1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ የዩሮ ቦንድ ዕዳ ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 2 2016

ኢትዮጵያ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በዩሮ ቦንድ ተበድራዋለች የተባለው አንድ ቢሊየን ዩሮ ወለዱ አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል ። የወለዱ አካል ነው የተባለውን 33 ሚሊዮን ዶላር የመክፈል አለመክፈሏ ጉዳይም መነጋገሪያ ሆኗል ። ኢትዮጵያ የዩሮ ቦንድ ዋናው ብድሯንም ሆነ ወለዱን እንድትመልስ በተቀመጠላት ጊዜ መክፈል ካልቻለች ጣጣው ብዙ ነው።

Äthiopien Währung Birr Geld
ምስል፦ Solomon Muchie/DW

የዩሮ ቦንድ ብድር ክፍያ መዘግየት የሚያስከትለው ጫና

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በዩሮ ቦንድ ተበድራዋለች የተባለው አንድ ቢሊየን ዩሮ ወለዱ አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል ።  የወለዱ አካል ነው የተባለውን 33 ሚሊዮን ዶላር የመክፈል አለመክፈሏ ጉዳይም መነጋገሪያ ሆኗል ። ኢትዮጵያ ከሀገር ውስጥ ባለሐብቶች ይልቅ ከውጭ አበዳሪዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ዕዳ እንዳለባት እና ይህም በጥቅሉ እስከ 30 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚገመት የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ለዶይቸ ቬለ ገልፀዋል ። የኢትዮጵያ የዩሮ ቦንድ ዋናው ብድሯንም ሆነ ወለዱን እንድትመልስ በተቀመጠላት ጊዜ መክፈል ካልቻለች ጣጣው ብዙ ነው። በቀጣይ ከአበዳሪዎች ብድር የማግኘት መተማመን ልታጣ እንደምትችል አልፎም የውጪ መዋእለ ንዋይ ፍሰትን የሚቀንስ አደጋ ሊጋርጥ እንደሚችል ባለሙያ ገልፀዋል ። በጉዳዩ ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ለማግኘት የተደረገው  ጥረት ምላሽ አላገኘም ። ለዝርዝሩ የአዲስ አበባ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ ።

የቦንድ ብድር ምን ማለት ነው ?

የቦንድብድር ምንድን ነው ? በዋናነት የዚህ ዓይነቱ ብድር ተጠቃሚዎችስ መንግሥታት እና ሀገራት ወይስ ኩባንያዎች የሚለው በቅድሚያ ለምጣኔ ኃብት ባለሙያው ዶክተር ቀስጠንጢኖስ በርኸ ያነሳነው ጥያቄ ነው።

«ቦንዶች እርግጠኛ ኪሳራ የሌላቸው ኢንቨስትመንቶች ናቸው። ምክንያቱም በ አሥር ዓመትም ሆነ በ ሠላሳ አመትም ሆነ በተወሰነ ጊዜ ባለው ስምምነት ቦንዱ እንዲከፈል ነው ዋናው መሠረታዊ ነገር። የውጭ አበዳሪዎች ሌላ ሀገር ላለ  ኩባንያ የሚያበድሩት ወይም ሌላ ሀገር ላለ መንግሥት የሚያበድሩት ነው። በመንግሥት አካባቢ ብዙ የተለመደ አይደለም» ሲሉ መልሰዋል።

የዩሮ ቦንድ ብድር ክፍያ መዘግየት የሚያስከትለው ጫና

ኢትዮጵያ ክፉኛ ኢኮኖሚዋን ካደቀቀ ጦርነት ወደ ሌላ ጦርነት ተሸጋግራለች። የኮሮና ወረርሽኝም ብርቱ ምጣኔ ኃብታዊ ጫና እንዳሳረፈባት ተደጋግሞ ተገልጿል። በዩሮ ቦንድ የተበደረችውን ጨምሮ ከውጪ አበዳሪዎች እስከ 28 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ የተሽከመች ሀገር መሆኗም ይታወቃል። ያም ሆኖ ግን ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንደሚሉት ሀገሪቱ የዚህ የዩሮ ቦንዱ ወለድ አካል እንደሆነ የተነገረው 33 ሚሉዮን ዶላርን ባለፈው ሳምንት እንድትከፍል የተቀመጠው ቀነ ገደብ ሽግሽግ እንዲደረግላት የመፈለግ ጉዳይ ካልሆነ በቀር መክፈል ትቸገራለች የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

የአውሮጳ ምክር ቤት፤ ሽትራስቡርግ፤ ፈረንሳይምስል፦ Daniel Kalker/picture alliance

ኢትዮጵያ በየአመቱ ወደ ሁለት ቢሊየን ዶላር የዕዳ አገልግሉት ክፍያ ወይም ወለድ የምትከፍል መሆኗንም በአስረጂነት ጠቅሰዋል።

የዩሮ ቦንድአበዳሪዎች በአብዛኛው ግለሰቦችና የግል ኩባንያዎች መሆናቸውን የሚጠቅሱት የምጣኔ ኃብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ኢትዮጵያ በእነዚህ አበዳሪዎች ዕዳ መክፈል እንደተሳናት ግንዛቤ ተይዞ ጉዳዩ አደባባይ ከወጣ ተጽእኖው ቀላል አይደለም።

ከአለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት እና መንግሥታት ጋር የብድር ሽግሽግ እና የመክፈያ ጊዜ ይራዘምልኝ ጥያቄን ለማሳመን የሚደረገው ድርድር እና ንግግር ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ጫናም ብርቱ ጉዳት ያለው ነው።

ኢትዮጵያ በጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር 2023 የመክፈል ግዴታ ካላባት የብድር መጠን 1.5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላሩ የመክፈያ ጊዜው እንዲራዘምላት ከአበዳሪ ሀገራት ይሁንታ ስለማግኘቷ ቀደም ብለው የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW