የኢትዮጵያ ያለፉት ሰባት ዓመታት እንዴት ይታወሳል?
ረቡዕ፣ መጋቢት 24 2017
ኢትዮጵያ ውስጥ በ2010 ዓ.ም. የመንግሥታዊ አመራር ለውጥ ተደርጎ በወቅቱ አገሪቱን ሲመራ በነበረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙት ጠቅላይ ሚኒሰርትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ዛሬ ድፍን ሰባት ዓመታት ተቆጠረ ። ባለፉት ሰባት ዓመታት በበጎም ሆነ በአነቃቂነታቸው የሚታወሱ በርካታ ክስተቶች በአገሪቱ ውስጥ ተከስተዋል። ያለፉትን ሰባቱን ዓመታት አንዳዶች በጎ ለውጦች የሚጎሉበት ሲሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስታወስ እንኳ የሚያሳቅቁ አስከፊ ድርጊቶች የተከናወኑበት ነው ይሉታል ።
ዛሬ መጋቢት 24 ቀን፣ 2017 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ድፍን ሰባት ዓመታትን ደፍነዋል፡፡ መጋቢት 24 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቃለመሃላ የፈጸሙት አቢይ የሥልጣን ዘመናቸው ጅማሮ ከሞላ ጎደል አልጋ በአልጋ የሆነላቸውና አንድነት ጎልቶ የታየበት ነበር ማለት ይቻላል። ይሁንና በኢትዮጵያ ታሪክ አስከፊው ነው የተባለለት የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነትን ጨምሮ በአገሪቱ ትላልቆቹ ክልሎች በኦሮሚያ ክልል እና አማራ ክልል ተራዝመው በመዝለቅ የዜጎችን መከራ ያበዛው አላባራ ያለው ግጭትም የዚሁ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰባት ዓመታት የሥልጣን ዘመን አካል ነው፡፡
ለመሆኑ ያለፉትን ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያውያን እንዴት ያስታውሱታል?
ዛሬ ዕለቱን በማስመልከት በኦሮሚያ ክልል በርካታ ከተሞች እና ከኦሮሚያ ክልልም ውጪ ባሉ የተወሰኑ ከተሞች መንግሥታዊ ለውጡን የሚያሞካሹና ባለፉት ሰባት ዓመታት ተገኙ የተባሉትን ትሩፋቶች ያወደሱ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች ሲከናወኑ ውለዋል፡፡ በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አመራርነት ተገኙ የተባሉት መልካም ለውጦች ተስተጋብተዋል፡፡
አቶ ሰለሞን ተፈራ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፖለቲካል ሳይንስን ባለሙያ እና የአገሪቱን ፖለቲካዊ ሁናቴዎችን በቅርበት ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው፡፡ እንደሳቸው አስተያየት ያለፉት ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን ከመገንባት ጥረቶች ጀምሮ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶች የተገኙበት ነው፡፡ «ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአምስት የኢኮኖሚ ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት የተገኘበትና በፖለቲካም ውይይትን መርሆ ያደረገ አዲስ የፖለቲካ ባህል የሰፈነበተት ነው» ብለዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ የፖለቲካ ተንታኝና የሕግ ባለሞያ የሆኑት ሔኖክ ገቢሳ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ እንደሳቸው አስተያየት ደግሞ ያለፉት ሰባት ዓመታት በጉልህ የሚታወሱት እንዲህ ነው፡፡ «በጣም አስቸጋሪ ዘመኖች ናቸው፡፡ ጦርነት ከመጀመሪያውም ጀምሮ እስካሁን ያልተለየው ብዙ እህት ወንድሞቻችን ያጣንበት አስቸጋሪ ዘመን ነው፡፡ ከልማት አኳያ በከተሞች አካባቢ የመጡ ከተሞች ማዘመን በበጎ ጎኑ ልነሱ ይችላሉ፡፡ ባጠቃላይ ግን ብዙ ነገሮች በተስተናገዱበት ሰባት ዓመታት ጦርነት ከጅምሩ እስካሁንም በመዝለቅ ነው የሚታወሰው» ብለዋል፡፡
ባለፉት ሰባት ዓመታት እንደ አገር ከተገኙ ትሩፋቶች እና ተግዳሮቶች የትኛው ይጎላል?
እንደ ዶ/ር ሔኖክ አስተያየት ጉድለቶቹ ይጎላሉ፡፡ «ጉድለቱ ነው የሚጎላው ምን ጥያቄ አለው» ያሉት ዶ/ር ሔኖክ የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈውን የትግራይ ጦርነት ጨምሮ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ዜጎችን በበርካታ ስፍራዎች ስጋት ላይ የጣለ ነው ያሉትን ግጭትም በጉድለቱ አንስተዋል፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ ባለሞያው አቶ ሰለሞን ግን አስተያየታቸው በተቃራኒው ነው፡፡ «ውጤቱ እንደሚጎላ ማኅበረሰቡ ያውቃል፡፡ ያለው እድገት ላይ የዓለም አቀፍ ተቋማት እና የሃገራት መሪዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ግን ይህ ማለት ችግር የለም ማለት አይደለም፡፡ ያለው ግጭት በዚህ መንግሥት ብቻ የሚቀሰቀስ ሳይሆን ለ100 ዓመታት የተጣሉ የችግር መሰረተ ልማቶች ናቸው» በማለት ለሚስተዋሉ ግጭቶች መንግሥት ብቻ ተጠያቂ እንደማይሆንበት ገልጸዋል፡፡ «አዲስ የፖለቲካ ባህል» ያሉት መፈጠሩንም በማውሳት ያለው እድል መወያየት መነጋገር መሆኑን በመግለጽ አስተያየታቸውን አጋርተዋል።
ዛሬ በኢትዮጵያ የታወሰው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አመራር ሰባተኛ የስልጣን ዓመት እና አባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ መሰረተ ድንጋይ የተቀመጠበት 14ኛ ዓመት መንግሥት በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን እና በባለሥልጣናቱ ዘንድ ዐቢይ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ውሏል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ