የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የኢንቨስተሮችን የድርሻ ድልድል እያካሔደ ነው
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 2 2016
ከ48 የኢትዮጵያ እና የውጭ ሀገር ተቋማት 1.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያሰባሰበው የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የኢንቨስተሮቹን የድርሻ ድልድል በማከናወን ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሰነደ-ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር ሚካኤል ሐብቴ “አሁን የድርሻ ድልድል እያደረግን ነው። ገና አልተጠናቀቀም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
በዚህ ሣምንት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ሒደት በኩባንያው ድርሻ የገዙ ባለ አክሲዮኖች ምን አይነት መብት እንደሚኖራቸው የሚወስን ነው።
ከካፒታል ገበያው ድርሻ ከገዙ ሦስት የውጪ ሀገር ኢንቨስተሮች አንዱ የሆነው የናይጄሪያው ኤክስቼንጅ ግሩፕ፤ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቴሚ ፖፖላ የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የቦርድ አባል እንደሚሆኑ አስታውቋል።
ከኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ 25 በመቶው ድርሻ የመንግሥት ነው። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና አራት የመንግሥት ተቋማት ለ25 በመቶው ድርሻ 225 ሚሊዮን ብር ከፍለዋል። የተቀረው 75 በመቶ ድርሻ በሀገር ውስጥ የግል ዘርፍ እና የውጭ ባለወረቶች የሚያዝ ነው።
በአዲስ አበባ፣ ናይሮቢ እና ሎንዶን ከተከናወኑ ተከታታይ የማግባባት ሥራዎች በኋላ የኢትዮጵያ ሰነደ-ሙዓለ ንዋዮች ገበያ 1.5 ቢሊዮን ብር ወይም 26.6 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ማሰባሰቡን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ጥላሁን እስማኤል ባለፈው መጋቢት 26 ቀን 2016 ተናግረዋል። ዶክተር ጥላሁን “631 ሚሊዮን ብር አካባቢ ለማሰባሰብ ነበር አስበን የነበረው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ 16 የግል የንግድ ባንኮች፣ 12 የኢንሹራንስ ድርጅቶች እና ሌሎች 17 የሀገር ውስጥ ተቋማዊ ባለሐብቶች ድርሻ ገዝተዋል። ብርቱ የዋጋ ግሽበት እና በባንኮች የሚታየው የጥሬ ገንዘብ እጥረትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ማክሮ ኤኮኖሚያዊ ፈተናዎች የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያው ካፒታል ለማሰባሰብ ለሚያደርገው ጥረት ተግዳሮት ይሆናል የሚል ሥጋት እንደነበር አቶ ሚካኤል ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ይሁንና የተሰበሰበው የገንዘብ መጠን ከታቀደው በ240 በመቶ የላቀ ሆኖ ተገኝቷል።
“የዘጋን ዕለት ድረስ ሰዉ ማመልከቻ እየላከ ነበር። በጣም ደስተኞች ነን” ያሉት አቶ ሚካኤል ከተጠበቀው በላይ ፍላጎት እንዳለ መረዳታቸውን ገልጸዋል። ሒደቱ አቶ ሚካኤል እንደሚሉት “የመንግሥት እና የግል አጋርነት (Public-Private Partnership) በኢትዮጵያ በተለይ በፋይናንስ ዘርፍ ሊሰራ እንደሚችል የሚያሳይ ነው።”
ከካፒታል ገበያው ድርሻ መግዛት የተፈቀደላቸው “ተቋማዊ ኢንቨስተሮች” ብቻ ናቸው። “ለግለሰቦች እኛም ብንፈልግ ክፍት አልተደረገም ነበር” ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዶክተር ጥላሁን የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ለምን ይኸን አቋም እንደያዘ አብራርተዋል።
“ገበያው ሲመሠረት በአንድ ዓመት በሁለት ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ትርፋማ ሆኖ ትርፍ መክፈል ስለማይችል በተለይ ደግሞ ግለሰብ ኢንቨስተሮች የተሰጠውን propspectus የማንበብ፣ የመረዳት፣ ትርፍ እና ኪሳራውን የመተንተንም አቅም ስለማይኖራቸው” ተቋማዊ ኢንቨስተሮች ብቻ እንዲሳተፉ መደረጉን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል።
ገበያው ሥራ ሲጀምር “ስትራቴጂካዊ የሆኑ ድጋፍ የሚያደርጉላቸውን ተቋማት ለመጋበዝ” የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያን 10 ወይም 15 በመቶ ድርሻው ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ ሲሰራ እንደነበር ገልጸዋል። ካፒታል ገበያው ሥራ ሲጀምር በኢትዮጵያ ሰነደ-ሙዓለ ንዋዮች ኢንቨስት ያደረጉ ባንኮች ተመዝግበው ድርሻዎቻቸውን ለሽያጭ እንዲያቀርቡ የገበያው ሥራ አመራሮች እና አማካሪዎች ፍላጎት አላቸው።
ለግብይቱ የሚያስፈልጉት እንደ ኢንቨስትመንት ባንኪንግ ያሉ አገልግሎቶች በማቅረብ የኢትዮጵያ ባንኮች ላቅ ያለ ሚና እንዲጫወቱም ይጠበቃል። ከካፒታል ገበያው ድርሻ በመግዛት 12 የግል የኢንሹራንስ ድርጅቶች ያሳዩት ተሳትፎም ለአቶ ሚካኤል እና ባልደረቦቻቸው ትልቅ ተስፋ የሰጠ ነው።
“በካፒታል ገበያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ትልቅ ሚና አላቸው” የሚሉት አቶ ሚካኤል በሌሎች ሀገሮች የጡረታ ፈንድ እና የመድን ዋስት አቅራቢ ድርጅቶች በአክሲዮንም ይሁን በዕዳ ገበያ ተቀዳሚ የረዥም ኢንቨስተሮች መሆናቸውን ገልጸዋል። ፈታኝ ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ ባለበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ድርጅቶች በካፒታል ገበያው “እንደዚህ አይነት ፍላጎት በማሳየታቸው እጅግ እኛ ከጠበቅንው በላይ ነው። ለካፒታል ገበያው የረዥም ጊዜ ስኬትም በጣም ጠቃሚ ነው” ሲሉ አቶ ሚካኤል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያዋን መልሳ ለማቋቋም ስትነሳ “አዋጪነቱን ለመፈተሽ እና የገበያውን አቅም ለመገንባት የቴክኒክ ድጋፍ ሲያደርግ” የቆየው እና መቀመጫውን በናይሮቢ ያደረገው ኤፍኤስዲ አፍሪካ በኢትዮጵያ ሰነደ-ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ድርሻ ከገዙ የውጭ ኩባንያዎች አንዱ ነው።
ከ60 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው የናይጄሪያ ኤክስቼንጅ ግሩፕ “በአፍሪካ የነቃ ግብይት ከሚካሔድባቸው የካፒታል ገበያዎች አንዱ” መሆኑን የገለጹት አቶ ሚካኤል በገበያው ከ150 በላይ ኩባንያዎች እንደተመዘገቡበት ተናግረዋል። የውጭ ኢንቨስተሮች ጭምር ከሚሳተፉበት የናይጄሪያ ኤክስቼንግ ግሩፕ የኢትዮጵያው ተቋም የቴክኖሎጂ እውቀት እና ክህሎት የመሳሰሉትን ሊያገኝ እንደሚችል አቶ ሚካኤል ተስፋ አላቸው።
በምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ገበያዎች የሚሰራው የኮሜሳ (COMESA) የንግድ እና የልማት ባንክ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ጋር ጭምር የሚሰራ ነው። ይኸ ባንክ መሠረተ-ልማትን ለመሳሰሉ ግዙፍ የካፒታል ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማቅረብ የብድር ሠነዶች ኬንያ እና ዩጋንዳን በመሳሰሉ ሀገሮች ለግብይት የሚያቀርብ ነው። ባንኩ ለኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ከፍ ያለ ጠቀሜታ የሚኖራቸው ተመሳሳይ አሰራሮች ሊያቀርብ እንደሚችል አቶ ሚካኤል ጥቆማ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ሥራ ሲጀምር ግብይቱ የሚመራበትን ሕገ-ደንብ ለሕዝብ ውይይት ይፋ አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪ ግብይት የሚካሔድበትን ቴክኖሎጂ ለመዘርጋት አቅራቢዎች የሚመርጥበት ደረጃ ላይ ነው። ተቋሙ “ግብይትን ተግባራዊ ለማድረግ ቁልፍ የሆነውን መሠረተ-ልማት አቅራቢ ድርጅቶች የቴክኒክ ግምገማ” ማጠናቀቁን አስታውቋል።
“ግብይት የሚካሔድበት ዋናው ቴክኖሎጂ automated trading system ይባላል። አቅራቢ ምርጫ ላይ ነን። እዚህ ሒደት ላይ የዓለም ባንክ እየረዳን ነው” ያሉት አቶ ሚካኤል “አቅራቢው ተመርጦ አንዴ ከገዛንው በኋላ የኢንቨስትመንት አማካሪዎች፣ የኢንቨስትመንት ባንኮች ፈቃድ ሲይዙ ቀጥታ ወደ [ኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ] ኤክስቼንጅ መጥተው አባል ይሆናሉ። አባል ከሆኑ በኋላ የግብይት ሥርዓቱን እንዴት እንደሚጠቀሙ፤ ደንበኛ ሲመጣ የልምምድ ግብይት ማካሔድ እንጀምራለን” ሲሉ በሚቀጥሉት ስድስት ገደማ ወራት ትኩረት የሚደረግበትን ሥራ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያው ሥራ ሲጀምር ቁጥጥር የሚያደርግበት የራሱ የቴክኖሎጂ መሠረተ-ልማት ለመዘርጋት አስር ኩባንያዎች ያቀረቡትን የጨረታ ሠነድ መመርመር ጀምሯል።
ሙዓለ-ንዋዮች በኤሌክትሮኒክ ሰነድ የሚቀመጡበት፣ ግብይት ሲከናወን ከገዢ ወደ ሻጭ የሚዘዋወሩበት ሴንትራል ሴኪዩሪቲስ ዲፖዚተሪ (Central Securities Depository) የተባለ መሠረተ-ልማት የመዘርጋቱን ሥራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለአሜሪካ ኩባንያ ሰጥቷል። “አቅራቢው ሞንትራል የተባለ ኩባንያ specification እየሰራ ነው። እሱም በዚህ ዓመት ይዘጋጃል” ያሉት አቶ ሚካኤል የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ሥራ ከመጀመሩ በፊት መጠናቀቅ እንደሚኖርበት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ሥራ ሲጀምር በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሕንጻ ላይ ገዥ እና ሻጭ የሚገናኙበት ቦታ (trading floor) ይኑረው እንጂ ግብይቱ ሙሉ በሙሉ ኤሌክትሮኒክ እንደሚሆን አቶ ሚካኤል ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ የካፒታል ገበያ ዲጂታል የሥልጠና ማዕከል የሚቋቋም ይሆናል። የኢትዮጵያ ሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ከመስከረም 2017 በኋላ ሥራ ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ሚካኤል ተናግረዋል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ