የኢትዮጵያ ሰራዊት ከሶማሊያ አካባቢዎች መውጣት ያለው አንድምታ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 15 2009የሰሞኑ የወታደሮች የቦታ ሽግሽግ የጀመረው በማዕከላዊ ሶማሊያ ሂራን ክልል በምትገኘው ሞኮሪ ከተማ ነበር፡፡ በዚያው ክልል በምትገኘው ኤል አሊ መንደር የሰፈሩ ወታደሮች ከሳምንት በኋላ ተከተሏቸው፡፡ ብዙም ሳይቆይ ከበለድዌይን 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የአልጋን መለቀቅ ዜና ተሰማ፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች መልቀቅ ከፍተኛ ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገው ደግሞ የየቦታዎቹ ቁልፍነት ነው፡፡
ወደ 20 ዓመት ግድም የሶማሊያን ጉዳይ ሲከታተሉ የቆዩት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ አብደታ ድሪብሳ የተለቀቁት ከተሞች ስልታዊ ስፍራዎች በመሆናቸው ጠቀሜታቸው ከፍተኛ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
“ስትራቴጂካሊ ጠቃሚ ናቸው ይባላሉ፡፡ ገዢ መሬት አላቸው ይባላል፡፡ ውሃ አካባቢያቸው ይኖራል፡፡ የውሃ ጉድጓድ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ሰራዊት ለሚፈልጋቸው ነገሮች አመቺ ናቸው፡፡ ቦታዎችን ለመቆጣጠር እና ብዙ ይዞታዎችን ለመቃኘት አመቺ ቁልፍ ቦታዎች ናቸው ነው የሚባሉት” ሲሉ አቶ አብደታ ያብራራሉ፡፡
በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን የተጠቀሱት ሦስት ከተሞች ይሁኑ እንጂ እንደውስጥ አወቅ የዶይቸ ቨለ ምንጮች ከሆነ ግን የኢትዮጵያ ወታደሮች የለቀቋቸው ቦታዎች ብዛት 11 ይደርሳል፡፡ ኢትዮጵያ ሶማሊያ ዉስጥ በዘመተው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ስር ወደ አራት ሺህ ገደማ ወታደሮች አዝምታለች፡፡ እነዚህ ወታደሮች በቤይ፣ ባኮል እና ጌዴኦ ክልሎች ያሉ ተልዕኮዎችን የማስፈጸም ኃላፊነት የተረከቡ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው ሂራን ክልልም ወታደሮቿ ይገኛሉ፡፡ ከአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮዋ በተደራቢነት የሰፈረው ኃይል “የማጥራት እና ጥቃት የመፈጸም ሚና” ያለው ተንቀሳቃሽ ኃይል እንደሆነ የሚናገሩት ምንጮች አሁን ቦታዎችን የለቀቀው ይሄ ኃይል እንጂ በአሚሶም ስር ያለው እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡
ከኢትዮጵያ የሶማሊያ ውሳኔ ጀርባ ምን እንዳለ በመንግስትም ሆነ በአሚሶም በኩል የተገለጸ ነገር ባለመኖሩ የተለያዩ መላምቶች እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ህዝባዊ ተቃውሞ በማየሉ ምክንያት መንግሥት ወታደሮቹን ወደ ሀገር ቤት ለመሳብ በመገደዱ ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ ለአካባቢው የጸጥታ ጉዳይ ስሱ የሆኑትን “የምዕራባውያንን ጫና ለመመከት የተጠቀመበት ዘዴ ነው” ሲሉ የሚከራከሩም አሉ፡፡
እንደ ምንጮች ገለጻ ግን ኢትዮጵያ የአሚሶም የአሁን አወቃቀር እንደገና እንዲከለስ እና በተለያየ ቦታ የሰፈሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሰላም አስከባሪው ስር እንዲካተቱ ያቀረበችው ሀሳብ እስካሁንም ምላሽ ባለማግኘቱ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ በማሰብ ያደረገችው ነዉ፡፡ የእርሷ ወታደሮች ከአካባቢዎቹ መውጣትን ተከትሎ የሶማሊያ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አልሻባብ አካባቢዎቹን መቆጣጠሩ በእርግጥም የምዕራባውያንን እና ጉዳዩን የሚከታተሉትን ሁሉ ቀልብ ገዝቷል፡፡
“በደረሰበት ተደጋጋሚ ጥቃት ተዳክሟል፤ ከዚህ በኋላ ማንሰራራት አይችልም” ሲባልለት የነበረው አልሻባብ በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡ ጭራሽ ኬንያ ድንበር ማንዴራ ላይ ጥቃት አድርሶ 12 ሰዎች ገድሏል፡፡ አቶ አብደታ ግን እንዲህ አይነት ጥቃቶች የአልሻባብን እውነተኛ ገጽታ አያሳዩም ይላሉ፡፡
“የአልሻባብ ሁኔታ ተለዋዋጭ ነው፡፡ አልሻባብ አንዳንድ ጊዜ በእውነታው አለም ካለው ተቃረነ ምስል ያለው ነው፡፡ በአልሻባብ ስም አካባቢውን የሚያስተዳድሩ አለ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሰራዊት ጉዞ ጀመረ ሲባል ውጊያም ሲይደረግ አካባቢውን ለቅቀው ይሰወራሉ፡፡ በአልሻባብ ስም የሚጠቀሙ የሚሊሽያ መሪዎች እና የጦር አበጋዞች አሉ፡፡”
“አልሻባቦች ፊታቸው ተሸፍኖ ነው የሚያስተዳድሩት፡፡ ማንነታቸውን ለመለየት ያስቸግራል፡፡ አልሻባቦች የጎሳ ህግ አይገዛቸውም፡፡ ሲሞት ደግሞ የጎሳ ህግ ጥበቃ ያደርግለታል፡፡ አልሻባብ ሁለቴ ነው የሚጠቀመው፡፡ የሶማሊያ መንግስት ኃይል በየቦታው በተጠናከረ መልኩ አልተደራጀም፡፡ ሰዎች ደግሞ አልሻባብ ጭካኔ የተሞላበት ስራ ስለሚሰራ ቶሎ የመንበርከክ እና በእርሱ የፖለቲካ ማስፈጸሚያዎች የመገዛት ነገር ነው ያለው” ሲሉ ኢትዮጵያ በለቀቀቻቸው ቦታዎች ስለሚተካው የአልሻባብ ኃይል ያብራራሉ፡፡
አልሻባብ ጠንካራም ሆነ አልሆነ የከተሞቹ በታጣቂው ቡድን መውደቅ በሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ ትልቅ ተጽእኖ እንዳለው አቶ አብደታ ይናገራሉ፡፡
“ስጋት ይፈጥራል፡፡ በተለይ ደግሞ አሁን ምርጫ የሚካሄድበት ወቅት ነው፡፡ ስለዚህ [የሶማሊያ] መንግስት በየቦታው ሊፈረከረክ ይችላል፤ ጫና ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ አሁን ጊዜው ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ይህን ከምን ተነስቶ እንዳደረገ እና ለምን እንደሆነ መነጋገር እና መመካከር ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም ለምን ይህን እንደደረገ በተወሰነ መልኩ ጥቆማ ቢሰጥ የሚጎዳ አይሆንም ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡
ሶማሊያ ዉስጥ ለተሰማሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች በአንድ ወቅት ተቆጣጥረዋቸው የነበሩ ቦታዎችን ለቅቆ በሌላ ቦታ መስፈር እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ይህን የምታደርገው ማስፈጸም የምትፈልገውን አጀንዳ ለመወጣት እንደሆነ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ የአሁኑም እንደዚያው ሊታይ እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡
ተስፋለም ወልደየስ
ሸዋዬ ለገሰ