1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በጀርመናዊትዋ እይታ

ሐሙስ፣ ኅዳር 16 2014

በኢትዮጵያ ከፈጠራ ኢንዱስትሪዉ ከተውጣጡ ወጣት ስራ ፈጣሪዎች ጋር በአማካሪነት እየሰራሁ ነው። በፍርሃት እኔ ስራዬን ባቆም፤ ወጣቶቹን ያለምንም ምክንያት በማያቁት ነገር መተዉ ይሆናል። በእነዚህ አገሮች ውስጥ ያለው ወጣት ትውልድ በስራ የመበልፀግ ሂደት ላይ እና በሰላም የመኖር ሁኔታን የተላመደ ነዉ።

Beate Wedekind
ምስል Privat

ቤአተ ቬደኪንድ፤ ኢትዮጵያን ወዳጅዋ ጀርመናዊት

This browser does not support the audio element.

 

በኢትዮጵያን ከአርባ አምስት ዓመታት በላይ ጀምሮ በቅርበት የምታቃት በተለይ ደግሞ ወጣት ኢትዮጵያዉያንን በመርዳት በኢትዮጵያ እዉቅናን ያገኘችዉ ጋዜጠኛ ቤአተ ቬደኪንድ፤ ስለወጣት ኢትዮጵያዉያን ስራ ፈጣሪዎች መናገርን ትወዳለች። ቤአተ ቬደኪንድ በጀርመን ታዋቂ የሆነዉ መጽሔት «ቡንት» ዋና አዘጋጅ፤ በጀርመን ታዋቂ ሰዎች ሰዎች ሽልማት የ«ባንቢ» እና የ«ጎልደን ካሜራ» መድረክ፤ ዋና አዘጋጅ ሆና ከፍተኛ እዉቅናን ያገኘች ጋዜጠኛ ነች። ታዋቂዋ ጀርመናዊት ጋዜጠኛ ቤአተ ቬደኪንድ ባለፈዉ ሳምንት «The Pioneer» በተሰኘዉ በጀርመን የዜና አገልግሎት ላይ ቀርባ  ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ ሰጥታ ነበር።  በዚህ ዝግጅታችን ይህንን ቃለ ምልልስ ጨምቀን ይዘን ቀርበናል።

ምስል Privat

ዘ ፒዮኔር የተባለዉ፤ የዜና አገልግሎት ክፍል ለቤአተ ቃለ ምልልስ ከመጀመሩ በፊት ጋዜጠኛዋ አድማጮችዋና በሃሳብ ወደ ኢትዮጵያ እንዲህ ስትል ነበር የወሰደችዉ።

ዛሬ እይታችንን በማስፋት ወደ አፍሪቃ አህጉር ማለትም ወደ በአፍሪቃ ቀንዷ ሀገር ኢትዮጵያ እንጓዛለን። ስለ ኢትዮጵያ ምን ያህል እናውቃለን? ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን እናቃታለን? ዛሬ በጦርነት ላይ ስለምትገኘዉ ኢትዮጵያ በደንብ ከምታውቀው ሴት ጋር  ቃለ- ምልልስ ይዘናል። ቤያተ ቬደኪንድ ትባላለች ። እንኳን ደህና መጣሽ ቤአተ፤ እስቲ ስለራስሽ ስለ ኢትዮጵያ ትንሽ ንገሪን።

«በደስታ፤ በቃለ ምልልሳችን መጀመርያ አንድ የምኮራበትን ነገር መናገር እፈልጋለሁ። ደስተኛ የ 70 ዓመት አዛዉንት ነኝ። ኢትዮጵያን የተዋወኩት ከዛሬ 45 ዓመት በፊት ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ በጀርመን ልማት አገልግሎት የባንክ ፀሐፊ እና የሎጂስቲክስ ረዳት ሆኜ ሰርቻለሁ። በዚያ ወቅት ሥልጣን ላይ የነበሩት ኮሚሲስቶቹ ነበሩ። ኢትዮጵያ ዉስጥ በተቀጠርኩበት ሥራ ለዓመታት ካገለገልኩ በኋላ ነዉ። በ 30 ዓመቴ ነዉ ጋዜጠኛ የሆንኩት። በ 36 ዓመቴ ዋና አዘጋጅ፤ በ 42 ዓመቴ አርታኢ ሆኛለሁ። የቴሌቪዥን ዋና አዘጋጅ ሆኜም አገልግያለሁ። ሌሎችም ብዙ ነገሮችን ሰርቻለሁ። ከዝያም 55 እና በ60 ዓመት ሲሞላኝ፤ አዲስ ህይወትን ጀመርኩ። ይህ ማለት ያለኝ እዉቀት በወጣት ኢትዮጵያዉያን ዘንድ ሚዛን ደፍቶአል።»  

ምስል Privat

ስለ ኢትዮጵያ እናውራ። በአሁኑ ጊዜ በሃገሪቱ እየሆነ ያለው ነገር በጣም ከባድ ነው። ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜያት ትመላለሽያለሽ። ረዘም ላሉ ጊዜያቶች ኖረሻል። አሁንም እዝያዉ ትኖርያለሽ። ስለኢትዮጵያ ያለዉን ሁኔታ በደንብ ማስረዳት የሚችል ሰዉ በማግኘታችን እድለኞች ነን። ኢትዮጵያ ዉስጥ ምን እየሆነ ነዉ ያለዉ?    

«በመጀመርያ ሥልጣኑን ያጣ አንድ ብሔር እንደገና ሥልጣንን ለማግኘት ከሌላዉ ብሔር ጋር ጦርነት ዉስጥ የገባት ብሎም ስልጣናቸዉን ያጡት ሰዎች ስልጣንን ለማግኘት ዉግያ ላይ መሆናቸዉን መግለፅ እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ተመሳሳይ አይነት ሁኔታ ሲከሰት ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑን በደንብ አዉቃለሁ። የኮሚኒስት ሥርዓትን ሲያራምዱ በነበሩት ዘመን እዝያዉ ነበርኩ። ከዝያም በመቀጠል በተነሳዉ አብዮትም ወቅት እዝያዉ ነበርኩ። አሁንም ተመሳሳይ አይነት ሁኔታ ዳግም ሲከሰት እዝያዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነኝ። አሁንም ቀድሞ ስልጣን ላይ በነበሩ ግለሰቦች እና በመንግሥት መካከል የተቀሰቀሰ፤ ሕዝብ መስዋእት የሆነበት ዉዝግብ ነዉ። ኢትዮጵያ አሁን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዉስጥ ትገኛለች። ምክንያቱም በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰዉ ጦርነት፤ አዉዱን እያሰፋ በመሆኑ ነዉ። በግጭቱ ሆነ ተብሎ ገንዘብ ተከፍሎአቸዉ ቀዉስን የሚያባብሱ፤ ሰላማዊ ሰዎችን የሚገድሉ፤ ሴቶች የሚደፍሩ፤ ወጣት ታጣቂዎች አሉ። ለዚህ ወንጀል ተጠያቂ ያልሆኑ ሰዎች፤ ይወነጀላሉ። በዚህም ትክክለኛ ሰዎች አለመሆናቸዉን አስረግጪ እናገራለሁ። ምክንያቱም  ከአካባቢዉ መረጃን የማገኝበት ጥሩ አዉታረ-መረብ ስላለኝ እና በኢትዮጵያ አሁን ስላለዉ ሁኔታ ጥሩ ግንዛቤ ስላለኝ ነዉ።»  

ምስል Privat

እስቲ በደንብ አስረጅን። በርግጥ ነገሩ ዉስብስብ ሊሆን ይችላል። የትኛዉ ፓርቲ ከየትኛዉ ፓርቲ ጋር ነዉ ቅራኔ የተፈጠረዉ ?  

«ግጭቱ አሁን በዲሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጡ የ 44 ዓመት ጎልማሳ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ቀደም ሲል የፓርቲ አባል በሁኑት በአሁኑ ጠላቶቹ መካከል ነው። ፓርቲዉ ህወሓት ይባላል። ለ 28 ዓመታት የኢትዮጵያ ዋንኛ ገዥ ፓርቲ ነበር። ፓርቲዉ በአሁኑ መንግሥት አስተዳደር ዉስጥ የለም። ምክንያቱም ከፓርቲዉ መካከል አንዱ፤ ሃገሪቱን በጥንካሪ መምራት ባለመቻሉ ስልጣኑን በገዛ ፈቃዱ በመልቀቁ ነዉ። እና የያኔዉ የ 42 ዓመት ጎልማሳ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ በሃገሪቱ እስከሚቀጥለዉ ምርጫ፤ በምክር ቤቱ  ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ተሾመ። አሁን በቅርቡ በኢትዮጵያ ዴሞክራስያዊ ምርጫ ተካሄዶ በድጋሚ ተመርጦአል። የቀድሞ የሃገሪቱ ገዥ የነበረዉ ፓርቲ ባለሥልጣናት ይቅርታ ይደረግልኝና፤ አንዳንዶቹን በደንብ አዉቃቸዋለሁ፤ ለማመን ይቸግራል እስከ ከእግር ጥፍራቸዉ በሙስና የተዘፈቁ ነበሩ። እነዚህ ሰዎች በሱ ስር መተዳድርን አልወደዱም። 

ለምን እዉነታዉ ምንድነዉ እዚህ ላይ?

«እዉነታዉ የመጨረሻዉ ለዉጥ ወይም አብዮት በታየበት በጎርጎረሳዉያኑ 1991 ዓመት የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ገና ተማሪ ነበር።  ኮሚኒስቶቹን ከስልጣን ለማዉረድ በተደረገዉ ትግል አዲስ አበባ ከተማ ላይ መንገድ ላይ ተቆጣጣሪ በመሆን ረድቶአል። ዐቢይ በዚያን ጊዜ ትንሹ ተማሪና አብዮተኛ ነበር። በመቀጠል የከፍተኛ ትምህርቱን አጠናቋል። በወታደር ቤትም ነበር። 32 ዓመት ሲሞላዉ፤ የኢትዮጵያ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆኖ ተሾሞአል። ምክንያቱም ፈጣን፤ አስተዋይና ብልህ ወጣት በመሆኑ ነበር። ዐቢይ ትምህርቱን በመቀጠለ ተማረ። በኋላ በ 2018 በገዛ ፈቃዳቸዉ ስልጣን የለቀቁትን ጠቅላይ ሚኒስትርን ለመተካት ከተመረጡት ሦስት እጩዎች አንዱ ሆኖ ቀርቦም ነበር። ከዝያም በፓርላማዉ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን ተመረጠ። ሌሎቹ ግን አሁን ጠላቶቹ ሆነዋል።»   

አብረዉት የነበሩት የቀድሞ ገዥ ፓርቲ አባልት ናቸዉ?

ምስል Collection Rolf Heyne

«የቀድሞዉ የገዥ ፓርቲ አባላት ናቸዉ። ለዐቢይን እዉቅና አልሰጡትም። ምክንያቱም ምኞታቸዉ በእጩነት የቀረቡት ሌሎች እንዲመረጡ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በጠላትነት መተያየት ተጀመረ። ከዛም ዐቢይ ከብዙ ዓመታት በኋላ፤ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል እርቅ በማዉረዱ የሰላም ኖቤልን አሸነፈ። ሌላዉ የካቤኔዉን 50 በመቶ ሴቶች በማድረግ አድርጎ ሾሞአል፤ የፖለቲካ እስረኞችን ለቆአል፤ የመንግሥት ተቃዋሚ የነበሩ ፖለቲከኞችን ወደ ሃገር ቤት መልሶአል። ወጣቱ ፖለቲከኛ ትክክለኛ እርምጃን አካሂዶአል። በዝያን ጊዜ 43 ዓመቱ ነበር። ሌሎቹ ምን እየሆነ ነዉ? ይህ ሰዉ ከኛ የወጣ አይደል እንዴ፤ መቀጠል የነበረበት እንደነበረዉ ነዉ ብለዉ ነበር የሚያዩት።» 

ማለት የተንሰራፋ ሙስና እንዲቀጥል ነዉ?

«እነሱ በስልጣን በነበሩበት ጊዜ ሲሰራ እንደነበረዉ በወንገንተኝነት ስራዉ እንዲቀጥል ነበር። የትግራይ ባለስልጣናቱ፤ ከ110 ሚሊዮን ከሚሆነዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አምስት ሚሊዮን ከሚሆነዉ አካባቢ የመጡ ናቸዉ። በሁሉም የኢትዮጵያ የግጭት ታሪኮች በዋነኝነት ተዋጊዎች እኛ  ነን ይላሉ ሲልም ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቦአል። ሁሌም ቢሆን በጦርነት አንደኞች ነን ሲሉ ይናገራሉ። መጀመርያ ላይ የተደረገዉን የተኩስ አቁም ጥሪ አልተቀበሉትም። ዐብይ አሕ መድ በኮሮና ምክንያት ምርጫዉን እናራዝማለን ሲል ግጭቱ እየተባባሰ መጣ።» 

ምስል Privat

እዚህ በበርሊን በሚካሄድ ምርጫ እንኳ በኮሮና ሰዓት ምርጫን ማስተናበር ከባድ ነዉ። ስለዚህ የኢትዮጵያን ችግር እረዳለሁ።

«ለዚህም ነዉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ የነበረዉ ህወሓት፤የማዕከላዊዉን መንግሥት ዉሳኔ ባለመቀበል  እኛ በክልላችን ምርጫ እናደርጋለን ሲሉ ወስኑ። ይህ ማለት በርሊን ያለዉ ማዕከላዊዉ መንግሥት፤ ምርጫ አይካሄድም ብሎ ሲወስን፤ ባቫርያ ያለዉ ክልላዊ መንግሥት፤ ምርጫ እናካሂዳለን ብሎ ምርጫን ማካሄድ እንደማለት ነዉ። የፈለጉትንም አደረጉ። ከዝያ ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያኑ 2020 ጥቅምት 4 ለጥቅምት 5 አጥብያ፤ በትግራይ የሚገኝዉን የሃገሪቱን  ብሔራዊ ጦር፤ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን፤ በስለት ወግተዋል፤ ገድለዋል፤ አቆስለዋል፤ መሰሪያዎቻቸዉንም ሰርቀዋል። ይህን ያደረጉት ሰዎች፤ ብሔራዊዉ የሃገሪቱ ጦር ወግቶናል ሲሉ ከሰዋል። እዉነታዉ ግን ይህ አይደለም። እዉነታዉ የብሔራዊ ጦሩን መሳርያ ሰርቀዋል። ይህ የዉሸት ዜና ሳይሆን እዉነተኛ ታሪክ ነዉ። የተረጋገጠም ነዉ። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዉ ድርጅት፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይህንኑ ዜና አንድ በአንድ አረጋግጦአል። እናም እነዚህ የቀድሞ ባለሥልጣናት እና የሃገሪቱን ስልጣን መልሰዉ እንደማያገኙ ያወቁት እና ነገሩን መረዳት ያልፈለጉት ሰዎች፤ ለወረራ ወደ አዲስ አበባ እንሄዳለን ሲሉ ተነሱ።»  

ምስል Privat

ይህ የውሸት ዜና አይደለም ብለሽ ተናግረሻል። ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ ወስደን፤ ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ የሚሰጠዉን የዜና ሽፋን እንመልከት። ሁኔታዉ እዉነታዉን ለመዘገብ ምን ያህል  አመች ነዉ?  

«በጣም የሚነገርመዉን ነገር ልናገር። ቀውሱ ከጀመረ አንድ ዓመት ሆኖታል። የመንግስት ለውጥ የተካሄደዉ በጎርጎረሳዉያኑ 2018 ነዉ። አዲሱ መንግስት እራሱን ለማቋቋም እና ከነበሩት ሰዎች ለመለየት ሁለት ዓመት ነበረዉ።  ግን አሁን ስለ ኢትዮጵያ የሚጽፉት ጋዜጠኞች ሁሉ እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ግንኙነት ያላቸዉ፤ ለ28 ዓመታት በመንግስት ስልጣን ላይ ከነበሩት ሰዎች ጋር እንጂ አዲስ ከተመሰረተዉ መንግስት ባለስልጣናት ጋር አይደለም። ስለዚህ አሁንም ትልቅ የመረጃ ፍሰት የሚመጣው ከአሮጌው ወይም ከተሻረዉ ፓርቲ ባለስልጣናት ብቻ ነው። ይህ ደግሞ በመረጃ የሚረጋገጥ ነዉ። ስለዚህም የሚጻፈዉን ሁሉ፤ እነሱ ትክክል እንደሆኑ በሚመስል መንገድ፤ ይተረጎማል። የቀድሞ የፓርቲ አባላት ለምን ዐብይ አሕመድ በአስተዳደር እና በመሳሰሉት ውስጥ ብዙ ሰዎችን ይለዋዉጣል ሲሉም አልተቀበሉትም። በይፋ እንደተናገሩት በዋሽንግተን ተሰብሰበዉ ይህን ሰዉ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቀበለዉም ብለዋል። እኛም አንቀበልም፤ የተኩስ አቁሙ ሕጋዊነቱንም አንክተለም ነዉ ያሉት» 

በሕጋዊ ምርጫ የተመረጠ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆንም?

ምስል Privat

«አዎ፤ በሌላ በኩል በዉሸት የሚሰራጨዉ ዜና እጅግ ከባድ ሆንዋል። ህወሓት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የትዊተር አባልነት ገፅን በመክፈት ሰዎች በቲዊተር ገፃቸዉ ዜናውን እንዲያሰራጩ ገንዘብ የሚከፍል መሆኑ ተረጋግጧል። ይህ የትዊተር ገጽ እጅግ ብዙ ስለሆነ የትኛዉ ትክክለኛ፤ የትኛዉ ሃሰተኛ መረጃ መሆኑን መለየት አስቸጋሪ ሆንዋል። በዚህም ምክንያት፤ የመንግሥት መግለጫ ተብሎ በጋዜጠኞች የሚወጣዉን መረጃ፤ አንዳንድ ጊዜ እዉነት ነዉ ብሎ መቀበል ያስቸግራል። በዚህም ምክንያት፤ እንደማንኛዉም ጋዜጠኛ፤እኔም እንደማደርገዉ፤ ጉዳዩን ለማወቅ ራሱ ጋዜጠኛዉ፤ መመርመር እና ማግኘት ይፈልጋል። ይሁንና አሁን፤ ሰሜን ኢትዮጵያ ባለዉ ጦርነት ምክንያት፤ ሁኔታዉ ይህን ለማድረግ አይፈቅድም።» 

እና እንዴት ነዉ ታድያ የታወቀዉ?

«ውጤቱ ለወራት በዘገባዎች እንደሰማነዉ፤ ተፋላሚ ሃይላት አንዱ ሌላኛዉን ሲከስና ራሱን ነፃ እያደረገ ነዉ። በጦርነቱ በርግጥ ሴቶችን ማን መደፈር እንደጀመረ፤ ማንም አያውቅም? የርዳታ አቅርቦቶች ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ መድረስ እንዳይችሉ ያደረገዉ ማን ነው? መንግሥት እንደገለፀዉ፤ መጀመሪያ ላይ ለምግብ አቅርቦት እንዲሆን ገንዘብ ሰጥተናል ብሏል። ከዝያም የርዳታ እህል ጭነት መኪናዎች ተዘርፈዋል። በደል ደርሶአል፤ የጦር መሳሪያ በርዳታ ጭነት ማጓጓዣ መጫናቸዉ፤  በፎቶ ማስረጃ ተረጋግጦአል። ነገር ግን ይሄ መረጃ በ CNN አልተዘገበም፤ አልታየምም። እዉነቱን ለመናገር እኔ እዚህ ላይ ወገንተኛ ነኝ። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉኝ ጓደኞቼ፤ በወያኔ መንግስት የ 28 ዓመታት አገዛዝ፤ ለፍርድ ሳይቀርቡ ታስረዋል። ራሱ በሙስና መከሰስ ያለበት ህወሓት ሳይከሰስ እነሱ በሙስና ተከሰዋል፤ በዚህም ምክንያት ወገንተኛ ሆኛለሁ። እናም በህወሓት ስልጣን ዘመን በተለይም በመካከለኛው ሕብረተሰብ ዘንድ የነበረዉን ስቃይ መናገርና መገመት እጅግ ያስቸግራል።»   

እኛ፣ የልማት ፖሊሲን ለምንከተል ሙሉ ምስሉ ምን ይመስላል? በአንቺ እምነት፣ ከውጭ ሆነው ኢትዮጵያን መደገፍ ለሚፈልጉ በቅድምያ አሁን መጀመር ያለብት ምንድን ነው ትያለሽ?

«በመጀመሪያ ደረጃ በእነዚህ ሁለት ተፋላሚ ወገኖች መካከል ንግግሮች እንዲኖሩ ፖለቲካዉ ሁሉንም ነገር ማድረግ ይኖርበታል። እና አሁን ከሁለቱም ወገን እንደምንሰማዉ ለሰላም ቆምያለሁ፤ ለሰላም ያቀረብኩት ጥሪ ተቀባይነት አላገኘም የሚል ነዉ። ስለዚህ አሁን በቅድምያ የሚያስፈልገዉ የሰላም ድርድሩን የሚያስጀምር ነዉ። ለዚህም አሁን አንድ አፍሪቃዊ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የሰላም ድርድር እንዲያስጀምሩ መቀመጫውን አዲስ አበባ ባደረገው የአፍሪቃ ህብረት ተወክለዋል።  ባለሥልጣኑ በአፍሪቃዊ መፍትሄቸዉ በሚቀጥሉት ቀናት ሊያሳኩት ይችላሉ። እንደኔ አስተያየት እና እንደኔ ተሞክሮ ለዓመታት በተለያዩ መንግሥታት ሥር ያገለ ግለሰብን መተዉ እና አለመቀበል አይገባም»  

ግን እንዴት ነዉ አለመተዉ አለማሳዘን የሚቻለዉ?  

ምስል Privat

«አፍጋኒስታንን በምሳሌነት ልጠቅስእችላለሁ። የፌደራል ጀርመን የልማት ትብብር ሚኒስትር ጌርድ ሙለር ሁሌም በሚሰጡት ቃለ ምልልስ አፍጋኒስታን ውስጥ ልማታዊ ሰራተኞች እና ከሲቪል ህዝብ ጎን የሚቆሙ የርዳታ ሰዎች ሁሉ፤ ሃገሪቱ ዉስጥ መቆየት አለባቸዉ ይላሉ። እስካሁንም በአፍጋኒስታን ይህ ተፈፃሚ ሆንዋል። ኢትዮጵያ ዉስጥም ይህ ተግባራዊ ይሆናል። መንግሥታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ የርዳታ ድርጅቶች ሃገሪቱን ለቀዉ መዉጣት የለባቸዉም፤ በአሁኑ ወቅት ጦርነቱ ሰሜን ኢትዮጵያ እና ጥቂት ቦታዎች ላይ ምዕራብ ኢትዮጵያ ላይም ይታያል። የዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎዉ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ የትግራይ ኃይላት ሴቶችን እንደደፈሩ በርግጥም ዘገባዉን ይፋ አድርጎአል። እኔ አሁን መናገር የምችለዉ፤ እኛ መስራት የምንችለዉን ነገር ነዉ። ለምሳሌ እኔ በኢትዮጵያ ከፋሽን እስከ ጨርቃጨርቅ፣ ፊልም እና ሙዚቃ ላይ ከፈጠራ ኢንዱስትሪዉ ከተውጣጡ ወጣት ስራ ፈጣሪዎች ጋር በአማካሪነት እየሰራሁ ነው። በፍርሃት እኔ ስራዬን ባቆም፤ ወጣቶቹን ያለምንም ምክንያት በማያቁት ነገር ሜዳ ላይ መተዉ ይሆናል። በሌላ በኩል ስለስደት ምክንያቶችም እንናገራለን። በእነዚህ አገሮች ውስጥ ያለው ወጣት ትውልድ በስራ የመበልፀግ ሂደት ላይ እና በሰላም የመኖር ሁኔታን የተላመደ ነዉ። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የቀድሞ የመንግስት ባለስልጣናት፤  በጎሳ ግጭት ሀገሪቱን በማተራመሳቸዉ ሃገሪቱን በአንዴ ጥለዉ መዉጣት፤ የስደት መንስኤ ይሆል» 

 ይህ ማለት የአንድን ህብረተሰብ የዴሞክራሲ እና የዘመናዊነት ሂደቶች እንዲሁም ተጨባጭ ሁኔታዎችን በተመለከተ የወደፊት ጉልበት ሞተሩ ወጣቱ ትውልድ ነዉ?

«በትክክል! በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር ዉስጥ ትልቅ የትምህርት ውጥኖች ነበሩ። የጀርመን ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ባለፉት 20 ዓመታት አስራ አንድ ዩኒቨርሲቲዎችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ገንብቷል። በሺዎች የሚቆጠሩ ጥሩ የተማሩ፣ ለማወቅ የሚጥሩ፣ ማህበራዊ እና ፍትሃዊ አስተሳሰብ ያላቸው ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች አሉ። እነዚህ ወጣቶች ጥንካሬ እንደሚሰማቸው እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል። ኮሮና እንኳ፤ በድንገት ሰዉ መስራት መገናኘት እና ማምረት መፍጠር እንዳይችል አደናቅፎአል። እናም አሁን ደግሞ፤ በቀድሞው እና በዛሬው መንግስት መካከል በብሔር ደረጃ በተፈጠረው ግጭት፤ ወጣቱ ችላ ሊባል አይገባም። ይህ ሊሆን የማይችል ነገር ነዉ። በፍፁም አይደረግም። በአውሮጳ ኮሚሽን እና ከአሜሪካ ለኢትዮጵያ የሚሰጠዉ እርዳታ ለጊዜ ዉ ተይዞአል፤ ይህ እንዲለቀቅ በተፋላሚ ኃይላት መካከል ድርድር ሊጀመር ይገባል። የሚታየዉ ጥቃት ሊቆም ይገባል። ደኅዉ ህብረተሰብ ርዳታን ሊያገኝ ይገባል። በአገሪቱ ውስጥ በተለይ ደግሞ በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ረሃብ አለ። በሰላም ጥረቱ ላይ ሊሰራ ይገባል። በኢንተርኔት እና በፌስቡክ እንዲሁም ጎግልን በመጠቀም ዓለም አቀፍ አድማሳቸዉን ያሰፉ፤ በተለይ ከ25 እስከ 35 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙትን ወጣቶች ልንተዋቸዉ አይገባም።»     

ምስል Privat

ኢትዮጵያ ውስጥ መቼና ስንት ጊዜ ነዉ የምትኖሪዉ? ጊዜሽን እንዴት ነዉ ከፋፍለሽ ኢትዮጵያ የምትሄጂዉ?

«በርግጥ ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈዉ ኢትዮጵያ ውስጥ ነዉ። በስፔንዋ ደሴት ኢቢዛ ውስጥም ብዙ ኖሬያለሁ። ኮሮና ያዘኝ እና   ለ14 ወራት የትም ሳልጓዝ ኢቢዛ ተቀምጫለሁ፤ በአንድ ቦታ እንዲህ ስቀመጥ በህይወቴ ለመጀመርያ ጊዜ ነዉ። በርሊን መኖርም እወዳለሁ፤ እና በመሠረቱ አምስት ወር ኢትዮጵያ ውስጥ ሶስት ወር በርሊን ስምንት ሆነ ማለት ነዉ አራት ወራት ኢቢሳ ተቀምጫለሁ። የመኖርያ ጊዜዬ መርዘምና ማጠር የሚወሰነዉ ከያዝኩት ሥራና ፕሮጀክት ነዉ» 

«ከሚቀጥለዉ የጎርጎረሳዉያን ዓመት ጀምሮ ዋና መኖርያዬ አዲስ አበባ አድርጌ እመርጣለሁ። በጎርጎረሳዉያኑን 2022 ዓመት ውስጥ ራሴን ሙሉ በሙሉ ለኮሚኒኬሽን ፕሮጀክት አደርጋለሁ። ይህ እኔን ደስተኛ ያደርገኛል። አዲስ አበባ በዓለም ላይ ካሉ  አስደናቂ ከተሞች አንዷ ናት። ከተማዋን በደንብ አዉቃታለሁ። አስደሳች ከተማ ናት። አዲስ አበባ ላይ በጣም ምቾት ይሰማኛል። እዚህ ጀርመን ላይ የቀድሞዋ የታዋቂ ዋና አዘጋጅ ነኝ። ኢትዮጵያ በምኖርበት አካባቢ ስዘዋወር ፤ አካባቢዬ ላይ የሞኖሩ ሰዎች ያዉቁኛል። በ 70 ዓመት እድሜዎች አሁንም ይሰራሉ?  ጥሩ ነዉ ሲሉ ያደንቃሉ። እኔም በተራዬ የናንተ አያት ብዙ ገና የምትሰራዉ ስራ አላት ስል እመልስላቸዋለሁ»   

ቤአተ እዚህ ጀርመን የታዊቂ ሰዎችን የሚዘግበዉ ቴሌቭዥን እና መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆነሽ ለብዙ ዓመታት ሰርተሻል። በጀርመን ታዋቂዉ የጎልድነ ካሜራ፤ የባንቢ ሽልማት መድረክ ዋና አዘጋጅም ነበርሽ። በሌላ በኩል ግጭት ጦርነት ድህነት በሚታይበት አካባቢ ከፍተኛ ስራን ትሰርያለሽ። ታድያ  ሁለቱን ዓለም እንዴት ነዉ ማስታረቅ የምትችይዉ?

«ምክንያቱም፤ ለየት አድርጌ ራቅ አድርጌ ማሰብን ስለምወድ ነዉ። በኑሮ እና ስራዬ ላይ ፈተናዎች ባያጋጥሙኝ እና እነሱን በመፍታት ባልጠመድ ደስተኛ የምሆን አይመስለኝም። የህይወት ፈተናዎችን የማይፈልጉ ሰዎች እንቅልፍ ላይ ናቸዉ፤ ወይም በጭራሽ እየኖሩ አይደለም። ብልጭልጩን እና የማራኪውን ዓለም ማየት በራሱ ፈታኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ማራኪውን አለም በህይወቴ ውስጥ ተካፍዬ አላውቅም። በኢትዮጵያን ማየት በጣም ያስደስተኛል።  ከ40 ዓመታት በፊት በጎርጎረሳዉያኑ 1981 ካር ሃይንስ ቦም ሰዎች ለሰዎች ወይም በጀርመንኛዉ ሜንሽን ፎር  ሜንሽን የተባለዉ የርዳታ ድርጅት ሲያቋቁም ነበርኩ አይቻለሁ። የካር ሃይንስን የህይወት ታሪክን ፅፌያለሁ፤ ስለ ኢትዮጵያም ሁለተኛ መጽሐፍን ጽፌያለሁ።  አዲስ አበባ ብቻን አይደለም የማዉቀዉ፤ ከሰዎች ለሰዎች የርዳታ ድርጅት ጋር በሃገሩቱ የተለያዩ ክፍሎች ፤ እጅግ ድህነት የሚታይባቸዉን አካባቢዎችን ሁሉ አይቻለሁ። የሰዎች ለሰዎች መስ  ራች ካርል ሃይንስ በም እና የድርጅቱ ሰራተኞች የሰዎችን ህይወት ለማሻሻል ያደረጉትን ጥረት አይቻለሁ። ይህ በኮሚኒስቶቹም በሶሻሊስቶቹም ዘመነ መንግሥት ሲሰራ የነበረ ሰብዓዊ ድርጅት ነዉ። አሁንም ድርጅቱ የሰብዓዊ ርዳታዉን እየሰራ ነዉ ስራዉንም ይቀጥላልም።»   

ምስል Privat

ታዋቂዋ ጀርመናዊት ጋዜጠኛ ቤአተ ቬደኪንድ፤ የጀርመኑ የልማት ትብብር ሚኒስትር ጌርድ ሙለር  ወደ ኢትዮጵያ ሲጓዙ አብራ የምትጓዝ ጋዜጠና ናት። ኢትዮጵያን በተለይም ወጣቱን ለመደገፍ ባላት ሁሉ መነሳትዋን፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚያዉቋት ሁሉ ይናገራሉ። በጀርመን ከሚገኘዉ ዘ ፒዮኔር ከተባለዉ የዜና ማሰራጫ ጋር ባደረገችዉ ቃለ-ምልልስ ላይ እንደተናገረችዉ፤ በመጭዉ መጋቢት ወር ላይ ከኢትዮጵያ ሆና፤ በአዲስ አበባ እና በበርሊን መካከል ክሮስ «ጀነሪኅን ኮንፈረንስ» ማለትም በትዉልድ መካከል የሚካሄድ የልምድ የእዉቀት ጉባኤን ትመራለች። አድማጮች ረዘም ያለዉ የቃለ ምልልስ ክፍ በድረ ገፃችን ላይ ወይም ፌስ ቡክ ላይ ይገኛል እንድትከታተሉ በመጋበዝ የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW