የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 30 2013
ማስታወቂያ
የአውሮጳ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ የባለሙያዎችን ቡድን ከትናንት ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ መስማማቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው አስቸኳይ መግለጫ አስታወቀ።
ሕብረቱ የራሱ የኮሙኒኬሽን መሣሪያ እንዲያስገባ እና የምርጫን ውጤት ቀድሞ ለማሳወቅ ያቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በኢትዮጵያ መንግሥት ውድቅ መደረጋቸውን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት የምርጫ ታዛቢ እንደማይልክ ገልፆ ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለውጪ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫቸው ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ማዕቀፍ እንዲቀጥል ግፊት እያደረገች መሆኑን ፣ ሱዳን በኢትዮጵያ ሕጋዊ መሬት ላይ ወረራ መፈፀሟ ሳያንስ አሁን ደግሞ ቤኒሻንጉል ላይ የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳቷ ለሱዳንም፣ ለቀጣናውም ሆነ ለኢትዮጵያ የማይበጅ የውክልና ተልዕኮን የማስፈፀም ሂደት ላይ የመሆኗ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በሱዳን ወታደራዊ ሠራዊት የተያዘባትን ድንበር አስለቅቃ የሱዳን ወታደሮችን ከግዛቷ አስወጣች ተብሎ ከሰሞኑ ስለሚነገረው መረጃ ተጠይቀው "መረጃ የለኝም" ብለዋል። አክለውም ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ነፃ እና ፍትሓዊ እንዲሁም ሰላማዊ ሆኖ መካሄዱ ይቀጥላል ብለዋል።
ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ