የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሰላምና ደህንነት ፤ የሰዎች አስተያየት
ረቡዕ፣ ነሐሴ 24 2015
የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሰላም ፣ የዜጎቿ ደህንነት፣ በሰላም ወጥቶ መግባት ፣ ከጦርነትና ግጭት ድባብ መውጣት፣ የልዩነት ችግሮች ጠበው የአንድነት፣ የመተባበርና የመከባበር ብሎም የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ምላሽ የሚጠየቅባቸው አሳሳቢ ጉዳዮች ሆነዋል። ሕዝብ በሰላም በፈለገው ሥፍራ ወጥቶ ተንቀሳቅሶ የመሥራት፣ የመኖር መብቱን እየጠየቀ ነው። ስለ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ነባራዊ የሰላምና ደህንነት ሁኔታ ፣ ስለ ሥጋትና ተስፋቸው በሙያ ደረጃ ጋዘጠኛን፣ የመንግሥት ሠራተኛን ፣ ነጋዴን፣ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባል የነበሩ አሁን በጥበቃ ሥራ የተሰማሩን ፣ እና በጡረታ ተገልለው በእረፍት ጊዜ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሀሳባቸውን እንዲያጋሩን ጠይቀን አሰባስበናል።
የመንቀሳቀስ ሥጋት
«ትናንት ከዚህ መቀሌ መሄድ ፣ ከመሃል አዲስ አበባ ተነስትህ ወለጋ መሄድ ሰላም የነበረ ሀገር እዚያ መሄድ ፍርሃት አድርጎብህ ከዚያ ተመልሶ ዛሬ ደግሞ ከዚህ ባሕርዳር መሄድ ከዚህ ደብረ ብርሃን መሄድ አትችልም ዛሬ። ወይም ደግሞ እዚህ አምቦ ጫፍ ያሉ ቤተሰቦችህን አታገኝም ኔትዎርኩም፣ መንገዱም ተዘግቶብሃል። ይሄ የምንገብርለት መንግሥት መጀመርያ እንዲያደርግልን የምንፈልገው የመጀመርያው ነገር ቢያንስ ከቤታችን መሥሪያ ቤታችን፣ ከመሥሪያ ቤታችን ቤታችን ፣ ቤተሰባችን ጋር ደርሰን እንድንመጣ ማድረግ የመጀመርያው ጥቅማችን ነው ። ከመንግሥት ልናገኘው የሚገባን የምንከፍልለት፣ የምንገብርበት ነው። ይሄንን እያደረገልን አይደለም። በእኔ እይታ እና ከዚህ አኳያ አሁንም ቢሆን ምን ትሻለህ ካልከኝ መንግሥት ይሄንን ቢያንስ ትንሹን አላማውን እንዲያሳካልን እንፈልጋለን።»
የኢትዮጵያ የሰላም ሁኔታ በአስተያየት ሰጪዎች ምልከታ
«የኢትዮጵያ የሰላም ሁኔታ ትንሽ ያሰጋል። ሕዝቡ ወጥቶም መግባት የማይችልበት ደረጃ ላይ የደረሰበት ሁኔታ ላይ ነው ያለው። ቢቻል ወደ ሰላማዊ መንገድ መምጣት የሚችሉበትን መንገዶች ቢያመቻቹ መልካም ነው።»
«ስለ ሰላም ሳይይዘመር ውሎ አያውቅም። ግን ወደ ተግባር የሚለውጠው ጠፋ። መንግሥት ራሱ አሁን ሰላም መሆን አለበት፣ መቃቃር የለብንም እያለ ያወራል። ግን ወደ ተግባር የሚያውለው ጠፋ። ሰላም ስለሌለ እኮ ነው እንደዚህ የሆነው። በየመንገዱ እየተዘጋ ሰላም አጥቶ ሕዝቡ ከወዲያ ወዲህ ተንቀሳቅሰህ ካልሰራህ ሰላም አለ ብለህ መውሰድ አትችልም። በዚያ ላይም እየተዘረፈ ነው። በቀን ዘረፋ አለ። በየሄድክበት በትራንስፓርት ላይም ዘረፋ አለ።»
«በሀገሪቱ ላይ ካሉ የተለያዩ ግጭቶች ጋር ተያይዞ ዜጋው ብቻ አይመስለኝም፤ የከተማው አስተዳደሩ ራሱ ሥጋት እንዳለበት አመላካች ነው። ለለዚህ ደግሞ ማታ ላይ የሚያሰማሯቸው እና ከተማውን ይቃኛሉ ብለው ያደራጇቸው የተለያዩ ታች ያሉ የፀጥታ መዋቅሮችን ማየት እንችላለን።»
«ሰላም ሆኖ ሀገራችን ሲበለጽግ ደስ ይለናል። ሰላም ስንሆን ፣ ስንጠነክር ደግሞ አንድ ሰውም አይገባንም። ወደ ሀገራችንም አይጠጋም። ይፈራል። ራስ በራስህ ስትጣላ ደግሞ ብዙ ችግር ስላለ ጠላቶች ይገባሉ።»
የሰላም መታጣት ችግር ምንድን ነው?
«አንዱ ትልቁ ጉዳት ያመጣው የሥነ ምግባር ትምህርቶች ከትምህርት ቤት መወገዳቸው ነው። ወደኋላ ሄዶ የራስን ታሪክ እና ባህል ምን እንደነበርን፣ ማን እንደሆንን ማየት ካልተቻለ ብዙ ጥፋቶች፣ ብዙ ጉዳቶች ፣ ብዙ ነገሮች ያልፋሉ። ከዚያ በኋላ ግን መልካም ነገር ይታየኛል ብየ አምናለሁ። ሰላም እንደሚመጣ ፣ አንድነት እንደሚመጣ፣ ፍቅር እንደሚመጣ አምናለሁኝ።»
የችግሩ መፍትሔዎች ምንድን ናቸው ? ተስፋና ሥጋቶችስ ?
«እንዲህ እንደሆነ አይቀርም። የተሻለ ነገር፣ የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብየ አምናለሁ። መንግሥት የሕዝቡን ሮሮ ቢሰማ ቀላል ነገር ነው።»
«ሕዝቦች የሚያነሷቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ባለመመለሳቸው ምክንያት ከቀን ወደ ቀን ችግሮች እየሰፉ ነው። እንደ ተስፋ የማየው ምናልባት መንግሥት የሕዝብ ጥያቄ ሆነው አልመለስኳቸውም ብሎ ገምግሞ ከሚያስቀምጣቸው ጉዳዮች አንዱ የሰላም እና ደህንነት ወይም የዜጎች ወጥቶ በሰላም የመሥራት ፣ የመንቀሳቀስ ጉዳይን በትኩረት አይቶ የሚሰራበት ሊሆን ይችላል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ።»
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ