የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ከዓለም ሕግ አኳያ
ዓርብ፣ መስከረም 9 2018
“በኢትዮጵያ እና በህንድ መካከል ድልድይ እንጂ ዳገት አልነበረም በታሪካችን፤ ዛሬ የእኛ የሆነውን ቀይ ባህር መልሶ ለመጠየቅ የሚሰጋ የሚጠራጠር ትውልድ መፈጠሩ የስነልቦና ስብራት አካል ነው፤ እኔ ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ ኢትዮጵያ ትችላለች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዚህ ሳምንት “የመደመር መንግስት” የተባለውን መጸሃፋቸውን በሚያስመርቁበት ወቅት “አይቀሬ” ስላሉት የኢትዮጵያን ወሰን ወደ ቀይባህር የመመለስና የወደብ ጥያቄን በማስመልከት በአጽእኖት የተናገሩት ነው፡፡
የወደብ አጠቃቀም ዲፕሎማሲያዊ መርህ እና ዓለም አቀፍ ሕግ
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዓለም አቀፍ ሕግ አዋቂነት ስያገለግሉ የቆዩና የዲፕሎማሲ ተንታኝ ሆነው አስተያየቶችን የሚሰጡት አቶ ባይሳ ዋቅዎያ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ባለስልጣናት መካከል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተደጋግመው ስለሚወረወረው የወደብ አገልግሎት ሃሳቦች ላይ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት፤ ጦርነት ሕጋዊ አማራጭ እንደማይሆን በአስተያየታቸው ጠቁመዋል፡፡
“በዓለም ዓለም አቀፍ ሕግና ዲፕሎማሲ ውስጥ ወደብ አልባ አገራት የወደብ አገልግሎትን በጎረቤቶቻቸው በኩል ሲያገኙ በልምድ ሲተገበር የነበረው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው” ነው የሚሉት አቶ ባይሳ፤ ዓለም ላይ በዚህ እንደአብነት የሚጠቀሱትን እንደ ስዊዘርላንድ፣ ቼክሪፐብሊክ፣ ሃንጋሪ እና ዩጋንዳ ያሉትን አገራት ጠቃቅሰው “ኢትዮጵያ በ1991 በህወሓት መራሹ መንግሥት የአሰብን ወደብ ለኤርትራ ግዛት ለመተው ከወሰነበት ጊዜ አንስቶ የዓለም አቀፍ ሕግ ግዛቱን የሚያውቀው የኤርትራ እንደሆነ ነው” ብለዋል፡፡ ያንንም በወቅቱ መደራደር የተሻለ ነበር የሚሉት ተንታኙ አሁን ላይ “ቀይ ባህር መውጫ መንገድ መቶ በመቶ ቢያስፈልገንም ወደ ትግበራው መገባት ያለበት ከጦርነት ውጪ ነው” የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሌሎች አገራት እንደሚፈጸመው ነገሩን በኃይል የማሳካት አድል ግን አላት የሚሉት የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያው ሂደቱን በዚያ መልኩ ለመበየን የሚያስችል የዓለም አቀፍ ሕግ ባለመኖሩ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የሚደረግ ዲፕሎማሲያዊ ውይይት እና የሰጥቶ መቀበል መርህ ከምንም በላይ ጠቃሚ ነው የሚለውን ሃሳባቸውንም አክለውበታል፡፡
ኢትዮጵያ ወደብን ለምን በአንገብጋቢነት ትሻለች?
ስለቀይ ባህርና የኢትዮጵያ የወደብ አንገብጋቢ አስፈላጊነት ደጋግመው የሚነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሰሞኑ ንግግራቸው፤ “ኢትዮጵያን የሚያክል ሀገር ተከባ ተዘግታ ለልጆቻችን መሸጋገር አለባት ብሎ ተገቢ አይደለም” በማለት ኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄዋን ለመመለስ ግን ግጭት እንደማያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
“ኢትዮጵያ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና ለዘላለም ትኖራለች ብሎ የሚያምን ኢትዮጵያዊ ካለ የሞተ ነው” ሲሉም በቁጣ የወረፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ጎረቤት አገራትም የእንደራደር ጥሪን በዚሁ ወቅት አሰምተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የወደብ ይገባኛል ከታሪክ አኳያስ…
የዓለም አቀፍ ሕግ ተንታኙ አቶ ባይሳ ዋቅዎያ እንደሚሉት ነገሮች ከሕግ አኳያ የሚታዩ ከሆነ ከታሪክ ይልቅ አሁን ላይ ማተኮሩ አይቀሬ ነው፡፡ “ታሪክን ተከትሎ የይገባኛል ጥያቄ ማንሳትን እኔ የምቀበለው ነገር አይደለም” የሚሉት የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያው “በታሪክ ፣አሰብ ብቻ ሳይሆን ኤርትራም የኢትዮጵያእንደነበሩ ታሪክ ልብ ቢለውም፤ አሁን ግን አይደሉም በማለት” ከታሪክ ይለቅ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን ማስቀደም መንገዶችን ሁሉ እንደሚያፋጥን ገልጸዋል፡፡ “ወደብ ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ይህን ለማሳካት ደግሞ አንድ ህዝብ የሆነው የኤርትራ እና ኢትዮጵያ ህዝብ በሁለት ግዛት ቢኖሩም ተነጋግረው መግባባት ይችላሉ፡፡ ሁለቱ መንግሥታትም ተነጋግረው ለችግሩን እልባት መስጠት ከነገሮች ሁሉ ቀላሉ እንደሆነ አስባለሁ” በማለት ቀዳሚ ስላሉት አማራጭ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከሲቪል ባለስልጣናትም ባሻገር የኢትዮጵያ ወታደራዊ መኮንኖችና ከፍተኛ የጦር አመራሮች ስለ ጉዳዩ በተደጋጋሚ በሰጡት አስተያየት በቀጣናው የግጭት ስጋት ይፈጥር ይሆን በሚል የሰጉም በርካቶች ናቸው፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር