1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ገቢራዊነቱ

ሰኞ፣ ኅዳር 5 2015

ሁለቱ ወገኖች ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ የፈረሙትን ግጭትን በዘላቂነት የማስወገድ ስምምነትን ገቢር ለማድረግ መዋዋላቸዉ የዘግናኙ እልቂት የመጨረሻዉ መጀመሪያ መሆኑ ሊያከራክር አይገባም።ለኢትዮጵያ ሕዝብ-ባጠቃላይ፣ በተለይ ባልሰራዉ ወንጀል፣ ለማይጠቅመዉ ጦርነት ልጅ፣ወዳጅ ዘመዱን ለገበረዉ፣ ለቆሰለ፣ ለተፈናቃለ፣ ለተሰቃየዉ ሕዝብ በርግጥ እፎይታ ነዉ።

Kenia I Friedensabkommen von Pretoria
ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ገቢራዊነቱ

This browser does not support the audio element.

                

ፊልድ ማርሻል ብርሐኑ ጁላ ለገቢራዊነቱ ቃል ገቡለት።ጄኔራል ታደሰ ወረደ ተስፋ ጣሉበት።ተፈራረሙም።አደራዳሪ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆና ኡሁሩ ኬንያታ ተደሰቱበት።ለኢትዮጵያ ሰላም ፕሪቶሪያ ደገሰች፣ናይሮቢ ገበታዉን ዘረጋች።ለኢትዮጵያዉን እፎይታ።እንዴት?እና ከእንግዲሕስ?ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ በፀና ሐገረ-መንግስትነት ታሪክ፣ ቅኝ ባለመገዛትም ከብዙዎቹ የዓለም መንግስታት ቀዳሚ ናት።ሰማይን የሚታከክ ተራራን፣ ከጥልቅ ስምጠት፣ ደጋን ከበረሐ አሰባጥራ የያዘች፣ ከኮሪያ ልሳነ-ምድር እስከ ኮንኮ (ዛኢር) የጦር አዉዶች ጀግንነትን ያስመከሩ ወታደሮች፣ከሮማ እስከ አትላንታ የረጅም ርቀት ሩጫ ድንቅ አትሌቶች ያፈራችና የምታፈራ ድንቅ ሐገር ናት።

የዚያኑ ያክል ባጭር ጊዜ ምናልባትም ብዙዎች እንደሚሉት ለትርጉም የለሽ ጦርነት  ብዙ መቶ ሺዎችን የረገፉባት፣ ብዙ ሺዎች ደም አካላቸዉን ያጡባት፣ሚሊዮኖች የተፈናቀሉ፣ብዙ መቶዎች የተደፈሩ፣ጎሳ ከጎሳ የተናጩባት፣ ሚሊዮኖች የሚራቡባት ሐገርም ናት።

የፕሪቶሪያዉ የሰላም ዉል ሲፈረምምስል Siphiwe Sibeko/REUTERS

አምና ይኸኔ ስለዉይይት፣ድርድር፣ዕርቅ የዘገቡ ወይም የተናገሩ ዜጎችዋ ባደባባይ የተዋረዱ፣የተበሻቀጡ፣የተረገሙባት ለግድያ የተዛተባቸዉ ሐገርም ናት ወይም ነበረች።ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ በሚታወቀዉ የጦርነት ታሪክ ባጭር ጊዜ ዉጊያ ብዙ ሰዉ በመጨረስ ከጥቂት ሐገራት እንዷ እንደሆነች ሁሉ፣ ዘንድሮ፣ የቀድሞዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የድርድር ጉዳይ ባለሙያ ባይሳ ዋቅወያ እንደሚሉት ባጭር ጊዜ ድርድር የሰላም ዉል ከተፈረመባቸዉ ጥቂት ሐገራት አንዷ ሆነች።የመቐለ ድባብ በስምምነቱ ማግስት

«በታሪክ ዉስጥ ከእንደዚሕ ዓይነት መገዳደልና መፈናቃቀል በኋላ ባጭር ጊዜ ስምምነት ላይ የተደረሰበት---ጦርነት እኔ አይቼ አላዉቅም።በጣም ፈጣን ነዉ።በጣም አስደሳች ነዉ»

ለፈጣን ግን አስደሳቹ ስምምነት ብዙዎች ብዙ ምክንያት ይጠቅሳሉ።የጦር ሜዳዉ የኃይል ሚዛን መለወጥ፣በሕዝቡ ላይ የሚደርሰዉ ስቃይ ማየልና መራዘም፣ የተፋላሚ ኃይላት መሰላቸት፣ ለጎበዝ መዉጪያ  ፍለጋ መቃተት፣ የምዕራባዉያን በጣሙን የአሜሪካኖች ጫና ብዙ ጊዜ የሚጠቅሷቸዉ ምክንያቶች ናቸዉ።

ፕሪቶሪያ ላይ የአደራዳሪዎች ጥንቃቄ፣የተደራዳሪዎች ጭፍግግ ስሜት፣የድርድሩ ሒደት ጥብቅ ሚስጥር የወጠረዉ ንግግር ናይሮቢ ላይ ለቀቅ፣ፈገግ፣ ከፈት ዘና ባለስሜት መቀጠሉን የሚጠቅሱም አሉ።ቪዲዮና ፎቶዉም ይናገራል።

ኦሌሶጎን አባሳንጆ እና ኡሁሩ ኬንያታ (ከግራ ወደ ቀኝ)ምስል African Union

ድርድሩ ለሻሒ-ቡና ዕረፍት ሲቋረጥ የሁለቱ ወገኖች ዋና ተደራዳሪዎች ሪድዋን ሁሴንና ጌታቸዉ ረዳ፣ከሌሎች ጋር ክብ ሰርተዉ ሲነጋገሩ ማየት ለብዙዎች የድርድሩን ሒደት አግባቢነት ጠቋሚ ነበር።የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ ረሺድ አብዲ በትዊተር ገፃቸዉ የለጠፉት ፎቶ ደግሞ የመግባባቱን ቅርበት መስካሪ ነዉ።ፊልድ ማርሻል ብርሐኑ ጁላ በግራቸዉ፣ ጄኔራል ታደሰ ወረደ በቀኛቸዉ ጣቶቻቸዉ የተለኮሰ ሲጋራ ይዘዉ፣ ጌታቸዉ ረዳን ከመሐል አድርገዉ ያወጋሉ።«ይሕ የሲጋራ ዕረፍት ስምምነቱን ለመፈረም ከፍተኛ ስልታዊ ሚና ተጫዉቷል» ይላሉ።» ረሺድ።

ሊሆንም ላይሆንም ይችላል።ነገር ግን ከአርባ ዘመን በላይ ለሁለት ተገምሳ የምስራቅ-ምዕራብ ክፍሏ መሪዎች በጠላትነት ሲዛዛቱባት የነበረችዉ ጀርመን ዳግም የተዋሓደችዉ የአራትዮሽ ይባል ከነበረዉ የኃያላን  መንግስታት ድርድር ይበልጥ «የዛዉማገን ዲፕሎማሲ» በሚባለዉ ንግግር ነበር።ሕዳር 1990 (እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር) የሶቭየት ሕብረቱ መሪ ሚካኤል ጎርቫጆቭ ምዕራብ ጀርመንን ጎበኙ።

ከጉብኝቱ ባንዱ ምሽት የያኔዉ ምዕራብ ጀርመን መራሔ መንግስት ሔልሙት ኮል እንግዳቸዉን ዳይዲሽሀይመር ሆፍ ከተባለዉ ሆቴል ዛዉማገን የተባለዉን የጀርመኖች ምግብ ራት ጋበዟቸዉ።በሹካ-ቢላ- ማንካዉ ቅጭልጭታ መሐል በምርጥ ወይን ያወራረዱት ዉይይት የበርሊንን ግንብ ደረመሰ።

የረሺድ አብዲ የትዊተር ዘገባ እዉነትም-ሐሰትም ሊሆን ይችላል።የሁለቱ ወገኖች ተደራዳሪዎች ተነጋገሩ፣ አወሩ፣ የጦር አዛዦቹም ተነጋገሩ፣አጤሱ፣ተግባቡ ተፈራረሙ።እና ፊልድ ማርሻል ብርሐኑ ጁላ ቃል ገቡ።

«ለሕዝባችንና ለሐገራችን ሰላምና መረጋጋት ለማስፋን ሙሉ ቁርጠኝነታችንን መግለፅ እንወዳለን።ስለዚሕ የፕሪቶሪያዉን ስምምነትና ይሕንን ዉል ገቢር ለማድረግ እራሳችንን ሙሉ ተገዢ እናደርገለን።»

ጄኔራል ታደሰ ወረደ የስቃዩን መጠን ጠቀሱ፣ተስፋ አደረጉ።

«ባለፉት ሁለት ዓመታት ባልተነገረ ሰቆቃ ተሰቃይተናል።አሁንም እየተሰቃየን ነዉ።ዛሬ የምንገባዉ ቃል የሕዝባችን ስቃይ ያበቃል እና ባስቸኳይ ያበቃል ከሚል ተስፋና እምነት ጋር ነዉ።»

ሁለቱ ወገኖች ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ የፈረሙትን ግጭትን በዘላቂነት የማስወገድ ስምምነትን ገቢር ለማድረግ መዋዋላቸዉ የዘግናኙ እልቂት የመጨረሻዉ መጀመሪያ መሆኑ ሊያከራክር አይገባም።ለኢትዮጵያ ሕዝብ-ባጠቃላይ፣ በተለይ ባልሰራዉ ወንጀል፣ ለማይጠቅመዉ ጦርነት ልጅ፣ወዳጅ ዘመዱን ለገበረዉ፣ ለቆሰለ፣ ለተፈናቃለ፣ ለተሰቃየዉ ሕዝብ በርግጥ እፎይታ ነዉ።

«ሁሉም አሸነፉ» ይላሉ የሕግ ባለሙያዉና የቀድሞዉ ዲፕሎማት ባይሳ ዋቅወያ።

የተመታ ታንክምስል Tiksa Negeri /REUTERS

«በኔ ግምት ሁለቱም አሸንፈዋል።ሁለቱም ወደዚሕ ጦርነት የገፋፋቸዉ በነሱ አባባል የሕገ-መንግስት መጣስ ነዉ።እነ አቦይ ስዩም በትግራይ ቲቪ ቀርበዉ የዶክተር ዓብይ መንግስት ሕገ-መንግስቱን ጥሶ የስልጣን ዕድሜዉን ስላራዘመ ቅቡልነት የለዉም፣ ስለዚሕ ከፌደራሉ መንግስት ምንም ዓይነት ትዕዛዝም አንቀበልም---መንግስት ደግሞ በሕገ-መንግስቱ መሰረት ያወጅኩትን  ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥሰወዉ ምርጫ አድርገዋል ብሎ ነዉ የተጣሉት።----አሁን የተደረገዉ ስምምነት ባንድ ዓረፍተ ነገር ሲጠቃለል ሁለቱም ቡድኖች ችግራቸዉን በሕገ መንግስቱ መሰረት ለመፍታት ነዉ የተስማሙት።»

ስምምነቱ ያላረካቸዉ፣ ሲገፋም የሚቃወሙት አሉ።ከተቃዋሚዎቹ አንዳዶቹ የኢትዮጵያ መንግስት «ሕግ ማስከበር» ያለዉን ወታደራዊ ዘመቻ ድፍን ሁለት ዓመት ሲደግፉ የከረሙ ናቸዉ።ሕግ እንዲከበር እየደገፉ ሕገ-መንግስት የሚያስከብረዉን ስምምነት መቃወማቸዉ በርግጥ ታዛቢን ለፈገግታ መዳረጉ አልቀረም።ሌሎች የአወዛጋቢ ግዛቶች አስተዳደር ጉዳይን፣ የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መዉጣትና የሕወሓት የመሪ ፓርቲነት ብቃትን ይጠቃሳሉ።

የብዙዎቹ አባባሎች ግን ከስምምነቱ ይዘት ጋር የሚጣጠም አይደለም እንደ አቶ አቶ ባይሳ።በዉሉ መሰረት ሰብአዊ ርዳታ ዉሉ ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ትግራይ መግባት አለበት።ሰላማዊ ሰዎችን ከጥቃት ይከላከላሉ።ተፈራራሚዎች ስምነቱ ገቢር መሆኑን የሚከታተል የጋራ ኮሚቴ ይመሰርታሉ።

የትግራይ ታጣቂዎች ከነገ ጀምሮ ትጥቅ ይፈታሉ።ተዋጊዎቹ የኢትዮጵያ ፈደራዊ ጦርን ይቀላቀላሉ።ይሁንና ተዋጊዎቹ በተለይ ከባድ የጦር መሳሪያ የሚያስረክቡት በስምምነቱ «የዉጪ ኃይል» ተብሎ የተጠቀሰዉ የኤርትራ ጦርና ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዉጪ ያሉ ታጣቂዎች ከትግራይ ክልል ሲወጡ ነዉ።

የኤርትራ መንግስት እስካሁን ስለስምምነቱ በይፋ ያለዉ ነገር የለም።የቀድሞዉ የኤርትራ የነፃነት ታጋይ፣ፀሐፊና ተመራማሪ መሐመድ  ኸይር ዑመር ባለፈዉ ሐሙስ እንደፃፉት ስምምነቱን ገቢር ለማድረግ እንቅፋት ከሚሆኑ ችግሮች አንዱ ምናልባትም ዋነኛዉ የኤርትራ አቋም ነዉ።

መሐመድ እንደሚሉት በዉጊያዉ አዉድ የኤርትራ ጄኔራሎች ከኢትዮጵያ የዕዝ መዋቅር ዉጪ እንዳሻቸዉ ሲዋጉና ሲያዋጉ ስለነበር ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ የዉጊያዉን አዉድ ሙሉ በሙሉ አይቆጣጠሩም።

«ያሁኑም ሆነ ሌሎች አፍሪቃ ቀንድ ዉስጥ የሚደረጉ የሰላም ስምምነቶች ዘላቂ ዉጤት እንዲኖራቸዉ» ይላሉ መሐመድ ኸይሬ ዑመር ፕሬዝደንት «ኢሳያስ በአካባቢዉ ሰላም ላይ የሚደቅኑት ስጋት መላ ሊበጅለት ይገባል።»

አቶ ባይሳ ዋቅ ወያ ግን የኤርትራን ጦር ከኢትዮጵያ ለማስወጣት ሕጋዊዉ «መፍትሔ ቀላል ፣እርምጃዉም በኢትዮጵያ መንግስት እጅ ነዉ» ይላሉ።

 የስምምነቱ ተፈራራሚዎች በጦርነቱ ወቅት የደረሰዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማጣራትና ተጠያቂዎችን ለፍርድ ለማቅረብ ስለሚደረገዉ ጥረት ብዙም የጠቀሱት ነገር የለም።የመብት ተሟጋቾች «ፍትሕ ከሌለ ዘላቂ ሰላም አይኖርም።» ይላሉ።

ሰላማዊ ሰዎችን የገደሉ፣ ሴቶችን የደፈሩ፣ የጦር ወንጀልና ሌሎች ግፉችን የፈፀሙ በሙሉ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል።

የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት የተፈፀመዉን ግፍ ማጣራት፣ በዳዮችን ለፍርድ ማቅረብ፣ ተበዳዮችን መካስ የስምምነቱ ገቢራዊነት አካል መሆን አለበት።ስምምነቱን ገቢር ማድረጉ ራሱ ታዛቢዎች እንደሚሉት በርግጥ ከእስካሁኑ ሒደት ሁሉ ሳይከብድ አይቀርም።

መቀሌ የድሮን ጥቃትምስል UGC/AP/picture alliance

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የብዙ ሺዎችን ሕይወትና አካል ያጠፋ፣ ሚሊዮኖችን ያፈናቀለ፣ ያስራበ፣ ያሰቃየ ዘርን-ከዘር ያዛዛተ፤ ተጎራባቾችን ያቂያቂያመ ጦርነትን ማቆም፣የተፋላሚ መሪዎችን ማስማማት ከባድ ነዉ። ደንቡን ወይም ስምምነቱን ገቢር ማድረግ ደግሞ ሲበዛ ከባድ ነዉ።እንደገና አቶ ባይሳ።

«ስምምነት ላይ መድረስ ከስምምነቱ ተፈፃሚነት ሒደት አንፃር ሲታይ በጣም ቀላል ነዉ።---በተለይ በርስበርስ ጦርነት ወቅት የታጠቁ ሁለቱን ወገኖችን አስማምቶ የትግራይ ታጣቂዎችን ማፍረስ ቀላል ነገር አይሆንም።ከሁሉ በላይ ለኔ አድካሚዉ ይኸ ነዉ----»

ሰኔ 26፣ 1945 (እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር (መተዳደሪያ ደንብ) ሳንፍራንሲስኮ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ሲፀድቅ፣ የያኔዉ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሐሪ ኤስ ትሩማን «ከጥቂት አመታት በፊት ይሕ ደንብ፣ ከደንቡም በላይ ደንቡን ገቢር የማድረግ ቁርጠኝነቱ ቢኖረን ኖሮ» አሉ፤ «ዛሬ የሞቱ ሚሊዮኖች በሕይወት ይኖሩ ነበር፤ ለወደፊቱ ደንቡን ገቢር የማድረግ ፈቃዳችኝነታችንን ከጣስን ደግሞ ዛሬ በሕይወት ያሉ ሚሊዮኖች መሞታቸዉ እርግጥ ነዉ» ብለዉ ነበር።«

ምስል Joerg Boethling/IMAGO

ባለፉት 77 ዓመታት የግዙፉ ድርጅት ደንብ መጣስ መከበሩ፣ የጣሰ-ያከበረዉ ወገን ማንነት ብዙ እንዳነጋገረ፣ እንዳስተዛዘበ፣ እንዳወዛገበም ነዉ።የትኛዉም ደንብ ወይም ስምምነትን መፈረም ግን ቀላል አይደለም።ቃል አክብሮ ስምምነቱን ገቢር ማድረግ ደግሞ ሲበዛ ከባድ ነዉ።የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ ኃይላት ተወካዮች የገቡት ከባድ ቃል ገቢር ለማድረግ፣ ቢከብድም የማድረግ ግዴታ አለባቸዉ።

ነጋሽ መሐመድ 

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW