1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ማሳሰቢያ

ሰኞ፣ ጥር 29 2015

ጉባኤው የተፈጠረው ችግር በቤተ ክርስትያኒቱ ሕግ፣ ቀኖን እና ሥርዓት ላይ ብቻ ተመሥርቶ እንዲፈታ፣ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በኢፊዴሪ ሕገ መንግሥት የመንግሥት እና የሃይማኖት መለያየትን የሚደነግገውን አንቀጽ 11ን እና የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነትን የሚደነግገውን አንቀጽ 27ን ብቻ መሠረት አድርገው እንዲሠሩ አሳስቧል።

Äthiopien | Haji Mesud Adem mit führenden Vertretern des Interreligiösen Rates
ምስል Solomon Muchie/DW

ሁሉም ምእመን ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ጥቁር ልብስ በመልበስ፣ በጸሎት እንዲተጋ አውጃለች።

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ከሰሞኑ የገጠማት ችግር "እየተባባሰ እና እየተካረረ መሄዱ በእጅጉ አሳስቦኛል" ሲል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። ከሰባቱ የጉባኤው አባል የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ባልተገኘችበት በዛሬው መግለጫ ቤተ ክርስትያኗ "ውይይትን ፣ ይቅርታንና እርምትን" እንድታስቀድም ተጠይቋል። ጉባኤው የተፈጠረው ችግር በቤተ ክርስትያኒቱ ሕግ፣ ቀኖን እና ሥርዓት ላይ ብቻ ተመሥርቶ እንዲፈታ፣ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በኢፊዴሪ ሕገ መንግሥት የመንግሥት እና የሃይማኖት መለያየትን የሚደነግገውን አንቀጽ 11ን እና የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነትን የሚደነግገውን አንቀጽ 27ን ብቻ መሠረት አድርገው እንዲሠሩ አሳስቧል። ቤተ ክርስትያኗ ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ጥቁር ልብስ መልበስ ምእመኑ በፀሎት እንዲተጋ አውጃለች። የመንግሥት ኮሙኑኬሽን ባበኩሉ "በቤተ ክርስቲያኗ አባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት ሰላማዊ በሆነ መንገድ በውስጣዊ አሠራር መፈታት እንዳለበት" ገልጿል። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የሰሞኑ ችግር ከከተከሰተበት  ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩ በሰላም እንዲፈታ ከሃይማኖቱ መሪዎች ጋር መነጋገሩን የስድስቱ አባል የጉባኤው አባል የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ገልፀዋል። "ሆኖም ችግሩ ይበልጥ ተባብሶ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ መድረሱ አሳስቦናል።" ብለዋል። መግለጫውን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ  ምክትል ጠቅላይ ፀሐፊ እና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ሀጂ መሱድ አደም አቅርበዋል። "የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤታ ክርስትያን አባቶች ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ከማክበር እና ከማስከበር ጎን ለጎን የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በመገንዘብ ውይይትን፣ ይቅርታንና እርምትን እንድታስቀድሙ እንጠይቃለን" ፤ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የፌዴራልና የክልሎች መንግሥታት በቤተ ክርስትያኗ ላይ የተፈጠረውን ችግር በራሷ በቤተ ክርስትያኗ ሕግ ቀኖና እና ሥርዓት ላይ ብቻ ተመሥርቶ እንዲፈታ በሕገ ማንግስቱ የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየትን የሚደነግገውን አንቀጽ 11ን እንዲሁም የሃይማኖት ፣የእምነትና የአመለካከት ነፃነትን የሚደነግገውን አንቀጽ 27ን ብቻ መሠረት አድርገው እንዲሠሩም አሳስቧል። 
"በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በሃይማኖት ፣ በፖለቲካና በብሔር ማንነት ምክንያት እየደረሱ ያሉ ግድያዎች እና የንፁሐን ህልፈት በእጅጉ ያሳዝነናል።" 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ. ም በአባ ሳዊሮስ አማካኝነት "ኢ - ሲኖዶሳዊ በሆነ መልኩ የቀኖና ጥሰት በመፈፀም በሕገ ወጥ መልኩ የተሰጠ" የተባለውን ሲመት አውግዞ ሲመት ሰጪዎችንም ሆነ ተቀባዮቹን የተሰጣቸውን ከዲቁና ጀምሮ ያለውን ሙሉ ሥልጣናቸውን በመሻር ከቤተ ክርስትያን ለይታቸዋለች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስትያኗ በእምነቱ አባቶች እና ተከታዮች ላይ ጥቃት እየተፈፀመ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታውቃል። በሻሸመኔ ከተማ ማእመናን ከፀጥታ አካላት በተተኮሰ ጥይት መሞታቸውም ተነግራል። በዛሬው መግለጫ የጉባኤው አባል የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን አልተገኘችም። በመግለጫው መንግሥት በቤተ ክርስትያኗ ላይ ስላወጣው መግለጫ፣ ከአንዳንድ የሌላ እምነት አስተማሪዎች ቤተ ክርስትያኗን አስመልክቶ ስለሚቀርቡ ትንኮሳዎች ምንም አልተባለም። ለጋዜጠኞችም ጥያቄ የማቅረቢያ እድል አልተሰጠም። 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን "ሁሉም ምእመን ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ጥቁር ልብስ በመልበስ፣ በጸሎት እንዲተጋ አውጃለች። ቅዱስ ሲኖዶሱ ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ "በነዚህ የጸሎትና የምሕላ ጊዜያት 'የደነደኑ' ያሏቸው ልቦች ወደ ልቦናቸው ተመልሰው የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥሪ ሰምተው የማይፈጽሙ ከሆነ ለየካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ ወስኗል።
ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት "ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ በውስጣዊ አሠራር መፈታት እንዳለበት መንግሥት ያምናል።" ሲል አስታውቋል። ለዚህም ሁሉም አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል። ሲም አሳስቧል። መንግሥት አማኞች ችግሩን ከማወሳሰብና ለሌሎች አካላት መጠቀሚያ ከመሆን እንዲቆጠቡ የጠየቀ ሲሆን "በሕዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር፣ ብሎም ሀገርን ወደፈተና ለማስገባት በሚጥሩ" ባላቸው  አካላት ላይ ሕግ የማስከበር ሥራውን እንደሚሠራም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤምስል Solomon Muchie/DW


ሰሎሞን ሙጬ


ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW