1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገበያ እና ብር ወዴት እያመሩ ነው?

እሑድ፣ ጥቅምት 30 2018

የውጭ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲወሰን ከተደረገ ወዲህ ኢትዮጵያ ከሸቀጦች የወጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ ዕድገት ቢያሳይም ብር እየተዳከመ ነው። የወርቅ ኤክስፖርት መሻሻል ብር እንዲረጋጋ ሊያደርግ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ተስፋ አድርጓል። ሦስት ባለሙያዎች የተሳተፉበት ውይይት የምንዛሪ ገበያው ብር ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ይፈትሻል።

የኢትዮጵያ ብር እንቁላል እና ዳቦ አጠገብ ይታያል
የኢትዮጵያ ብር እና የደቡብ ሱዳን ፓውንድ በጎርጎሮሳዊው 2025 ደካማ የአፍሪካ መገበያያ ገንዘቦች መሆናቸውን የዓለም ባንክ ሪፖርት አሳይቷል። ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገበያ እና ብር ወዴት እያመሩ ነው?

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ብር እና የደቡብ ሱዳን ፓውንድ በጎርጎሮሳዊው 2025 ደካማ የአፍሪካ መገበያያ ገንዘቦች መሆናቸውን የዓለም ባንክ ሪፖርት አሳይቷል። አፍሪካስ ፐልስ በተባለው ሪፖርት መሠረት ሁለቱ መገበያያ ገንዘቦች በዓመት ውስጥ ከ10 በመቶ በላይ ዋጋቸውን አጥተዋል።

በኢትዮጵያ ቢዝነሶች በገበያ ብቃት ማነስ እና በገደቦች ምክንያት ከባንኮች ዶላር ማግኘት ሲቸገሩ የውጭ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና በፍላጎት እንዲወሰን የሚደረገው ጥረት በትይዩ ገበያው የተመን ዕድገት እየተፈተነ እንደሚገኝ የዓለም ባንክ ሪፖርት ይጠቁማል።

የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ በሐምሌ 2016 ከተደረገ በኋላ ብር ዶላርን ከመሳሰሉ የመገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን እየተዳከመ ቢሔድም ሀገሪቱ ከሸቀጦች የወጪ ንግድ እና ከሐዋላ የምታገኘው ገቢ ማሻሻል አሳይቷል። የሥርዓት ለውጡ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በዓለም ባንክ ብድር እና እርዳታ የሚደጎመው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ቁልፍ አላባዎች አንዱ ነው። 

በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት ኢትዮጵያ ከሸቀጦች የወጪ ንግድ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንዳገኘች የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ ሪፖርት አድርገዋል። ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ ካገኘችው ገቢ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት በዓለም ገበያ የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ የታየባቸው ወርቅ እና ቡና ናቸው። በሦስት ወራት በሀገሪቱ 11.47 ቶን ወርቅ የተመረተ ሲሆን ከወርቅ 1.2 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች። 

የወርቅ ኤክስፖርት ሲጨምር የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት በማሳደግ የብር የምንዛሪ ተመን እንዲረጋጋ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ ለብሎምበርግ ተናግረዋል። ይሁንና አሁንም በመደበኛ እና ትይዩ ገበያዎች መካከል ያለው የተመን ልዩነት መቀራረብ ባለመቻሉ የብር አቅም እየተዳከመ በመሔድ ላይ ይገኛል። 

ይህ ውይይት የብርን የመግዛት አቅም እያደከመ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ግብይት ይፈትሻል። በውይይቱ የፕራግማ ኢንቨስትመንት አድቫይዘሪ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መርዕድ ብሥራት፣ የፋይናንስ ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ እና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት ዶክተር ቀልቤሳ መገርሳ ተሳትፈዋል።
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW