1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ትምህርትአፍሪቃ

የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ለምን ዝቅተኛ ሆነ?

ሰለሞን ሙጬ
ረቡዕ፣ መስከረም 14 2018

የ12ኛ ክፍል የተማሪዎች ውጤት ለምን ዝቅተኛ ሆነ? ኩረጃን ማስቀረት የትምህርት ሁሉን አቀፍ ጥራት መመዘኛ መሆን ይችላልን? ካልሆነ መፍትሔው ምንድን ነው?

የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ሕንጻ አዲስ አበባ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

የሕዝብ አስተያየት

This browser does not support the audio element.

 

በ2017 ዓ.ም ፈተና ከወሰዱ የ12ኛ ክፍል የመሰናዶ ተማሪዎች 8.4 በመቶ ተማሪዎች ብቻ 50 በመቶና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል። እንዲያም ሆኖ ሚኒስቴሩ የዓመቱ የፈተና ውጤት ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር «ለውጥ የታየበት» መሆኑንም ገልጿል። ለመሆኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ለፈተና ምዘና እየተቀመጡ እጅግ ጥቂቶች ብቻ የሚያልፉት ለምንድን ነው? መፍትሕውስ ? ተማሪ፣ አስተማሪ፣ ወላጅ እና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አነጋግረናል።

የትምህርት ሥራ ላይ ያለው መሠረታዊ ችግር ምንድን ነው?

የ4ኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ አስተያየት

«የፖሊሲ ለውጥ ሲመጣ ዋናው ኩረጃን ለማስቀረት በሚል ነበር። ግን እንደ ተማሪ ከእኔ የበለጠ ያጠኑ የነበሩ ልጆች ወድቀዋል ፈተና። መኮረጅ ያስቀራል የተባለው ነገር አልቀረም። ያሳዝናል ሦስት በመቶ አልፏል ተብሎ እንደ ስኬት ሲወራ ማየት፤ ያኔ ነው የኢትዮጵያ ትምህርት እንደወደቀ የምትረዳው። ትምህርት አሁን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ እየተጠቀሙት ያለው እንጅ ትምህርት አለ ብየ አላስብም። ምክንያቱም እኔ በጣም ትኩረት የማደርግ ታታሪ ተማሪ ነበርኩ። ከትምህርት ውጪ ምንም የማውቀው ነገር የለም። ስለዚህ ከእኔ እንደዚህ ዓይነት አስተያየት ከመጣ ምን ያህል ልጆች እንደተጎዱ ትረዳለህ።»

በትምህርት ዘርፍ ላይ የሠሩ ሰው አስተያየት

«ያለፉት 20፣ 30 ዓመት አካባቢ ያለው ችግር [የትምህርት ዘርፍ] ቶሎ ቶሎ የትምህርት ሥርዓቱ መቀያየሩ ነው። አንድ ትልቅ ነገር ይታየኛል። መሠረታዊ ነገር ስለሆነ ትምህርት ወዲያው ወዲያው መቀያየር የለበትም።»

የወላጅ አስተያየት

«ቀስ በቀስ ትምህርት ፖለቲካ ውስጥ ገባ። ያንን ደግሞ የትምህርት ሥርዓቱ ምን አደረገው በፖለቲካ እንዲመራ፣ ኩረጃ እንዲኖር፣ ሰዎች በቀላሉ ሳያውቁ ጢባ ጢቤ እንዲጫወቱበት ሆነ። በዚያ ላይ ደግሞ ለአስተማሪ የሚሰጠው ክብር እና ቦታ እየቀነሰ መጣ። ግብረገብ እና ሥነ ምግባራዊ ነገሮች እየወረዱ መጡ።»

የኢትዮጵያ ትምህርት ጥራት ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ መነጋገሪያነቱ ጨምሯል። ብዙዎች ተማሪዎች ከትንሽነታቸው ጀምሮ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጣቸው ያሳስባሉ። ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አስተያየት  

«መነሻው የመጀመርያው [የትምህርት ችግር] የትምህርት ፖሊሲው ነው። የትምህርት ፖሊሲው ከፍተኛ ችግር አለበት። ለምሳሌ በአሁኑ ሰዓት ትምህርት ቤት ላይ ፖለቲካ ነው እየተራመደ ያለው። በተለይ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ። ሁለተኛው ነገር ደግሞ የተማሪዎች የትምህርት ፍላጎት ማጣት። ለምሳሌ በቤተሰብ ደረጃ ላይ ሁለት ሦስት ወንድም ወይም እህት ተምረው የተቀመጡ አሉ። ሥራ ያልያዙ። ልጆች ያንን ያያሉ። ስለዚህ ሥራ አጥነት ስለበዛ እኔም ብማር ያ ነው የሚገጥመኝ፣ ዕጣ ፋንታየ ያ ነው የሚለው ነገር ስላላቸው የመማር ፍላጎታቸው ዜሮ እየሆነ ነው። ሌላኛው መምህራን የሚያስተምሩት ኢኮኖሚን እያሰቡ ነው። አንድ መምህር ክፍል ውስጥ ገብቶ ለማስተማር በቀን ሦስት ጊዜ ዳቦ መብላት አለበት። በአሁኑ ሰዓት ያለው የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ ያንን የሚያሳካ አይደለም።»

የሌላ ወላጅ አስተያየት

«ይህ ኩረጃ የተባለውን ነገር መንግሥት ጥሩ አድርጎ ነው የሠራበት። ለምን በኩረጃ ወደ ሥራው ዓለም በሚሄዱበት ሰዓት ሥራዎች በጣም እየተበደሉ እና ከአቅም በታች እየሆኑ ይታያል። ተቋማቶች በብዛት ችግር የሆነባቸው የትምህርት አሰጣጡ ላይ ነው። ትምህርቱ ከተስተካከለ መዋቅሩም እየተስተካከለ ይመጣል።»

ለዘላቂ መፍትሔው ምን ይደረግ?

«ከመሠረቱ ከመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ በማስተማር ነው እንጂ የሚሻሻለው ፈተና ላይ ብቻ አተኩሮ ይህን ያህል ወደቀ፣ ይህን ያህል አለፈ በሚል ሊታይ አይገባም። ያንን ለማሻሻል ደግሞ የትምህርት ሥርዓታችንን ብናስተካክል [ይበጃል] ።»

ያሉ እንዳሉ ሁሉ፤ «ሦስት በመቶ አለፈ ማለት ሦስት በመቶው ብቻ ነው ጎበዝ ማለት አይደለም። በጣም ተምረው ጎበዝ የሆኑ ልጆች በጭንቀት የወደቁ አሉ። ስለዚህ የእነዚህ ልጆች ሀሳብ መሰማት አለበት።» የሚል አስተያየት የሰጡም አሉ።

ሌላው አስተያየት ሰጪም «መምህራን ላይ መሠራት አለበት። መምህራን በኢኮኖሚ እየደቀቁ ነው። በተለይ አዲስ አበባ ላይ መኖር እየተቻለ አይደለም። መምህር ለመሆን መቼ ነው ተሳስቼ የገባሁት ትላለህ አንዳድ ጊዜ።» በማለት ሃሳባቸውን አጋርተዋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW