1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል

ረቡዕ፣ ግንቦት 23 2015

የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ችግር ፈቺ ያልሆነ፣ የሀገሪቱን ኑሮ እና ተጨባጭ ጉዳዮች የማይመለከት፣ ከውጪ የተገለበጠ መሆኑ በውጤትም ሆነ በጥራት ማሽቆልቆል እየታየበት መቀጠሉን የትምህርት ባለሙያዎች ተናገሩ። ትምህርት ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ውስጥ ከጠቅላላ ትምህርት ሰጪ 47 ሺህ ገደማ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸው የላቁት አራት ናቸው ማለቱ ተሰምቷል።

Äthiopien Bildungsministerium gibt ESLCE Endergebnis bekannt
ምስል Solomon MUCHIE/DW

አነጋጋሪው የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል

This browser does not support the audio element.


የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ችግር ፈቺ ያልሆነ፣ የሀገሪቱን ኑሮ እና ተጨባጭ ጉዳዮች የማይመለከት፣ ከውጪ የተገለበጠ መሆኑ በውጤትም ሆነ በጥራት ማሽቆልቆል እየታየበት መቀጠሉን የትምህርት ባለሙያዎች ተናገሩ። ባለሙያዎቹ የዚህ ጥሩ ማሳያ ያደረጉት በኢትዮጵያ አጠቃላይ ትምህርት ከሚሰጥባቸው 47 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በተሻለ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት በጣት የሚቆጠሩ ብቻ መሆናቸው ከሰሞኑ በትምህርት ሚኒስቴር መነገሩን ነው።
አስተማሪነት ከአመላመሉ ጀምሮ ዝቅተኛ ውጤት ያላቸው የሚገቡበት፤ እና ሙያው ለበረታ የኑሮ ጫና የተጋለጠ እየሆነ መምጣቱ የትምህርት ጥራት ለመጓደሉ ዋንኛ ችግር መሆኑን የገለፁት ባለሙያዎቹ የትምህርት ሥርዓት ለውጥ አለመኖሩንም እንደ ሌላ መሠረታዊ ችግር ይጠቅሳሉ። 

ትምህርት ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ውስጥ ከጠቅላላ ትምህርት ሰጪ 47 ሺህ ገደማ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸው የላቁት አራት ናቸው ማለቱ ተሰምቷል። ቀደም ብሎ ለዘንድሮው ዓመት የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ለፈተና ከተቀመጡት 909 ሺህ ተማሪዎች ማለፊያ ያመጡት 30 ሺህ ያልሞሉ መሆናቸውን ሲገልጽ ድንጋጤ ፈጥሮ ነበር። የዚህ ችግር ሥረ መሠረቱ ምንድን ነው ብለን የጠየቅናቸው የትምህርት ባለሙያው ዶክተር ሰለሞን በላይ በዋናነት አስተማሪነት ላይ የተከሰተው ውድቀት ነው ይላሉ።
«መምህራን ካመላመላቸው ጀምር አሰለጣጠናቸው፣ እንደገና ደግሞ አመዳደባቸው እያሽቆለቆለ በመምጣቱ» መሆኑን ጠቅሰዋል። ዝቅተኛ ውጤት ያላቸው ሰዎች አስተማሪ እንዲሆኑ የሚያደርግ ምልመላ መኖሩ፣ መምህራን ዝቅተኛ ተከፋይ መሆናቸው፣ ወደ ሌሎች ሙያዎች ትኩረት ማድረግ እና አስተማሪ የመሆን ፍላጎት እያሽቆለቆለ መምጣት ግልጽ ምክንያት መሆናቸውን ገልፀዋል።
ያነጋገርናቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪም ይህንኑ ምክንያት ይጋራሉ።
«አማራጭ ያጡ ሰዎች ናቸው መምህር እየሆኑ ያሉት» በማለት ያለውን ተጨባጭ እውነታ አስረድተዋል። ለትምህርት ጥራት መጓደል ብዙ ምክንያቶችን የሚጠቅሱት ያነጋገርኳቸው የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ተማሪዎች ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎች የትምህርት በአግባቡ አለመሰጠትን አንዱ ምክንያት አድርገው ይገልጻሉ።

የትምህርት ሚኒስቴር አርማምስል Hanna Demisse/DW

የትምህርት ባለሙያው ዶክተር ሰለሞን በላይ እንደሚሉት የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት «ከቅኝ ግዛት» ሊላቀቅ ይገባል ነው።
ትምህርት ሚኒስቴር ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የሥራ አፈፃፀም ዘገባው በትምህርት አሰጣጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች አምስት አይሆኑም ብሏል። ከ47 ሺህ ትምህርት ቤቶች። የዚህ ምክንያት ምንድን ነው የሚለውን እንዲመልሱልን ለሚመለከታቸው የሚኒስቴሩ ባልደረቦች ደጋግመን ብንደውልም በስልክ መዘጋትና አለመነሳት ምክንያት ማካተት አልቻልንም። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስቀድሞ እንዳለው ግን ችግሩን ለመቅረፍ «ሀገር አቀፍ የትምህርት ዘመቻ» በቅርቡ ይጀመራል።

 ሰሎሞን ሙጬ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW