የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ዓለም አቀፍ ሽልማት አገኘ
ቅዳሜ፣ መስከረም 16 2013
የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ የማሕበረሰቦችን ሕይወት እና ዓለምን ለሚያሻሽሉ የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ የጥምረት ሥራዎች የሚሰጠው ዓለም አቀፍ ሽልማት የዓመቱ አሸናፊ ሆነ። የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ሽልማቱ የተበረከተለት ለውድድር ከቀረቡ አምስት እጩዎች መካከል ተመርጦ ነው።
በእንግሊዘኛ ፒስሪ ኢምፓክት አዋርድ (P3 IMPACT AWARD) ተብሎ የሚጠራው ሽልማት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ጥምረት ቢሮ፣ ኮንኮርዲያ በተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እና በቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ፤ የማሕበረሰቦችን ሕይወት ብሎም ዓለምን ለማሻሻል በመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ጥምረት ለሚሰሩ ስራዎች እውቅና ለመስጠት የተዘጋጀ ነው።
የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ከቀረቡ እጩዎች መካከል በተደረገ ምዘና በአሸናፊነት መመረጡን ከተባበሩት መንግሥታት የዓመቱ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በተካሔደው የኮንኮርዲያ ስብሰባ ላይ ትናንት ይፋ ያደረጉት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ጥምረት ቢሮ ዳይሬክተር ቶማስ ዴባስ ናቸው።
የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ከተቋቋመ ጀምሮ 2,400 ንቅለ ተከላዎች ማካሔዱን በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ሽልማቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። መግለጫው እንደሚለው ከተካሔዱ ንቅለ ተከላዎች መካከል 70 በመቶው ስኬታማ ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ብዙኃን መገናኛዎች፣ ሆስፒታሎች የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች፣ ታዋቂ ሰዎች ዓለም አቀፍ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ባደረጉት ትብብር የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ የዓይን ብሌን አይነስውርነት መከላከያ ጥምረት የአገሪቱን የዓይን ብሌን ፍላጎት መቶ በመቶ እንዳሟላ በቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ ድረ-ገጽ የሰፈረው መረጃ ይጠቁማል።
የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ሳይትላይፍ ከተባለ የግብረ ሰናይ ድርጅት ባገኘው ድጋፍ 3,894 የዓይን ብሌኖች ለንቅለ ተከላ ማዘጋጀቱን የገለጸው የቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያው ተቋም ከአሜሪካ የዓይን ባንክ ማሕበር በመተባበር የጥራት ማረጋገጫ እንዳገኘም ገልጿል።
የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ከ17 አመታት ገደማ በፊት በመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥምረት የተመሠረተ ተቋም ነው። የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ፒስሪ ኢምፓክት አዋርድ (P3 IMPACT AWARD) ተብሎ የሚጠራውን ሽልማት በማሸነፍ ሰባተኛው ተቋም ሆኗል።
እሸቴ በቀለ