1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር የሚያስከፍለው ዋጋ በማን ላይ ይበረታል?

Eshete Bekele
እሑድ፣ ሐምሌ 21 2016

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ “በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት” ተግባራዊ ልታደርግ እንደሆነ ገልጸዋል። የኤኮኖሚ ማሻሻያ አካል የሆነው ውሳኔ የብርን የመግዛት አቅም በከፍተኛ መጠን ያዳክማል። ይኸ ውይይት የኤኮኖሚ ማሻሻያው የሚያስከፍለው ዋጋ ማን ላይ ይበረታል? ሲል ያጠይቃል

IWF Kredit, Symbolbild
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ኢትዮጵያ በጠየቀችው ብድር ላይ ለመወያየት ነገ ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ብሎምበርግ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የመረጃ ምንጮች ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።ምስል Maksym Yemelyanov/Zoonar/picture alliance

ውይይት፦ የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር የሚያስከፍለው ዋጋ በማን ላይ ይበረታል?

This browser does not support the audio element.

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ኢትዮጵያ በጠየቀችው ብድር ላይ ለመወያየት ነገ ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ብሎምበርግ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የመረጃ ምንጮች ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። ስብሰባው መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው አበዳሪ ተቋም ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው የኢትዮጵያ መንግሥት እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በባለሙያዎች ደረጃ ከሥምምነት ሳይደርሱ የተቀጠረ በመሆኑ ብሎምበርግ “ያልተለመደ” ብሎታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አምስት ዓመታት ፈጅቷል ያሉት ድርድር ወደ መገባደጃው ደርሷል የሚል እምነት እንዳላቸው የ2017 በጀት በጸደቀበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ተናግረው ነበር። ለድርድሩ መራዘም የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት “አስቸጋሪዎች” መሆናቸውን በምክንያትነት ቢጠቅሱም ዝርዝር ጉዳይ አልተናገሩም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አንዳንድ ወዳጅ አገሮቻችን ባደረጉልን ድጋፍ አብዛኛው ሐሳቦቻችን ተቀባይነት ያገኙ ይመስላል” ሲሉ ተደምጠዋል። ድርድሩ ከተጠናቀቀ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ 10.5 ቢሊዮን ዶላር በመጪዎቹ ዓመታት እንደምታገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር አካል የሆኑ የተለያዩ አዋጆች ባለፉት ወራት ባናት ባናቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቀዋል። የወጪ ንግድ የቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓት ማሻሻያ አዋጅ እና በገበያው ፓስታን የመሳሰሉ ሸቀጦች ዋጋ እንዲንር ያደረገው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ሰኔ 27 ቀን 2016 የጸደቁ ናቸው።

የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚፈቅድ የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤቱ ቀርቧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዋጅ የሚያሻሽል ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ቀደም መንግሥት ለነዳጅ ያደርግ የነበረውን ድጎማ በሒደት እያነሳ ሲሆን የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ጸድቆ ሥራ ላይ ውሏል።

የቴሌ-ኮም ገበያው ለውድድር ተከፍቶ ሳፋሪ ኮም በኢትዮጵያ ሥራ ላይ ይገኛል። በማሻሻያው ላይ የሚደረግ ድርድር የኢትዮጵያ መንግሥት የብርን የመግዛት አቅም በከፍተኛ መጠን እንዲያዳክም ሊያስገድድ እንደሚችል ይጠበቃል።

ለመሆኑ የኤኮኖሚ ማሻሻያው የሚያስከፍለው ዋጋ በማን ጫንቃ ላይ ይወድቃል? በኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሚና ምንድነው?

በዚህ ውይይት የገንዘብ አስተተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ፣ በዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት ዶክተር ቀልቤሳ መገርሳ እና በዩናይትድ ኪንግደም ብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ ሥር በሚገኘው ፔሪቮሊ አፍሪካ ጥናት ማዕከል ተመራማሪው ዶክተር ኢዮብ ባልቻ ተሳትፈዋል።

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW