ኢንቨስትመንትን ለመሳብ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 25 2018
የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ያስተዋወቀ መድረክ በፓሪስ
የፈረንሳይና የአውሮፓ ባለሐብቶችንና ኩባንያዎች መዋዕለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ፈሰስ እንዲያደርጉ እና ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ አማራጮችን ያስተዋወቀ ኢንቨስትመንት ጉባኤ በትላንትናው ዕለት በፈረንሳይ ዋና ከተማ በፓሪስ ተካሂዷል።
ይህ የፈረንሳይ ኢንተርፕራይዞች ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ከአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ባዘጋጀው መድረክ ላይ ለፈረንሳይ ባለሐብቶችና ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አዋጪ ናቸው የተባሉ የኢንቨስትመንትአማራጮች የቀረቡ ሲሆን በተለይም በዋነኝነት የግንባታ ሥራ እንደሚጀምር የሚጠበቀውና በርካታ ገንዘብም ይፈስበታል ተብሎ የተነገረለት የቢሾፍቱ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት የገንዘብ አበዳሪዎችንና በግንባታ ሥራ ላይ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ የፈረንሳይና የአውሮፓ ኩባንያዎች ቀልብ የሳበ እንደነበረ ተነግሯል።
በዚሁ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ጌድዎን ጢሞቲዎስ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ የመንግስት መስሪያቤቶች የተውጣጡ የሥራ ሐላፊዎች የታደሙበት ነበር። እንዲሁም ከአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽንና ከፈረንሳይ መንግስት በርካታ የኩባንያ ተወካዮችና ሐላፊዎች መገኘታቸውን ታውቋል።
በመድረኩ የተሳተፉት የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ለዶይቸቨለ በሰጡት አስተያየት መድረኩ ኢትዮጵያ የፈረንሳይ አጋርና ተደራሽ የኢንቨስትመንት አማራጭ መሆንዋን ያሳየ እንደነበር ገልጸዋል።
« በጣም ስኬታማ ነው። የቢሾፍቱ አለምአቀፍ ኤርፖርት ፋይናንሲንግም ሆነ የተሳታፊ ኮንትራክተሮች ፍላጎትን ለማነቃቃት ነበር ሲፈለግ የነበረው። በዚህ ረገድ ጥሩ ውይይት ነው የነበረው። ኤርባስ በከፍተኛ ደረጃ ይህን ልማት ይደግፈዋል፤ የአውሮፓ ሕብረት ይደግፈዋል፤ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ይደግፈዋል፤ ሌሎች የአውሮፓ ባንኮችም እንዲሳተፉ የማበረታት ሥራ ሰርተናል። ብዙ የአውሮፓ ኩባንያዎች የተለያዩ ቴክኖሎጂ ያላቸው በዚህ ኤርፖርት ልማት ላይ መሳተፍ ይፈልጋሉ።»
የጉባኤው ተሳታፊዎች ምን አሉ?
የጉባኤው ተሳታፊዎች በአገልግሎት አሰጣጥና የታክስ አስተዳደር በተመለከተ ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን ለዚህ እየተደረጉ ያሉ የማሻሻያ ለውጦችን በተመለከተ ገለጻ እንደተደረገላቸው ነው ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የገለጹት።
« አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች ያነሳሉ። ከታክስ አስተዳደር፤ ከከስተምስ አስተዳደርሪፎርሞችእየተደረጉ መሆኑንና ውጤቶች እየመጡ እንደሆነ ያውቃሉ ግን የበለጠ እንዲሻሻሉ የሚፈልጓቸው ጉዳዮች አሉ። በዚህ ላይም ተወያይተናል። ስለዚህ ከጀመርነው የኢኮኖሚ ሪፎርም አንጻርና ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አንጻር በጣም ጥሩና ፍሬያማ ውይይት ነው የተካሄደው።»
የሰላም ጸጥታ ጉዳይ
የውጭ ባለሐብቶች በሌላ ሐገር መዋዕለ ንዋያቸው ለማፍሰስ በሐገሪቱ ያለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የታክስና የጉምሩክ አስተዳደር፤ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና ተደራሽነት እና የመሳሰሉትን ስለመኖራቸው ማረጋገጥ ይፈልጋሉ። ከዚዚህ ባልተናነሰ መልኩ ደግሞ የጸጥታና ደሕንነት ጉዳይም ያሳስባቸዋል። በዚህ መልክ ባለሐብቶቹ ያነሱትን ጥያቄ አስመልክተው አቶ አሕመድ ሽዴ ተከታዩን ብለዋል።
« ብዙ ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያ ውስጥ እየሰሩ ነው ያሉት። በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ያለው ችግር በኢንቨስትመንት ላይ ጉዳት ያመጣል ምንም ጥርጥር የለውም። ያሉት ችግሮች በመላው አገሪቱ አደለም ያሉት፤ እሱም የበለጠ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመጣ መንግስት ቁርጠና ነው። ሰላም እንዲመጣ ከሁሉም ወገኖች ጋር ተነጋግሮ ለመፍታት ሁልጊዜ ዝግጁ ነው። አጠቃላይ ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አስጊ የሆነ ነገር የለም። ይሄም ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ነው የሚፈጥረው። በዚህ ላይም ጥሩ ተስፋ ነው ያላቸው። የኢትዮጵያ ሰላም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፤ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠርም ጥሩ እምነት ነው እየተፈጠረ ያለው። በዚህ ደረጃ ብዙ ስጋት የለባቸውም።»
የፈረንሳይ ኢንተርፕራይዞች ዓለምአቀፍ ንቅናቄ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፍሊፕ ጎቴ ለደይቸቨለ በሰጡት አስተያየትም ፈረንሳይ አሁን ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የንግድ ትስስር እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ሃይማኖት ጥሩነህ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ