1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ "ደህንነት ተግዳሮት" የተባለው "የተደራጀ ሌብነት" በኮሚቴ ሥራ ይቆማል?

Eshete Bekele
እሑድ፣ ኅዳር 25 2015

የኢትዮጵያ መንግሥት የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ኃላፊ እና የብሔራዊ መረጃና ደሕንነት አገልግሎት ባልደረቦችን ጨምሮ በሙስና የተጠረጠሩ ሹማምንት በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል። በጸረ-ሙስና ዘመቻው የጸጥታ፣ የፍትኅና የመሬት አስተዳደር ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል። የጸረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ የአገር ደህንነት ሥጋት የተባለውን ሙስና ማቆም ይችላል?

Hände übergeben Euros
ምስል picture-alliance/U.Baumgarten

ውይይት፦ የኢትዮጵያ "ደህንነት ተግዳሮት" የተባለው "የተደራጀ ሌብነት" በኮሚቴ ሥራ ይቆማል?

This browser does not support the audio element.

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት አዲስ የሰየመዉ ብሔራዊ ኮሚቴ በሙስና የተጠረጠሩ ሹማምንት መታሰራቸዉን ይፋ በማድረግ ሥራውን ጀምሯል። ሰባት አባላት ያሉት ይኸ ኮሚቴ የብሔራዊ መረጃ እና  ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የፍትኅ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እና የፌድራል ሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ የተካተቱበት ነው።

ኮሚቴው "የመንግሥትን ሙሉ አቅም በመጠቀም በተቀናጀ እና በተናበበ ሁኔታ" ሙስና የፈጠረውን ችግር ለመቀልበስ እንደተሰየመ የፍትኅ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ኅዳር 23 ቀን 2015 ከብሔራዊ መረጃና  ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

"የተደራጀ ሌብነት" በኢትዮጵያ ደህንነት ላይ የፈጠረው ተግዳሮት እና "መንግሥት ተግባራዊ ሊያደርጋቸው ለሚፈልጋቸው የኤኮኖሚ እና የፖለቲካ ለውጥ እርምጃዎች ሙስና ትልቅ እንቅፋት መሆኑ" ለኮሚቴው መሰየም ዋንኛ ገፊ ምክንያት ከተባሉ መካከል ናቸው። በጸረ-ሙስና ዘመቻው የአገሪቱ "የጸጥታ እና የፍትኅ ዘርፍ" እንዲሁም "የመንግሥት የመሬት አስተዳደር" ቅድሚያ እንደተሰጣቸው የፍትኅ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የመንግሥት ቤቶች አስተዳደር፣ የፋይናንስ፣ የመንግሥት ገቢ እና ጉምሩክ ሥርዓት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ አስተዳደር እና የመንግሥት ግዢን የመሳሰሉ ዘርፎች ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ከተባሉ መካከል ናቸው። 

"በፍትኅ እና በጸጥታ ዘርፍ ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም የዜጎችን ሰላም እና የሀገርን ደሕንነት የማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን ተገን አድርገው በተለያየ ሕገ-ወጥ መንገድ ከግለሰቦች እና ከንግድ ድርጅቶች ገንዘብ እና ሐብት ለመውሰድ የተንቀሳቀሱ ተጠርጣሪዎች ተለይተዋል" ሲሉ የፍትኅ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደሕንነት አገልግሎት ተቋማት የሥራ ኃላፊ የነበሩ ግለሰቦች በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል። ዐቃቤ ሕጎች፣ የማረሚያ ቤት አዛዦች የፖሊስ ኃላፊዎች እና ዳኞች ከዚህ ቀደም በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር እንደዋሉም የፍትኅ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። 

ለመሆኑ የኢትዮጵያ "ደህንነት ተግዳሮት" የተባለው "የተደራጀ ሌብነት" በኮሚቴ ሥራ ይቆማል? ፖሊስ እና የፍትኅ ተቋማት ችግሩ "የደህንነት ተግዳሮት" ከመሆኑ በፊት መቆጣጠር ለምን ተሳናቸው? ኢትዮጵያ ሙስናን መቆጣጠር ካልቻለች ምን ዓይነት ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ዳፋ ያስከትላል? 

በዚህ የእንወያይ መሰናዶ የኢትዮጵያ ሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋዬ ሻሜቦ፤ የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ የሥራ አመራር ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሳሙኤል ካሳሁን እና የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ተሳትፈዋል። 

ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW