልእክት "በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ የግል ፍላጎትና ዓላማ ለማስፈጸም መሞከር ፍጹም ስሕተት እና ተቀባይነት የሌለው ነው" ሲሉ ለፖለቲከኞች መልእክት አስተላልፈዋል። በሀገሪቱ እና በቤተክርስቲያን ላይ ያለው ድባብ "እጅግ በጣም አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ለማንኛችንም ግልፅ ነው" ያሉት ዐቡነ ማትያስ "አንዱን በመደገፍ ሌላውን በመንቀፍ፣ ወደ አንዱ ተለጥፎ ሌላውን ዘልፎ መናገር" ተገቢ አለመሆኑንም ለሃይማኖት አባቶች ባስተላለፉት መልእክታቸው ላይ ገልፀዋል። ፓትርያርኩ የዘመኑ ትውልድንም ተችተዋል። 


የፓትርያርኩ መልእክት አንኳር ጭብጦች


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ዐቡነ ማትያስ ትናንት የካቲት 24 ቀን 2016 ዓ.ም ቤተ ክርስትያኗ "በዓለ ሲመተ ክህነት" በሚል ባዘጋጀችው መርሐ ግብር ላይ የፓትርያርክነት መንበርን የተቀበሉበትን 11 ኛ ዓመት መነሻ አድርገው መልእክት አስተላልፈዋል።


ፓትርያርኩ "ሁሉም ሰው ወደ እግዚአብሔር መመለስ ይገባዋል" ያሉ ሲሆን ስለ ትውልዱም ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

"ያለንበት ዘመን ለእግዚአብሔር ክብርን የነሣ፤ ከፍቅርና ከአንድነት የራቀ፣ ራስ ወዳድነትና በቃኝ አለማለት የወረረው፤ በዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ የተዋጠ ትውልድ የታየበት ዘመን ነው" ብለዋል።


አክለውም "የዘመናችን ትውልድ ከተግባር ይልቅ አስመሳይ ሆኖ መታየትን፣ ከቅድስና ይልቅ ነውረ ኃጢአትን፤ ከትሕትና ይልቅ ትዕቢትን የተለማመደ፣ ለሃይማኖትም ሆነ ለማኅበረ - ሰብ ጤናማ ህላዌ ያልተመቸ ትውልድ እንደሆነ በግልጽ የሚታይ ነው" በማለት አዝማሚያው አደገኛ እንደሆነ ገልፀዋል። 


የሃይማኖቱ አባቶች "የእውነት፣ የፍትሕ፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የዕርቅ፣ የይቅርታ፣ የአንድነትና የስምምነት ጠበቃ መሆናችንን ማሳየት ነበረብን" የሚለውን በመልእክታቸው ያሰፈሩት ቅዱስ ፓትርያርኩ "በዓለሙ ብልሹ አሰራርም ተሳታፊ ከመሆን አላመለጥንም" ሲሉም ገልፀዋል።


የቤተ ክርስትያኗ የመንበረ ፓትርያርክ የሕዝብ ግንኙነት የሕትመትና ሚዲያ ዋና ክፍል ኃላፊ መምህር ዶክተር አካለወልድ ተሰማን ስለ መልእክቱ ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቀናቸዋል።


"አጠቃላይ ለቤተ ክርስትያኒቱ አባላት፣ ለሁሉም ምእመናን፣ ለብፁዐን ዐበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ እንደዚሁም ለመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጠንካራ መልእክቶችን ነው ያስተላለፉት"


በቤተ ክርስትያኗ ጉዳይ መንግሥት ጣልቃ ይገባል ስለመባሉ


ብፁዕ ዐቡነ ማትያስ ፓለቲከኞች ባልተፈቀደላቸው፣ የተቋቋሙበት ሕገ መንግሥት እንኳ የማይፈቅድላቸውን 'በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ የግል ፍላጎትና ዓላማ ለማስፈጸም" መሞከራቸውንና ይህም ፍጹም ስሕተት፤ ተቀባይነትም የሌለው እንደሆነ ተናግረዋል።


"ሁሉም ድንበሩን ጠብቆ በጋራ ጉዳዮች ላይ በፍቅርና በመከባበር ተመካክሮና ተግባብቶ መስራት ያሻል፤ በዚህ መንፈስ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት ተናበው ቢሰሩ በሀገር ላይ ሰላም ይሰፍናል፣ ልማት ይፋጠናል፣ ዕድገት ይመዘገባል" የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።
በቤተክርስቲያን ላይ "እጃቸውን እየዘረጉ የሚገኙ ሁሉ" እጃቸውን እንዲያነሡ እና "መንግሥትም ለቤተክርስቲያን የሕግ ከለላና ጥበቃ እንዲያደርግም መጠየቃቸውን መምህር ዶክተር አካለወልድ ተሰማ ገልፀዋል።
በፕትርክና ዓመቱ "በየአካባቢው መብቱ ተነፍጎ በቀየው እንዳይኖር በልዩ ልዩ ምክንያት እየተፈናቀለ ያለውን ሕዝብ ለማጽናናትና ለመደገፍ በአንድነት መቆም ይገባል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከአንድ ወር ገደማ በፊት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ተከልክለው ወደ አሜሪካ እንዲመለሱ መደረጉን ቤተ ክርስትያኗ አስታወቀች። ምስል Seyoum Hailu/DW

 

የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ መከልከል

ቅዱስ ፓትርያርኩ መንግሥት በቤቱ ክርስትያኗ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ መሆኑን በተመለከተ ላነሱት ሀሳብ የመንግሥትን ምላሽ ለማካተት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የውጭ መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ኃላፊ ቢለኔ ስዩም እና የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ ብንደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11 ሃይማኖት እና መንግሥት የተለያዩ መሆናቸው፣ በአንቀጽ 27 ደግሞ ሰዎች የሃይማኖት፣ የእምነት እና የአመለካከት ነፃነት እንዳላቸው እና ጉዳዩ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ እንደሆነ ተደንግጓል።  

ሰለሞን ሙጬ
ልደት አበበ
ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW