የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ይዞታ
ሰኞ፣ መጋቢት 9 2005አለም አቀፍ የመብት ተከራካሪ ድርጅቶች የውጭ መንግሥታት የሐገር ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንደማይከበሩ በተለያዩ ጊዜያት በሚያወጧቸው ዘገባዎች ይጠቁማሉ ። የኢትዮጵያ መንግሥት ግን እነዚህን ዘገባዎች አይቀበልም ። ይልቁንም በህገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መሠረታዊ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በማስጠበቅና በማስከበር ላይ እንደሚገኝ ይናገራል ። ይሁንና በህገ መንግሥቱ የተደነገጉ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ፣ በሌሎች መብቶችን በሚጥሱ ህጎች ምክንያት ሊተገበሩ አልቻሉም ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ድርጅቶችና የውጭ መንግሥታት እንዲሁም ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ስሞታ ያቀርባሉ ። እነዚህ ወቀሳዎች የሚቀርቡበት መንግሥት በቅርቡ «ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች የድርጊት መርሃ ግብር » ያለውን ሠነድ አዘጋጅቷል ። በተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀው የዚህ የድርጊት መርሃ ግብር ፋይዳ ና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ይዞታ በመጪው እሁድ የሚተላለፈው እንወይ የመነጋገሪያ ነጥቦች ናቸው ። በነዚህ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩልን አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ፣ አቶ እንዳልካቸው ሞላ በቀድሞው አጠራሩ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የአሁኑ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ሃላፊ እንዲሁም አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያም የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ተመራማሪን ጋብዘናል ። ሙሉውን ውይይቱን ያድምጡ ።
ሂሩት መለሰ
ልደት አበበ