የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተመድ ለየፃፈው ደብዳቤ ህወሓት ምላሽ ሰጠ
ሐሙስ፣ መስከረም 29 2018
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተባበሩት መንግስት ድርጅት የጻፈው ደብዳቤ ከዕውነት የራቀ ነው ሲል ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራት (ህወሓት) ምላሽ ሰጠበት ። ህወሓት ዝርዝር ምላሹን ያካተተበትን ደብዳቤ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ እና ሌሎች አካላት መላኩም ተዘግቧል ።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ የፃፈው እና የኤርትራ መንግስት እና ሕወሓትን የሚከስ ደብዳቤ ተከትሎ ሁለቱም አካላት ምላሽ ሰጥተዋል። ሕወሓት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ እንዲሁም በግልባጭ ለአፍሪቃ ኅብረት፣ ኢጋድና እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት የላከው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ በኩል የቀረበው ክስ አደገኛ እና እውነትን የገለበጠ፥ በተጨማሪም በዳዩ እንደተበዳይ፣ ተበዳይ ደሞ እንደበዳይ የሚያስቀምጥ ብሎታል ።
የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያን ስምምነት ከመተግበር ይልቅ በፈጠራ ታሪኮች ህወሓት ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት ለማሳት እየሞከረ እንዳለ ፓርቲው ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ በላከው ደብዳቤ አመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪ የፕሪቶርያ ስምምነት እየተጣሰ ነው ብሎ የተለያዩ ነጥቦች ያነሳው ህወሓት፥ ተፈፃሚነቱ ለማረጋገጥ አዲስ ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ዐሳውቋል ።
በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ እየተወዛገቡ ያሉት የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ወደሌላ ዙር ጦርነት ተመልሰው እንዳይገቡ በበርካቶች ዘንድ ስጋት ተፈጥሮ ይገኛል ። በመቐለ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች ይህንኑ ስጋታቸውን ይገልፃሉ፥ ሰላምን ዘላቂ የሚያደርጉ ርምጃዎች እንዲወሰዱም ይጠይቃሉ ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ በኢትዮጵያ በኩል ክስ የቀረበባት ኤርትራ ክሱን ወታደራዊ ፀብ አጫሪነት ስትል ውድቅ አድርጋለች ። የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል "የቀድሞ ግዛትን ለማስመለስ ያለመ" ያሉትን ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑ ዘመቻም ፀብ አጫሪነት የታከለበት ነው መናገራቸውን ተገልጿል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ፀሓይ ጫኔ