1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የአስር ዓመታት ዘመቻ ወደ ሶማሊያ

ረቡዕ፣ የካቲት 23 2008

ለአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር /አሚሶም/ ወታደሮችን ካዋጡ አገሮች መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ሶማሊያ መላኳ ተሰምቷል።

Somalia Soldaten
ምስል dapd

[No title]

This browser does not support the audio element.

አፍሪካ ኢንተለጀንስ የተሰኘው መጽሔት በየካቲት 11/2008 ዓ.ም እትሙ ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ማሰማራቷን አስነብቧል። ከሶስት ቀናት በኋላ (የካቲት 14/2008 ዓ.ም. ደግሞ) ከጽንፈኛው የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ቅርበት እንዳለው የሚነገርለት የሸበሌ ራዲዮ ከመንገድ ላይ የተቀበረ እና በርቀት መቆጣጠሪያ በፈነዳ ቦምብ በአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር (AMISOM) ስር የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ጉዳት እንደደረሰባቸው ገለጠ። እኒህ አይነት ዘገባዎች ላለፉት አስር ዓመታት በተደጋጋሚ ተደምጠዋል።

በጎርጎሮሳዊው 2006 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ጦር የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ሕብረትን ለመውጋት ወደ ሶማሊያ በዘመተበት ወቅት እንደ ወራሪ ተቆጥሮ ውግዘት ገጥሞትም ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ ጆርጅ ማሰን ዩኒቨርሲቲ የግጭት ትንተና እና አፈታት ትምህርት ቤት የድህረ-ምረቃ ተማሪ የሆኑት አቶ አለማየሁ ፈንታው በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ አለመረጋጋት ሲፈጠር አገሪቱ ጦሯን ወደ ሶማሊያ የማዝመት ልምድ ከብሔራዊ ደህንነት ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ይናገራሉ።

ምስል picture-alliance/dpa

በተ.መ.ድ. የሶማሊያ የቀድሞ አምባሳደር የነበሩት አቡበከር አርማን እና በኳታር ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑትን አፍያሬ ኤልሚን የመሳሰሉ የፖለቲካ ተንታኞች ዩናይትድ ስቴትስ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሶማሊያን ለማረጋጋት የተከተሉትን ስልት አብዝተው ይነቅፋሉ። ተንታኞቹ የኢትዮጵያ እና ኬንያን ጣልቃ ገብነት አበረታቷል ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ ስልት የጎሳ ፖለቲካን በማበረታታት ማዕከላዊ መንግስቱን አሽመድምዷል ሲሉ ይወቅሳሉ። አቶ አለማየሁ ፈንታው የሶማሊያ መንግስት የኢትዮጵያ ጦር በአገሪቱ እንዲቀሳቀስ እና የሶማሊያን ጦር እንዲያግዝ ፈቃድ በመስጠቱ ጉዳዩን ውስብስብ ቢያደርገውም በዓለም አቀፍ ህግጋት ፊት ስህተት አያደርገውም ባይ ናቸው።

በአስሩ ዓመታት ሶማሊያ «የመረጃ ጦርነት» ጭምር የተከፈተባት እንደሆነች አቶ አለማየሁ ይናገራሉ። በአስሩ ዓመታት ዘመቻ በኢትዮጵያ ጦር ላይ የደረሰ ጉዳት በግልጽ አይታወቅም። በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ተወካዮች ምክር ቤት ስለ ሶማሊያ ዘመቻ የተጠየቁት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ « የሞተው የቆሰለው ...ይህን ዝርዝር በሚመለከት ምክር ቤቱ በዚህ ደረጃ እያንዳንዱ ወታደር፤እያንዳንዱ ፖሊስ በእያንዳንዱ ግጭት ምን ያህል ቆስለዋል? ምን ያህል ሞተዋል በሚል ደረጃ ማወቅ ለስራው የሚያስፈልገው አይመስለኝም። በዚህ ደረጃም ሪፖርት የማቅረብ ግዴታም ያለኝ አይመስለኝም።» ሲሉ ነበር የመለሱት። ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ስለደረሰው ጉዳት መንግስት መረጃ ተጠይቆም ሰጥቶም አያውቅም።

በሶማሊያ ጦርነት የሚሳተፉ አካላት ሆን ብለው የተሳሳተ መረጃ መስጠት እና ተገቢውን ደግሞ የመደበቅ ድርጊት እንደሚታይባቸው ያስረዱት አቶ አለማየሁ ይህ ልምድ የጦርነቱ አካል መሆኑንም ጨምረው ገልጠዋል።

የአውሮጳ ህብረት ለአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ በ20% መቀነሱን አስታውቋል። የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ግን አፍሪቃውያኑ አገሮች ሶማሊያን ለማረጋጋት «በደም እና በስጋ» ዋጋ እየከፈሉ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለዋል። ለአሚሶም ወታደር ያዋጡ አገሮች በዕለተ-እሁድ በጅቡቲ ተገናኝተው የሶማሊያ ተልዕኮዎችን ስለማጠናከር ቢመክሩም ተልዕኮው የሚያበቃበት ጊዜ ስለ መኖሩ ግን ያሉት ነገር የለም።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW