የኢትዮጵያ የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ልማት ፕሮጀክት እንደ ቀደሙት ሙከራዎች ያሰጋል?
ረቡዕ፣ መስከረም 28 2018
ባለፈው ሣምንት የተጀመረውን የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ልማት እና የጎዴ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ታላቅ ታሪክ” ብለውታል። “በሶማሌ ክልል ላለፉት 100 ዓመታት ተደምሮ 10 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት አልተደረገም” ያሉት ዐቢይ በፕሬዝደንትነት የሚመሩት ብልጽግና ፓርቲ “ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ልማት ይገባቸዋል፤ ሁለተኛ አይደሉም፤ አጋር አይደሉም። የሀገር ምሰሶ ናቸው” ብሎ እንደሚያምን ተናግረዋል።
የሶማሌ ክልልን ይመራ የነበረውን ፓርቲ እንደ “አጋር” ይቆጥር የነበረውን የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ወርፎ መንግሥታቸውን አሊያም ፓርቲያቸውን ያወደሰ ንግግራቸው ግን የሰላም ጉዳይ ጥንቃቄ እንደሚፈልግ ማሳሰቢያ የሰጡበት ጭምር ነበር።
“ብልጽግና እንደዚህ ያለውን ኢንቨስትመንት ስላመጣ ጠብቃችሁ ከፍሬ እንድታደርሱት” የሚል መልዕክት ለሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሁመድ ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሰላማችሁን እንድትጠብቁ ፤ እነዚህን ኢንቨስተሮች እንድትንከባከቡ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና መንግሥታቸው ይፋ ያደረጓቸውን ዕቅዶች ግን የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) አንድ አንጃ በጽኑ ተቃውሟል። መቀመጫውን ከኢትዮጵያ ውጪ ያደረገው እና አብዲራሕማን ማሕዲ የሚመሩት የኦብነግ ክንፍ ዐቢይ ፕሮጀክቶቹን ይፋ ያደረጉት “የመሬቱ እና የሐብቱ ሕጋዊ ባለቤት ከሆነው የሶማሌ ሕዝብ ጋር ሳይመካከሩ፣ ፈቃደኝነቱን ሳያገኙ እና ሳያሳትፉ” እንደሆነ መስከረም 6 ቀን 2018 ባሠራጨው መግለጫ ኮንኗል።
የቀድሞው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባል ዶክተር አብዲ መሐመድ ቡባል “ይኸ ፕሮጀክት ከመጀመሪያ ጀምሮ ሲሰራ እስካሁን የአካባቢው ሕዝብ ተሳትፎ አያውቅም” ሲሉ ይናገራሉ። በፕሮጀክቱ ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች “የተለያዩ ጉዳቶች፣ በሽታዎች እና ረሐብ” እንደገጠማቸው የሚናገሩት ዶክተር አብዲ በአካባቢው በሚሠፍረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሳቢያ “አርብቶ አደሮች ይጠቀሙባቸው የነበሩ የውኃ ጉድጓዶች መበላሸታቸውን” እና “ሕዝቡ ከአካባቢው እንዲርቅ” መገደዱን ይናገራሉ።
“ከመከላከያ ሠራዊት እና ከሠራተኞቹ መካከል የአካባቢው አንድ ሰው የለም” የሚሉት ፖለቲከኛ “ቅርብ ያሉትን ገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ስናነጋግር ወይም ከእነሱ የምንሰማው መከላከያው ያጠቃቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል። ዶክተር አብዲ “ፕሮጀክቱ ለተገፋው የሶማሌ ሕዝብ የሚሠራለት ሳይሆን አዲስ እና ተደራራቢ ችግሮችን ያመጣል” የሚል ሥጋት አላቸው።
በሶማሌ ክልል ለረዥም ዓመታት የተደረጉ የነዳጅ ፍለጋ እና ልማት ጥረቶች “ከአመጽ እና ከማፈናቀል ጋር የተሳሰሩ” እንደሆኑ ዶክተር ጁዌርያ አሊ ከሁለት ዓመታት በፊት ያሳተሙት ጥናት ያሳያል። የኢትዮጵያ መንግሥት እና የውጪ ኩባንያዎች ከኦጋዴን ሸለቆ የሚገኘውን የነዳጅ ክምችት ለማውጣት ያደረጓቸው ሙከራዎች ያስከተሏቸውን ተፈጥሯዊ ችግሮች አርብቶ አደር የሆነው የአካባቢው ነዋሪ ለረዥም ዓመታት ለመጋፈጥ ተገዷል።
በነዳጅ ፍለጋ ወቅት “ከባድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተፈጽመዋል” የሚሉት ዶክተር ጁዌርያ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር መጋፈጣቸውን፣ መተዳደሪያዎቻቸው መውደማቸውን፣ መሬታቸውን ለመልቀቅ እና ለመፈናቀል መገደዳቸውን ያስረዳሉ።
በብሪታኒያ ዌስትሚኒስትር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ጁዌርያ “ሶማሌዎች እነዚህ የተፈጥሮ ሐብቶች ለራሳቸው እና ለሀገሪቱ የተሻለ አኗኗር እጅግ ጠቃሚ መሆናቸውን ይገነዘባሉ። ጥያቄው ‘ሐብቱ ተቆፍሮ መውጣት አለበት’ ‘የለበትም’ ወይም ‘ይህ ፕሮጀክት መጀመር አለበት’ ‘የለበትም’ የሚለው አይደለም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
“ጥያቄው ‘እንዴት እና በምን ዐይነት መንገድ?’ የሚለው ነው” የሚሉት ዶክተር ጁዌርያ “የፕሮጀክቱ ስኬት በማኅበረሰቦች አቀባበል” እንደሚወሰን ያስጠነቅቃሉ። “ሒደቱ ግልጽ እና አካታች እንዲሆን፤ በኢትዮጵያ የልማት አጀንዳ ከላይ ወደ ታች የሚወርድበትን ልማዳዊ አሠራር ለመቀየር የአካባቢውን ማኅበረሰብ በምክክር ማሳተፍ እጅግ ጠቃሚ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በሶማሌ ክልል የነዳጅ ፍለጋ እና ቁፋሮ የተጀመረው በዘውዳዊው ሥርዓተ-መንግሥት ሲንክሌር ኦይል ኮርፖሬሽን በተባለ የአሜሪካ ኩባንያ አማካኝነት ነው። በተለይ በካሉብ እና ሒላላ የተፈጥሮ ጋዝ ለማውጣት የጀርመን፣ የሶቭየት ኅብረት፣ የዮርዳኖስ፣ የቻይና እና የማሌዥያ ኩባንያዎች ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ቾንዩዋን ፔትሮሊየም ኤክስፕሎሬሽን (Zhongyuan Petroleum Exploration) የተባለ የቻይና ኩባንያ በደገሐቡር ዞን የነዳጅ ፍለጋ በሚያከናውንበት ቦታ ላይ በሚያዝያ 1999 የኦብነግ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት 65 ኢትዮጵያውያን እና ዘጠኝ የቻይና ዜጎች ተገድለው ነበር። ከጅግጅጋ በ100 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በነዳጅ ፍለጋ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሠራተኞች በተኙበት በተፈጸመው ጥቃት ሌሎች ሰባት ቻይናውያን ታግተው ተወስደዋል።
ያመለጠ ዕድል?
ለረዥም ዓመታት ከኢሕአዴግ መንግሥት ጋር ሲዋጋ የቆየው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን እንደያዙ በነሐሴ 2010 ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ነበር። የዐቢይ መንግሥት እና ኦብነግ የሰላም ሥምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ኢትዮጵያ በጦርነት እና ግጭት ስትታመስ የሶማሌ ክልል የተሻለ መረጋጋት አግኝቷል።
ነገር ግን ባለፈው ሚያዝያ 2017 ግንባሩ ለሁለት የተከፈለ ሲሆን አብዲራሕማን ማሕዲ የሚመሩት ክንፍ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ሥምምነቱን እንደተጣሰ በተደጋጋሚ ይወነጅላል።
የግንባሩ ለሁለት መከፈል የኢትዮጵያ መንግሥት ኦብነግን ለማዳከም የሚያደርገው ጥረት አካል እንደሆነ የሚተቹት ዶክተር አብዲ መሐመድ ቡባል በሒደቱ ግን የሶማሌ ክልል ያጣው ዕድል እንዳለ ይናገራሉ። “ብልጽግና በሰላማዊ መንገድ ለሀገር እና ለልማት የሚሠራ ድርጅት ቢሆን ኖሮ እነዚያን ዕድሎች ይጠቀም ነበር” ሲሉ ይተቻሉ።
አብዲራሕማን ማሕዲ የሚመሩት የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ክንፍ በሶማሌ ክልል የተጀመረው የኦጋዴን ጋዝ ልማት ፕሮጀክት እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል። በፕሮጀክቱ የሚሳተፉ ባለወረቶች እና የውጪ ኩባንያዎች “በሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና የአካባቢ ውድመት ተባባሪ” እንደሚያደርጋቸው ያስጠነቀቀው ኦብነግ “በስቃይ እና አፈና ላይ የተገነባ ልማት” እንደማይቀበል አስታውቋል።
በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦብነግ መካከል የተፈጠረው መቃቃር ከተወሳሰበው የቀጠናው ፖለቲካ ጋር ተደማምሮ ሌላ የትጥቅ ግጭት ይቀሰቀስ ይሆን? የሚል ሥጋት የሚያጭር ነው።
“እኛን ማንም ሊያቆመን አይችልም”
ዶክተር አብዲ ኢትዮጵያ ከግብጽ እና ከኤርትራ ጋር ያላት የሻከረ ግንኙነት እና ከሶማሊያ ጋር ያለው “ወጣ ገባ ሁኔታ” “ወደ ግጭት የመሔድ ሁኔታ የሚያፋጥን ነው” የሚል አተያይ አላቸው። ከዚህ በተጨማሪ በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች ያለው ነባራዊ ሁኔታ ተመሳሳይ ሥጋት የሚያጭር እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር አብዲ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኘው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር አንጃ በሀገር ውስጥ ከመንግሥት ጋር ከሚዋጉ ኃይሎች ጋር ጥምረት ፈጥሮ “ወደ ትጥቅ ትግል የመግባት ሁኔታው ከፍተኛ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሶማሌ ክልል ባለሥልጣናት ሰላማችሁን ጠብቁ ቢሉም የቀጠናው ውጥንቅጥ ግን የሚያሰጋቸው አይመስልም። “እኛን ማንም ሊያቆመን አይችልም” ያሉት ዐቢይ “የኢትዮጵያን ብልጽግና እናረጋግጣለን። የኢትዮጵያን የወደብ ባለቤትነት እናረጋግጣለን። የኢትዮጵያን ልማት እናረጋግጣለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
ባለፈው ሣምንት ይፋ የተደረገውን “የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ልማት የመጀመሪያ ምዕራፍ” ግንባታ ያከናወነው እና ቀጣዮቹን የሚሠራው ጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ (GCL) የተባለ የቻይና ኩባንያ ነው። ኩባንያው ከዚህ ቀደም የቻይና መንግሥት ንብረት ከሆነው ከቻይና ፖሊ ግሩፕ ኮርፖሬሽን ጋር ባቋቋመው ፖሊ-ጂሲኤል የተባለ ኩባንያ አማካኝነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን እንደያዙ ነዳጅ ማውጣት መጀመሩን አስታውቆ ነበር።
ይሁንና “የሚጠበቅበትን ሥራ” አላሳካም በሚል የተሰጠው የነዳጅ የፍለጋ እና የልማት ውል መስከረም 11 ቀን 2015 ላይ መሰረዙን መንግሥት አስታዉቆ ነበር። የማዕድን እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሐብታሙ ተገኝ የቻይናው ኩባንያ ወደ ሥራው የተመለሰው “በአዲስ መልኩ [ውል] በመፈራረም” እንደሆነ ተናግረዋል።
“የፍለጋ ጥናቱን ከጀመርን ከ85 ዓመታት በኋላ የነዳጅ ጉድጓድ ቁፋሮዎችን ከጀመርን ደግሞ ከ53 ዓመታት በኋላ በአንድ ዓመት ከሁለት ወራት ፈጣን ግንባታ የመጀመሪያውን ምዕራፍ የኦጋዴን ጋዝ ልማት ለሀገራችን ገበያ ለማቅረብ በቅተናል” ሲሉ ኢንጂኔር ሐብታሙ ገልጸዋል።
ከሒላላ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ከጎዴ አቅራቢያ የሚካሔደውን የነዳጅ ማጣሪያ ግንባታ በሁለት ምዕራፎች ለማጠናቀቅ ታቅዷል። የመጀመሪያው ምዕራፍ በ24 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ባለፈው ሣምንት በይፋ ሥራ የጀመረው የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት በዓመት ከ110 ሚሊዮን ሊትር በላይ የማምረት አቅም እንደሚኖረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ዐቢይ እንዳሉት 1,000 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ያመነጫል።
የመንግሥት ባለሥልጣናት የናይጄሪያዊው ባለጠጋ አሊኮ ዳንጎቴ ንብረት የሆነው ዳንጎቴ ግሩፕ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጋር በሽርክና የሚገነባው የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ሀገሪቱን ከሸማችነት ያላቅቃል የሚል ተስፋ አላቸው።
ዶክተር ጁዌርያ ግን ፕሮጀክቱ “የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከማጉላት ባሻገር ተያይዘው ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን መወያየት ያስፈልጋል” የሚል አቋም አላቸው። “የቀደሙ ችግሮችን የበለጠ እንዳያባብሱ እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል ማሰብ አለብን” የሚሉት ዌስሚኒስትር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ “መረጃ በቀላሉ እንዲገኝ ማቅረብ፣ በማኅበረሰቡ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ፣ አካታችነትን ማረጋገጥ” እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
“የተፈጥሮ ሐብቶች በሕዝቦች መብቶች፣ የኑሮ መሠረቶች እና የወደፊት ዕጣ-ፈንታ ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች ጥብቅ መሠረት በመሆኑ ቁልፍ የግጭት መነሻ ሆኖ ቆይቷል” የሚሉት ዶክተር ጁዌርያ አሊ በኦጋዴን የተጀመረው የተፈጥሮ ጋዝ ልማት “በብልኃት እና በጥንቃቄ መያዝ” እንዳለበት መክረዋል።
አርታዒ ፀሀይ ጫኔ